ነዳጅ እንዳለ የሚያመላክት ጥናትን ተከትሎ ዚምባብዌ ነዳጅ ቁፋሮን ልትጀምር ነው

ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ በሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል በኩል የተፈጥሮ ዘይትና የጋዝ ክምችት እንዳለ ተናግረዋል።

የአውስትራሊያው የማዕድን ኩባንያ ኢንቪክተስ ኢነርጂ ከዚምባብዌ መንግሥት ጋር በጥምረት በመሆን የቁፋሮ ስራ አዋጭነትን በመመርመር ላይ ላይ ናቸው።

ይህንን አስመልክቶ ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት ኢንቪክተስ የተባለው ኩባንያ ሙዛራባኒ በሚባለው አካባቢ በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ቁፋሮ ይጀምራል።

ዚምባብዌ በአስር ዓመታት ውስጥ አጋጥሟት የማያውቅ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃለች።

በዚምባብዌ የነዳጅ እጥረት በተደጋጋሚ የሚፈጠር ችግር ሲሆን መብራት መቆራረጥም ያጋጥማል።

"በአካባቢያችን ኢንቪክተስ የተፈጥሮ ዘይትና የጋዝ ክምችት መኖሩን ነግሮን ነበር፤ ምክሮችንም ለግሶናል" በማለት ምናንጋግዋ ተናግረዋል።

ጨምረውም " ውጤቱም ኢንቪክተስ እንደነገረን ሆኖ ለአገራችን የሚያስደስት ዜና ነው" ብለዋል።

የማዕድን ሚኒስትሩ ዊንስተን ቺታንዶ በበኩላቸው ነዳጅ የሚወጣበት ጉድጓድ ከመዲናዋ ሐራሬ በ240 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ለቁፋሮውም ወደ 20 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚገመትም ሮይተርስ ዘግቧል።

ዚምባብዌ በማዕድን የበለፀገች ሀገር ብትሆንም እስካሁን የነዳጅ ምርት አልነበራትም።