በአሽከርካሪና ተሳፋሪ ጠብ ምክንያት በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ ሕይወት ጠፋ የሚሉና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች

ከድልድይ ላይ ወንዝ ውስጥ የገባው አውቶብስ

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ የተመን ማሻሻያ ማድረጉን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።

አዲሱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተመን ከመጭው ታህሳስ ወር ጀምሮ ይደረጋል ተብሏል።

ደቡብ ሱዳን

የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ከአማፅያኑ መሪ ሪክ ማቻር ጋር ይሰሩ ነበር ያሏቸውን ፖለቲከኞች ከእስር ለቀቁ።

ግለሰቦቹ በጦር መሳሪያ ድጋፍና በስለላ ጥፋተኛ ተብለው የሞት ፍርድ ከተበየነባቸው ከወራት በኋላ ነው ነፃ የወጡት።

ሪክ ማቻር ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቃዊ ግዛት በኢቦላ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው።

እስካሁን 285 ኬዞች እንደተመዘገቡና ወደ ሰሜናዊ ግዛቷ ኪቩ እየተዛመተ እንደሆነ ተዘግቧል።

***

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ካናንጋ ብቻ በአንድ ዓመት 2,600 የሚሆኑ ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች እንዳከሙ ገለፁ።

ጥቃት ፈፃሚዎቹ የታጠቁ ግለሰቦች ሲሆኑ እንደ አንድ የጦር መሳሪያም ይጠቀሙበታል ተብሏል።

ደቡብ አፍሪካ

የደቡብ አፍሪካ የገንዘብ ሚንስትር ባለቤትነቱ የመንግስት የሆነውና በአፍሪካ ግዙፉ የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ መዘጋት አለበት አሉ።

አየር መንገዱ ላለፉት ሰባት ዓመታት ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም ያሉት ሚንስትሩ ችግሮቹ እስኪጣሩ ድረስ አማራጩ መዝጋት ነው ብለዋል።

ይህን ያሉት በአሜሪካ በተካሄደ የባለሃብቶች ስብስባ ላይ ነው።

ሳዑዲ አረቢያ

ሳዑዲ አረቢያዊው ጋዜጠኛ ጃማል ካሾግጂ አካሉ ከተቆራረጠ በኋላ በአሲድ አሟሙተው እንዳስወገዱት የቱርክ ከፍተኛ ባለስልጣን ያሲን አክታይ ይፋ አደረጉ።

ገዳዮቹ ይሄንን ዘዴ የተጠቀሙት ምንም አሻራ ትተው ላለማለፍ እንደሆነ አስረድተዋል።

አሜሪካ

የትራምፕ አስተዳደር ከሶስት ዓመታት በፊት ከኑዩክሌር ስምምነቱ ጋር የተነሳውን ማዕቀብ በድጋሜ ጣለ።

ከኢራን ነዳጅ የሚያስገቡ ስማቸው ያልተጠቀሱ 8 አገራትም ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

ቻይና

በቻይና በአሽከርካሪና ተሳፋሪ ጠብ ምክንያት ወንዝ ውስጥ በገባው የተሽከርካሪ አደጋ 13 ሰዎች ሞቱ።

ተሳፋሪዎችን ጭኖ ሲጓዝ የነበር አውቶቡስ በተፈጠረው ጠብ ሳቢያ 50 ሜትር ከፍታ ካለው ድልድይ ወንዝ ውስጥ መግባቱ ተገልጿል።

ጃፓን

የጃፓኑ ምክር ቤት የአገሪቱን የስደተኞች ህግ ለማለዘብ የቀረበውን ረቂቅ ህግ አፀደቀ።

ህጉ ሁለት የመዳረሻ ቪዛ እንዲኖር የሚያስችል ሲሆን ከውጭ አገር ስራ ለመቀጠር የሚገቡ ዜጎችን የሰው ኃይል እጥረት ባለበት ለማሰማራት ያስችላል።

ጃፓን ጥብቅ የስደተኞች ህግ ያላት አገር ስትሆን ለስራ የሚገቡ ጥቂት የውጭ አገር ዜጎችን ብቻ ትቀበላለች።

ፌስ ቡክ

መረጃ መንታፊዎች 81 ሺህ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን የግል መረጃ ለመሸጥ እየተደራደሩ ነው።

ፌስ ቡክ በበኩሉ የመረጃ ደህንነት ጉዳይ ተደራድሮ እንደማያውቅ ገልፆ፤ መረጃዎቹ በሌሎች ድረገፆች አማካኝነት ያፈተለኩ ሊሆኑ ይችላሉ ብሏል።