ፈረንሳዊቷ ሚንስትር ለካንሰር ታማሚዎች ፀጉሯን ለገሰች የሚሉና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች

የፈርንሳይዋ የስርዓተ ፆታ እኩልነት ሚንስትር ማርሌኔ ስቺሃፓ

ኢትዮጵያ

ትናንት ምሽት በአዲስ አበባ መርካቶ በተለምዶ ጭድ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደረሰ የእሳት አደጋ ንብረት ወደመ።

የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ንጋቱ ማሞ እንደገለፁት በቃጠሎው 600 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል።

አደጋውን ለመቆጣጠር 28 የእሳት አደጋ ባለሙያ ተሰማርቶ 3.5 ሚሊየን ብር የተገመተ ንብረት መታደግ እንደተቻለ ኃላፊው ተናግረዋል።

የአደጋው መንስዔ አልታወቀም።

***

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በቡራዩ በተፈጸመው ወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ተጨማሪ የ28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

የፌዴራል መርማሪ ፓሊስ የ10 ሰዎችን የምስክር ቃል መቀበሉን፣ ሀሰተኛ ማህተሞችንና ሰነዶችን ለፎረንሲክ ምርመራ መላኩንና በ17 ባንኮች የገንዘብ ዝውውር ማስረጃ ማጠናቀሩን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

ቀሪ ስራዎችን ለማከናወን ለህዳር 20፣ 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ታንዛኒያ

ታንዛኒያ ውስጥ አንድ ሃገረ ገዥ በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ያሉ ሰዎችን አድኖ የሚያሥር ግብረ-ኃይል እንደተቋቋመ ይፋ አደረጉ።

ግብረ-ኃይሉ ማሕበራዊ ሚድያውን እንደዋና መሳሪያ በመጠቀም በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ያሉ ሰዎችን አድኖ ለማሰር እንደተዘጋጀ ሃገረ ገዢው ይፋ አድርገዋል።

ጉግል

በተለያዩ አገራት ያሉ የጉግል ሰራተኞች ድርጅቱ ለሴቶች ያለውን ያልተገባ አያያዝ በመቃወም ቢሮ ለቀው ወጡ።

ሰራተኞቹ በርካታ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን በሴቶች ላይ ሚደርስ ወሲባዊ ትንኮሳ እንዲቆም፣ የሚያጋጥማቸውን ጥቃትም ለህግ ማቅረብ እንዲችሉ ጠይቀዋል።

ቱርክ

ሳዑዲ አረቢያዊው ጋዜጠኛ ጃማል ካሾግጂ ግድያ አስመልክቶ ቱርክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኦፊሴሊያዊ መረጃ ይፋ አድርጋለች።

ኢስታንቡል በሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ቆንስላ ውስጥ እንደተገደለ የታመነው ካሾግጂ ወደ ቅጥር ግቢው እንደገባ ነበር የታነቀው ስትል ቱርክ መግለጫ ሰጥታለች።

ፈረንሳይ

የፈረንሳይ የስርዓተ ፆታ እኩልነት ሚንስትር ፀጉራቸውን በመቁረጥ በካንሰር ለተያዙ ሴቶች አርቲፊሻል ፀጉር ለሚሰራ ድርጅት ለገሱ።

ሚንስትሯ በድረ ገፅ ላይ ያዩት በየሁለት ዓመቱ ፀጉሯን የምትለግስ ሴት መልዕክት እንዳነሳሳቸው ተናግረው ሌሎችም ፈለጋቸውን እንዲከተሉ ለማበረታታት እንደሆነ ተናግረዋል።

እንግሊዝ

በእንግሊዝ ለህክምና የሚውለው ካናቢስ ለመጀመሪያ ጊዜ በህክምና ባለሙያዎች መታዘዝ ጀመረ።

ህጋዊ ፈቃዱ የተሰጠው ሁለት በሚጥል በሽታ የሚሰቃዩ ልጆች ካናቢስን ለመድሃኒትነት ለመጠቀም አሻፈረኝ ማለታቸውን ተከትሎ ህብረተሰቡ ለመድሃኒቱ ያለውን አመለካከት ለማቃለል ታስቦ ነው።

ቻይና

በቻይና ማካኦ ግዛት አንድ የመንግስት ባለስልጣን ከሰማይ ጠቀስ ፎቅ ላይ ተፈጠፈጡ።

ባለስልጣኑ በድብርት ህመም ለረጂም ጊዜ ሲሰቃዩ እንደነበርና ራሳቸውን ሳይገድሉ እንዳልቀሩ የአገሪቱ ባለስልጣን አስታውቀዋል።