ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መበራከት ምንን ያመለክታል?

መሣሪያዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ነዳጅ ጭኖ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ይጓዝ የነበረ መኪና በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንደ ውሃ አካባቢ ተገልብጦ፤ ፖሊሶች ባደረጉት ፍተሻ ወደ 1,291 የቱርክ ሽጉጥ እንዲሁም 97 ክላሽ በቁጥጥር ስር የመዋሉ ዜና የተሰማው ከጥቂት ቀናት በፊት ነበር።

ከተለያዩ አቅጣጫዎች ድንበር አቋርጠው ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ሕገ ወጥ መሳሪያዎች የመያዛቸው መረጃ መሰራጨት ከጀመረ ውሎ አድሯል።

ባለፉት ጥቂት ወራት ባልተለመደ መልኩ መዲናዋ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ህገወጥ የመሳሪያ ዝውውር መበራከቱ እየተሰማ ነው።

በትናንትናው እለት ፌደራል ፖሊስ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው ከሃምሌ 1፣ 2010 ዓ. ም. እስከ ጥቅምት 20፣ 2011 ዓ. ም. 2,516 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ መያዛቸውንና 7,832 የጦር መሳሪያ ጥይቶችም ወደ ሀገር ውስጥለመግባት ሲሉ መያዛቸውን አስታውቋል።

ይህም ብዙዎችን ምን እየተካሄደ ነው ?የሚል ስጋት ውስጥ ከትቷል። መንግሥት ምን እያደረገ ነው ? የሚል ጥያቄም በስፋት እያስነሳ ነው።

ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውሩ በጉልህ ከታየባቸው ክልሎች የአማራ ክልል በዋነኛነት ይጠቀሳል። የክልሉ የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ እንደሚሉት በመተማና ሌሎችም ከተሞች በኩልም ሕገ ወጥ መሳሪያ ለማስገባት ሲሞከር ተይዟል።

"ስጋቱ ቀላል አይደለም" የሚሉት ኃላፊው፤ እንደ መፍትሔ ክልሉ የፍተሻ ቦታዎችን መምረጡን ተናግረዋል። ሆኖም ከተመረጡ የፍተሻ ቦታዎች ባለፈ የሚገኙ አካባቢዎች ለዝውውሩ እንዳይጋለጡ ከማህበረሰቡ ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነም ገልፀዋል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

"ከህገ መንግሥት ቀረጻ ጀምሮ ተሳታፊ ነበርኩኝ" - መዓዛ አሸናፊ

እሳቸው እንዳሉት ለፍተሻ በተመረጡት አካባቢዎች ስካነር (እቃ በኤሌክትሪክ መሳሪያ የሚፈትሽ) ለመግጠም ከፌደራል መንግስት ጋር እየሰሩም ነው።

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር ስማቸው ከሚነሱ ክልሎች ሌላው ነው። ክልሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር እንደመዋሰኑ በዋነኛነት ናኮሞ በተባለ ልዩ ወረዳ ሕገ ወጥ መሳሪያዎች እንደሚገቡ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ባየታ ተናግረዋል።

ቡዋ አልመሀል በተባለ ኬላ አልፎ አልፎም ከመሀል ሀገር መሳሪያ እንደሚገባ ተናግረው፤ ሕገ ወጥ መሳሪያዎችን በግንባር ቀደምነት "በፍተሻ እንይዛለን" ብለዋል። በዘላቂነት የሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት ደግሞ በክልሉና በፌደራል መንግሥት ጥምረት የተዋቀረ ግብረ ሀይል ማቋቋማቸውን ጠቁመዋል።

ሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር የክልሎች ብቻ ሳይሆን የመዲናዋ የአዲስ አበባ ራስ ምታትም ከሆነ ሰነባብቷል። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መሳሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ የመግባታቸው ዜና በተደጋጋሚ እየተሰማ ነው።

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዳደ ደስታ፤ በግለሰቦች ወይም በአነስተኛ ቡድኖች ሊያዙ የሚችሉ ሕገ ወጥ መሳሪያዎች መሰራጨታቸው ሀይል መጠቀም የመንግሥት ብቻ የሆነ ስልጣን ሆኖ ሳለ በሌሎች ሰዎች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች እጅም እየገባ መሆኑን እንደሚያሳይ ያስረዳሉ።

አደገኛ ነው የሚሉትን የሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር፤ በክልሎች ከሚነሱ ግጭቶች፣ ከፕሮፓጋንዳ መሳሪያነቱ እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሀገር ውስጥ ከገቡ ድርጅቶች ጋርም ያያይዙታል።

እነዚህ መሳሪያዎች በዘራፊዎች ወይም ሕገ ወጥ የፖለቲካ አላማ ባላቸው ሰዎች እጅ ሊገቡ የሚችሉበት እድል መኖሩ፤ መንግሥትን ሀይል ከማሳጣቱ ባሻገር ህብረተሰቡን አደጋ ላይ የሚጥልም እንደሆነ ይገልፃሉ።

አቶ ዳደ ዝውውሩ ወጥቶ መግባትንም አስጊ እንደሚያደርገው ይናገራሉ። ኅብረተሰቡ መንግሥት ላይ አመኔታ ሲያጣ ቤተሰቡን ለመጠበቅ ወደ ጦር መሳሪያ ሸመታ ሊያመራ መቻሉ ደግሞ ስጋታቸውን ያከብደዋል።

በአቶ ዳደ እይታ፤ መንግሥት ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን መቆጣጠር የሚገባቸው ተቋሞች መልክ ያልያዙና ያልተደራጁ ናቸው። "አደጋ ሲፈጠር ምላሽ ለመስጠትም በትክክለኛ ቁመና ላይ አይደሉም። ይህን ለማስተካከል ዋጋ ይጠይቃል" ሲሉ ያስረዳሉ።

ሕግና ስርአት ማስጠበቅ የመንግሥት ኃላፊነት መሆኑን አስረግጠው፤ "መንግሥት ሳይዘገይ አስፈላጊ የሆነ ቁጥጥር ማድረግ አለበት። አስፈላጊውን ንቅናቄ ማድረግም አለበት" በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሜጀር ጄነራል ደግፌ በዲ፤ የሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር፤ መሳሪያ ማን እንደሚይዝና እንደሚያዘዋውር የሚወስን ሕግ በመውጣት ሂደት ላይ እንደሆነ ገልጸው፤ በአጭር ጊዜ ተግባራዊ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ኮሚሽነሩ "ለወደፊት መሳሪያ መታጠቅ ያለበትና የሌለበትን ሕጋዊ መልክ ለማስያዝ እየተነጋገርን ነው" ብለዋል። ሕጉ ከወጣ በኋላ ማን መሳሪያ ይይዛል? ማን አይዝም? መሳሪያ እንዴት ይዘዋወራል? የሚሉ ጥያቄዎች መልስ እንደሚያገኙ አክለዋል።

በእርግጥ ከዚህ ቀደም ግለሰቦች በቂ ምክንያት እስካላቸው ድረስ ለመንግሥት አሳውቀው የመሳሪያ ባለቤት መሆን ይችላሉ። ሆኖም ዜጎች ያለ መንግሥት እውቅና መሳሪያ መታጠቅ ከጀመሩ፤ የመንግሥትን ኃይል መገዳደራቸው ስለማይቀር አደጋ ውስጥ እንደሚከት የፓለቲካ ተንታኝና በኬል ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት አወል ቃሲም አሎ (ዶ/ር) ይናገራሉ።

"ተራው ዜጋ በድብቅ መሳሪያ ከታጠቀ ብቸኛ ምክንያቱ ሊሆን የሚችለው ፖለቲካዊ ነው" ብለው፤ ሀገርን አደጋ ላይ እንደሚጥል ያስረዳሉ። በተለይም የጦር መሳሪያ ስርጭቱ በተደራጀ ኃይል ቁጥጥር ስር የሚውል ከሆነ ወደ እልቂት ማምራቱ አይቀርም።

ከዚህ በፊት ያለው ሕግ እንዳለ ሆኖ፤ ሕጉን ማጥበቅ ካስፈለገ አንድ ሰው መሳሪያ መያዝ እንዲፈቀድለት የሚጠየቁ መስፈርቶች ጠንካራ መሆን አለባቸው። መሳሪያ ያለ በቂ ምክንያት እንዲያዝ ከተፈቀደ ችግሩ እየተባባሰ ይሄዳል።

"ተራው ኅብረተሰብ መሳሪያ አያስፈልገውም። በልዩ ሁኔታ አንዳንድ ግለሰቦች ለህይወታቸው የሚያሰጋ ነገር ካለ፣ መንግሥት ፈቅዶ፣ መሳሪያቸው ተመዝግቦ ሊታጠቁ ይችላሉ" ሲሉ ያስረዳሉ።