የሴቶች መብት ታጋይዋ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ማን ናቸው?

የሴቶች መብት ታጋይዋ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ

የፎቶው ባለመብት, Dominique Charriau

የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት የቤተሰብ፣ የወንጀል፣ የጡረታና የዜግነት ህጎችን በተመለከተ ሴቶችን አግላይ በመሆኑ ሊሻሻል ይገባል በሚሉ ዘመቻዎች፤ የሴቶችን መዋቅራዊ ጥያቄ ወደፊት በማምጣትና ሀገራዊ አጀንዳ እንዲሆን ብዙ በመስራት የምትታወቀው የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ናት።

ይህችን ማህበር ከመሰረቷት አንዷና የመጀመሪያዋ ስራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር የነበሩት በዛሬው ዕለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ የድጋፍ ድምፅ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ናቸው።

ወ/ሮ መዓዛ ማን ናቸው. . .?

የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበርን ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ያገለገሉት ወይዘሮ መዓዛ ከድርጅቱ ጋር በመሆን የህግ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ ዘመቻ ከማካሄድ በተጨማሪ አቅመ ደካማ ለሆኑ ሴቶች ነፃ የህግ ድጋፍና ጥበቃ በመስጠት አገልግለዋል።

አንድ ሰሞን በብዙዎች ዘንድ መነጋጋሪያ የነበረው የ14 ዓመቷ አበራሽ በቀለን ጉዳይ አንዱ ነው።

አበራሽ ጠልፎ የደፈራትን ግለሰብ በመግደሏ ተፈርዶባት የነበረ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ጥብቅና ቆሞላት በነፃ ወጥታለች።

ይህ ታሪክ ዘረ ሰናይ መኃሪ ባዘጋጀው 'ድፍረት' በተሰኘው ፊልም ለዕይታ ቀርቧል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በሴቶችና በህፃናት መብቶች በህግ አማካሪነት ከስድስት ዓመታት በላይ ያገለገሉት ወይዘሮ መዓዛ የሴቶች መብት በአፍሪካ የሚሻሻልበትን፤ እንዲሁም የሴቶች መብት የሚጠበቅበትን፤ ምርምሮችን በማቅረብ እንዲሁም ለኃገራት ህጋቸውን የሚያሻሽሉበትን መንገድ ቴክኒካዊ ድጋፍ የሚሰጥበትን መንገድ በማማከር ሰርተዋል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ተወልደው ያደጉት ወይዘሮ መዓዛ የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ኮሚሽን የህግ አማካሪ የነበሩ ሲሆን በዚህም የሴቶችና የህፃናት መብቶች በህገ-መንግሥቱ እንዲካተቱ በሰፊው ጥረት አድርገዋል።

የፎቶው ባለመብት, Sean Gallup

በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰራውን የኢንተር አፍሪካ ድርጅትን በዳይሬክተርነት በመምራት የ1997 የምርጫ ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር እንዲካሄድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአፍሪካ ቻይልድ ፖሊሲ ፎረም በፖሊሲ አማካሪነት የመሩ ሲሆን በተለያዩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶችና በአፍሪካ ህብረት በአማካሪነት ሰርተዋል።

ከህጉም ወጣ ብለው የመጀመሪያው የሴቶች ባንክ የሆነው እናት ባንክ መስራች ሲሆኑ በቦርድ ሰብሳቢነትም አገልግለዋል።

ይህ ባንክም ለሴቶችና ለሴቶች ኢንተርፕረነሮች የገንዘብን አቅርቦትን ለማሳለጥ የተመሰረተ ባንክ ነው።

በህግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የማስተርስ ትምህርታቸውን በአለም አቀፍ ጥናት ትምህርት ከኮኔክቲከት አግኝተዋል።

በወቅቱም የመመረቂያ ጥናታቸው የነበረው ሴቶች በህዝብ ውሳኔ ላይ ያላቸው ተሳትፎን በጥልቀት ማየት ነበር።

በተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትም ተሳትፎ ያላቸው ወይዘሮ መዓዛ የሞ ኢብራሂም አፍሪካ ገቨርናንስ ኢንዴክስ አድቫይዘሪ ካውንስል አባል ናቸው፤ ከዚህም በተጨማሪ በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ፀሐፊም ተመርጠው የአፍሪካ የሴቶች ኮሚቴ ለሰላምና ለልማትም አባል ሆነው አገልግለዋል።

ለተለያዩ አገልግሎታቸውና በተለይም ለኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ላበረከቱት አስተዋፅኦ የተለያዩ ሽልማት ያገኙ ሲሆን ዘ አፍሪካን ሊደርሺፕ ፕራይዝ ኦፍ ዘ ሀንገር ፕሮጀክትና፤ ኢንተርናሽናል ውሜን ኦፍ ከሬጅ ይገኙበታል።