የሳዑዲው ልዑል «ኻሾግጂ አደገኛ ሰው ነበር» ማለታቸው እያነጋገረ ነው

«ኻሾግጂ አደገኛ ሰው ነበር» የሳዑዲው ልዑል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማን «ኻሾግጂ እንደ አደገኛና አክራሪ ኢስላሚስት ነው የማየው» ብለው ለአሜሪካ መናገራቸው እየተዘገበ ነው።

አልጋ ወራሹ ከዋይት ሃውስ ጋር በቀጭኑ ሽቦ ይህን ውይይት ያደረጉት ኻሾግጂ መሞቱ ሳይታወቅ ጠፍቶ ሳለ ነበር ተብሏል።

የአሜሪካዎቹ ጋዜጦች ዋሽንግተን ፖስት እና ኒው ዮርክ ታይምስ ያወጡትን ይህን ዘገባ የሳዑዲ አራቢያ መንግሥት ክዶታል።

ሳዑዲ አረቢያዊው ጃማል ኻሾግጂ ከሃገሩ ተሰዶ አሜሪካ ውስጥ ይኖር የነበረ ሲሆን ልዑሉ ለውጥ እንዲያመጡ በስራው ይወተውት የነበረ ግለሰብ ነበር።

ሬሳው የት ይግባ የት ውሉ ያልታወቀው ኻሾግጂ ኢስታንቡል በሚገኘው የቱርክ ኤምባሲ ውስጥ በመገደሉ ዙሪያ ቱርክ፣ አሜሪካና እና ሳዑዲ አራቢያ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ሳዑዲ አረቢያ ንጉሱ እና ቤተሰባቸው በጋዜጠኛው ግድያ እጃቸው የለበትም ስትል ሙጥጥ አድርጋ ክዳለች፤ «እውነቱን ለማውጣት የማልቆፍረው የለም» በማለት።

ባለፈው ሳምንት ልዑል ሞሐመድ «ወንጀሉ የሳዑዲዎች ልብ የሰበረ ነው» ብለው ማለታቸው አይዘነጋም።

ከትራምፕ ልጅ ባል ጃሬድ ኩሽነር እና ከደህንነት አማካሪው ጆን ቦልተን ጋር በስልክ ያወሩት ልዑሉ «ኻሾግጂ የሙስሊም ወንድማማቾች አባል ነው» ማለታቸውን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።

ልዑሉ ወደ አሜሪካ የደወሉት በፈረንጆቹ ጥቅምት 9 እንደሆነም ተነግሯል፤ ኻሾግጂ ከጠፋ አንድ ሳምንት በኋላ።

ልዑሉ አጋጣሚውን ተጠቅመው አሜሪካ ከሳዑዲ ጋር ያላትን ወዳጅነት በጥብቅ እንድትይዝ አደራ ብለዋል ተብሏል።

በጉዳዩ ዙሪያ ኦፊሴላዊ መግለጫ የሰጡት የኻሾግጂ ቤተሰቦች ጃማል የማንኛውም አክራሪ ቡድን አባል እንዳልነበር ገልፀዋል።

«ጃማል ኻሾግጂ ምንም ዓይነት አደጋ ሊያመጣ የሚችል ሰው አልነበረም፤ እሱን አደገኛ ማለት እንደመሳለቅ ነው» ይላል የቤተሰቡ መግለጫ።