ታንዛኒያ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎችን አድኖ የሚያስር ግብረ-ኃይል አቋቋመች

ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታንዛኒያ ውስጥ አንድ ሃገረ ገዥ በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ያሉ ሰዎችን አድኖ የሚያሥር ግብረ-ኃይል እንደተቋቋመ ይፋ አደረጉ።

የዋና ከተማዋ አስተዳዳሪ የሆኑት ፖል ማኮንዳ የግብረ ኃይሉን መቋቋም ለጋዜጠኞች ይፋ ባደረጉበት ወቅት አሰሳው በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚጀምር አሳውቀዋል።

ግብረ-ኃይሉ ማሕበራዊ ሚድያውን እንደዋና መሳሪያ በመጠቀም በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ያሉ ሰዎችን አድኖ ለማሰር እንደተዘጋጀ ሃገረ ገዢው ይፋ አድርገዋል።

ታንዛኒያ ውስጥ ከተመሳሳይ ፆታ ጋር የፍቅር ግንኙነት መመስረት በሕግ ያስቀጣል፤ በተለይ ይህ ጉዳይ ጥብቅ እየሆነ የመጣው ከፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊ መመረጥ በኋላ ነው።

በዚህ ምክንያት የተመሳሳይ ፆታ ጋር ግንኙነት ያላቸውና ፆታቸውን በቀዶ ህክምና የቀየሩ (ትራንስጀንደር) ግለሰቦች ለመደበቅ ይገደዳሉ።

የማጉፉሊ ቀኝ እጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ፖል ማኮንዳ «ምንም እንኳ በዚህ ጉዳይ ትችት ሊገጥመን ቢችልም፤ እግዚአብሔር ከሚቆጣ ሕዝብ ቢቆጣ ይሻላል» ብለዋል።

ማኮንዳ «ስማቸውን ስጡኝ» ማለታቸውንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቦ «ግብረ ኃይሌ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ማደኑን ይጀምራል» ሲሉ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውንም አክሏል።

እንደ ሃገረ ግዢው ከሆነ ግብረ ኃይሉ ከመገናኛ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት፤ ከፖሊስ እና ከመገናኛ ብዙሃን የተወጣጡ 17 ሰዎች የተካተቱበት ነው።

«እርቃናችሁን ያላችሁበት ፎቶ ካለ ከተንቀሳቃሽ ስልካችሁ ላይ አጥፉት፤ የብልግና ቪድዮም ካላችሁም ዋ!» ሲሉ ማስጠንቀቃቸውም ተነግሯል።

በሃገሪቱ የሚገኙ የኤችአይቪ ክሊኒኮች የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት እያስፋፉ በመሆኑ እንዲዘጉ ይሁን መባሉም እየተሰማ ነው።