ደሴ፡ የሰባት ዓመት ህፃን ገድሏል በተባለው የእንጀራ አባት ምክንያት ቁጣ ተቀሰቀሰ

የደሴ ከተማ Image copyright Woizer Sehen Poly Technic College Facebook

በደሴ ከተማ የሰባት ዓመት ልጅ ሬሳዋ በማዳበሪያ ተጠቅልሎ በመገኘቱ የአካባቢው ህዝብ በቁጣ እንደተነሳ የደሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ተስፋየ ጫኔ ገልፀዋል። በትናንትናው ዕለት ተገድላ የተገኘችው ይህች ህፃን ለሰባት ቀናት ያህል ከቤተሰቦቿ ጠፍታ ነበር።

የልጅቷን አሟሟት "በጣም አሰቃቂና ሰይጣናዊ" ያሉት ምክትል ከንቲባው ፖሊስ የህፃኗን ገዳይ ማንነት ባጣራው መሰረት የእንጀራ አባቷ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ግለሰቡ በሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያም ታስሮ ይገኛል።

ጀግኒት ከትናንት እስከ ዛሬ

የተነጠቀ ልጅነት

የግለሰቡን መያዝ የሰሙ ወጣቶች አሰቃቂ ግድያውን በመቃወምና "ፍፁም ከባህላችን ውጭ" ነው በሚል ሰውየው በሞት እንዲቀጣና ተላልፎም እንዲሰጥ ጥያቄ እንዳቀረቡ አቶ ተስፋየ ተናግረዋል።

ጥያቄው በመጀመሪያ የተነሳው በጥቂት ግለሰቦች ቢሆንም በኋላም እየሰፋ መጥቶ የአካባቢውን ማህበረሰብ በሰፊው ሊያካትት ችሏል ብለዋል።

ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መበራከት ምንን ያመለክታል?

የአካባቢው ህዝብ የተቃውሞ ሰልፍ በመውጣትም "ግለሰቡ በአሰቃቂ ሁኔታ ስለገደላት ተሰቅሎ ሊገደል ይገባል" የሚሉ መፈክሮችንና የልጅቷንም ፎቶ በመያዝ ተቃውሟቸውን ገልፀዋል።

"እውነት ለመናገር በከተማችን እንደዚህ አይነት ነገር መፈጠሩ ብዙዎችን አሳዝኗል። ሆኖም ግን ግለሰቡ ተጠርጥሮ እስከተያዘ ድረስ ተጣርቶ በህግ አግባብ በሚጠይቀው መሰረት ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል" የሚሉት አቶ ተስፋየ ይህ ግን በአካባቢው ማህበረሰብ ተቀባይነት አላገኘም።

ከህግ አግባብ ውጭ ሊሰቀል፣ ሊገደል ይገባል የሚለው ድምፅም በርትቶ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያንና አንዳንድ ሆቴሎች ላይ ድንጋይ ተወርውሮ መስታወት እንደተሰባበረም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ ሱቆች ላይ ዝርፊያ የተቃጣ ሲሆን ለማረጋጋትም የፀጥታ ኃይሎች ተኩሰዋል። ቁጥሩን በትክክል ባይገልፁም በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች አሉ።

ቀላል ጉዳት በአንድ የፀጥታ ኃይል ከመድረሱ ሌላ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልተከሰተና ሁኔታዎችም እንደተረጋጉ ምክትል ከንቲባው ጨምረው ገልፀዋል።

ግርግሩ ሲፈጠር ፒያሳ አካባቢ የነበረ ኃይለየሱስ በቀለ የተባለ የዓይን እማኝ በበኩሉ የእንጀራ አባቷ ገድሎ፣ ፒያሳ አካባቢ ጥሏታል የሚለው መረጃ ሲሰማ ሰዎች እንደተጋጋሉና ፒያሳ እንዲሁም የሔደበት ፖሊስ ጣቢያ ሰኞ ገበያ አካባቢ ግርግሮች እንደነበሩ ተናግሯል።

ግለሰቡ ከተያዘ በኋላ ሲሆን ወሬው የተሰማው " በአደባባይ እንግደለው" የሚሉ ድምፆች እንደተሰሙና ከእምነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችም እንደተነሱ ገልጿል። ፖሊሶች የአድማ ብተና እያደረጉ እንደሆነና ትንሽ እንደተረጋጋ ተናግሯል።

ህፃኗ ከእናቷና ከእንጀራ አባቷ ጋር ትኖር የነበረ ሲሆን፤ ዝርዝር መረጃ ባይኖራቸውም ሰውየው ከልጅቷ እናት የወለዳቸው ሌሎች ልጆችም እንዳሉ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል። ከመሞቷ በፊት ተደፍራለች ለሚለው ጥያቄ መረጃ እንደሌላቸው አቶ ተስፋየ ገልፀዋል።