ለቀናት የተዘጋው የአላማጣ- ቆቦ መንገድ ተከፈተ

ቆቦ

ለቀናት ተዘግቶ የቆየው የአላማጣ - ቆቦ መንገድ ትናንት ከሰዓት ጀምሮ መከፈቱን የቆቦ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ፅ/ቤት ተወካይ ኢንስፔክተር ዳዊት ዝናቤ ለቢቢሲ ገለፁ።

በዋጃና በአላማጣ የነበሩ ተቃውሞዎችን ተከትሎ በሰዎች ላይ የሚደርስ ድብደባና እስርን በመቃወም ጥያቄ ባነሱ ወጣቶች መንገዱ መዘጋቱን ያስታወሱት ኢንስፔክተሩ ፖሊስ መንገዱን በተደጋጋሚ ለመክፈት ሙከራ ቢያደርግም ወጣቶቹ ጥያቄያችን ካልተመለሰ አንከፍትም በማለት በተደጋጋሚ መንገዱን እንደዘጉት ያስረዳሉ።

ወጣቶቹንም ለማግባባትና ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለቀናት ውይይት መደረጉን ይገልፃሉ።

ይህንኑ ተከትሎ መንገዱን መዝጋት ተገቢ እርምጃ እንዳልሆነና ለቀናት በተዘጋው መንገድ ሳቢያ በተሽከርካሪዎችና በመንገደኞች ላይ መጉላላት እንደደረሰ በማስረዳት መግባባት ላይ እንደተደረሰ ይናገራሉ።

በመሆኑም ከትናንት ከሰዓት ጀምሮ ከወልዲያ -አላማጣ፣ ዋጃም ሆነ ከአላማጣ - ቆቦ ተሽከርካሪዎች መተላለፍ መጀመራቸውን ገልፀውልናል።

ቀደም ብለን ያነጋገርናቸው ሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንሳዔ መኮንን በበኩላቸው ከወጣቶቹና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ማድረጋቸውን ያነሳሉ።

በዚህም "መንገዱ በመዘጋቱ የሚገኘውን ጥቅምና ጉዳት በማስረዳት፣ ስሜታዊነት ብዙም አይጠቅምም በማለት፣ ጥያቄያቸውን በአግባቡ እንዲያቀርቡ ለረጂም ጊዜ የቆየ ጥልቅ ውይይት ማድረጋቸውን ነግረውናል።

የሰሜን ወሎ የፖሊስ መምርያ ኃላፊ ኮማንደር ሃብታሙ ሲሳይ ባለፈው አርብ ጥቅምት 23፣ 2011 ዓ.ም "ከህዝቡ ጋር ውይይት በማካሄድ ላይ እንገኛለን፤ ዛሬ መንገዱን እናስከፍታለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ሲሉ ለቢቢሲ ገልፀው ነበር።

ለቀናት ስለተዘጋው መንገድ የቆቦ ከተማ ነዋሪ ወጣት ብርሃን መንገዱ የተዘጋው ቆቦን አለፍ ብሎ በሚገኝ ሲቀላ በተባለ ወንዝ አቅራቢያ እንደሆነ ነግሮናል።

መስመሩ ዋና መንገድ በመሆኑ ሁልጊዜም በርካታ ተሸከርካሪዎችን ያስተናግዳል የሚለው ብርሃን በርካታ ተሸከርካሪዎች በግምት 200 የሚደርሱ መንገድ ተዘግቶባቸው ቆመው እንደነበር ታዝቧል።

"መጀመሪያ ላይ በወጣቶች አማካይነት ቢዘጋም፤ የአካባቢው ማህበረሰብም ሃሳቡን እየደገፈውና ወጣቶቹ ያነሱትን ጥያቄ እየተጋሩ ነው" ሲልም ይናገራል።

ሌላኛዋ ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈቀደች የከተማው ነዋሪ ደግሞ "መንገዱ በመዘጋቱ ሰዎች እየተጉላሉ፤ ለችግር እየተዳረጉ ነው" ስትል ለቢቢሲ ገልፃ ነበር።

መንገዱ ከተዘጋበት አቅራቢያ ወደ ቆቦ ለመሻገር ባጃጅ እንደሚጠቀሙም እንዲሁም በወልዲያ ወደ ዋጃ አላማጣ የሚሄዱትም ማለፍ እንዳልቻሉና ቆቦ ከደረሱ በኋላ እንደሚመለሱ ገልጻልን ነበር።

ጉዳዩን አስመልክተን ያነጋገርናቸው የሰሜን ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ የሆኑት ኮማንደር ሃብታሙ ሲሳይ መንገዱ የተዘጋው ዋጃና አላማጣ አካባቢ በነበሩት ግጭቶች የሰው ህይወት መጥፋቱንና ንብረት መውደሙን ተከትሎ እንደሆነ አስረድተዋል።

በዚህም ሳቢያ ቀደም ሲልም መንገዶች ተዘግተው የነበረ ሲሆን በውይይት እንደተፈታ አስታውሰው "የንግድ ሚኒባስ አሽከርካሪዎችና ለሥራ የሄዱ የመንግሥት ሰራተኞች ለምን ይደበደባሉ?" በሚል ጥያቄ ወጣቶቹ በድጋሚ መንገዱ ሊዘጉት እንደቻሉ ገልፀውልናል።

ወጣቶቹ የሚያነሱት ጥያቄም የሚፈፀመውን ድብደባ በመቃወምና የክልል ልዩ ፖሊስ ወጥቶ መከላከያ ይግባ፤ የሚል እንደሆነ ኮማንደር ሃብታሙ ይናገራሉ።

"ለሕይወታችን ሰግተናል፤ በዚህም ምክንያት መንገዱን ዘግተናል" ሲሉ መልስ እንደሰጧቸው ገልፀውልናል።

እስካሁን በሰዎችም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ የሚገልጹት ኮማንደሩ መንገዱ የተዘጋው ለተሸከርካሪዎች ሲሆን ሰዎች እንዳይቸገሩ ሌላ የትራንስፖርት አገልግሎት ተመቻችቶ እየተሸጋገሩ እንደነበር ነግረውናል።

ወጣቶቹ መንገዱን ለተሸከርካሪዎቹ ብቻ የዘጉት፤ የሁለቱም ክልል አመራሮች ተነጋግረው መፍትሔ ይስጡን በሚል ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ።