የዓመቱ ሐሰተኛ ዜናዎች በአፍሪካ፡ በኢትዮጵያ ሶማሌዎች ጥልቀት ወዳለው መቃብር እየተወረወሩ ነው መባሉ

በጥያቄ ምልክት የተሰራ ጋዜጣ

በአፍሪካ ውስጥ የሐሰት ዜና መሰራጨት የብሔር ግጭቶችን ማባባስ፣ በመራጮች ዘንድ ግራ መጋባትን በማምጣትና የገንዘብ መዋዠቅን እንዳስከተለ እየተወነጀለ ነው።

ቢቢሲ የሐሰት ዜና በአፍሪካ ምን አይነት ገፅታ አለው በሚለው ጉዳይ ላይ ጥናት ያደረገ ሲሆን በባለፉት 12 ወራት ውስጥም ከፍተኛ ተፅእኖ ማምጣት የቻሉ አምስት ሐሰተኛ ዜናዎችን ተመልክቷል።

አይሸወዱ፡ እውነቱን ከሐሰት ይለዩ

'ሃሰተኛ ዜና '፡ የኢትዮጵያ የማሕበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ስጋት?

1. ናይጀሪዊው የፕሬዚዳንት ተወዳዳሪ በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ድጋፍ ማግኘቱ

ዜናው ምን ነበር?

በአውሮፓውያኑ 2019 ዓ.ም ለሚካሄደው የናይጀሪያ ምርጫ ተወዳዳሪ በሆኑት አቲኩ አቡባከር ስም የተከፈተ ሐሰተኛ የትዊተር ገፅ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ማህበር የሆነውን "አሶሼስን ኦፍ ናይጀሪያን ጌይ ሜን" ለድጋፋቸው ምስጋናን ለግሷል።

በትዊተር ገፁ የሰፈረው ፅሁፍ እንደሚያመለክተው "አቲኩ አቡባከር" ፕሬዚዳንት ሆነው ቢመረጡ ቀዳሚ ተግባራቸው በአገሪቱ ውስጥ አከራካሪ የሚባለውን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ህግን መቀየር ሲሆን፤ ይህ ህግ ሆኖ የፀደቀው በፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን በአውሮፓውያኑ 2014 ዓ.ም ነው።

የተመሳሳይ ፆታ ፍቅርን መመስረት በናይጀሪያ 14 ዓመት ያህል እስር የሚያስቀጣ ሲሆን፤ ጋብቻም የተከለከለ ነው።

ዜናው ምንን አስከተለ?

Image copyright The Nation
አጭር የምስል መግለጫ የሐሰተኛ ዜና የወጣበት የጦማርያን ገፅ

በመጀመሪያ ይህ ፅሁፍ የሰፈረው በጥቅምት ወር ላይ ሲሆን፤ ቀጥሎም ሁለት ጦማሪያውያን ይህንኑ ዜና አወጡት። በዚያው አላበቃም ከ12 ቀናት በኋላ በናይጀሪያ ውስት ታዋቂ የሚባሉት ዘ ኔሽንና ቫንጋርድ የተባሉት ጋዜጦችም ዜናውን ባለበት ይዘውት ወጡ።

ከዚህም በተጨማሪ "ዳይቨርስ" የተባለ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ድርጅት አቡበከር "ነፃ የሆነ አስተሳሰብ" ያላቸው ተወዳዳሪ ናቸው በማለትም ድጋፋቸውን እንደሚለግሱ ገለፁ።

ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩ ግለሰብ የተመሳሳይ ፆታ ፍቅርን መብት መደገፋቸው ሐሰተኛ ዜና ጠንቅ ሊፈጥር የሚችል ጉዳይ ነው። በናይጀሪያ ውስጥ የተመሳሳይ ፆታ ፍቅርን በመቃወም የሚታወቁት የእስልምናና የክርስትና እምነት መሪዎች ተከታዮቻቸውን እንዳይመርጡ መልዕክት ሊያስተላልፉ ይችላሉ።

ሐሰተኛ ዜና መሆኑ እንዴት ታወቀ?

የትዊተር ገፁ የፖለቲከኛው አቲኩ አቡባከር ሳይሆን፤ የፖለቲከኛው ትክክለኛ የትዊተር አካውንታቸው (ገፅ) በትዊተር የተረጋጋጠ ሰማያዊ ምልክት እንዳለው ተረጋገጠ።

ከዚሀም በተጨማሪ በትዊተር ገፁ፣ በጦማሪዎቹ ፅሁፍም ሆነ በጋዜጦቹ ዜና ላይ የተጠቀሰው የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪው ድርጅትም ስለመኖሩ ምንም አይነት ማረጋገጫ የለም።

ድርጅቱ በናይጀሪያ ህግ መሰረት ህጋዊ ሆኖ መመዝገብ አይችልም።

ድርጅቱም ሆነ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ተብሎ የሰፈረው ስፒንኪ ቪክተር ሊ የመጀመሪያ ፀሁፋቸውን በትዊተር ካሰፈሩበት ከጥቅምት ወር በፊት በኢንተርኔት ላይ ስማቸው ተጠቅሶ እንደማያውቅም የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ሲያጣራ ደርሶበታል።

2. የታዋቂዋ ኬንያዊ ጋዜጠኛ የውሸት ምስጋና

ዜናው ምን ነበር?

የሲኤንኤን የቢዝነስ ፕሮግራም አቅራቢ ሪቻርድ ኩዌስት በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ጥቅምት ወር ላይ ለቲቪ ፕሮግራም ቀረፃ ላይ ነበር።

ይህንን ተከትሎም የቀድሞ ዜና አንባቢና ጋዜጠኛ ጁሊ ጊቹሩ በትዊተር ገጿ ሪቻርድ ኩዌስት የኬንያ ቆይታው እንዳስደሰተው ገልፃ ፃፈች።

" የኬንያን አቀባባል የሚወዳደረው የለም። ይሄው በቀጭኔዎች ተከብቤ ቁርስ እየበላሁ ነው። በአለም ባንክ በአፍሪካ ምርጥ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከተባለች ኃገር ይሄንን አይነት አቀባበል ማግኘቴ የሚገርም አይደለም። በእውነቱ ኬንያ ተአምራዊ ናት" የሚል ፅሁፍም እሱን ጠቅሳ በተጨማሪ አሰፈረች።

Image copyright Twitter
አጭር የምስል መግለጫ ሐሰተኛው ጥቅስ

ዜናው ምን አስከተለ?

ጁሊ በትዊተር ከሚሊዮን በላይ እንዲሁም በኢንስታግራም ከ600 ሺ በላይ ተከታዮች ያሏት ሲሆን፤ ዜናው በወጣ በደቂቃዎች ውስጥ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ግለሰቦች ዜናውን አጋሩት።

በሚዲያ ኢንዱስትሪው ታዋቂ ከመሆኗ አንፃር እንዲህ አይነት ሐሰተኛ ዜና ማውጣቷ ብዙዎች አፊዘውባታል።

ሐሰተኛ መሆኑ እንዴት ታወቀ?

የሲኤንኤኑ ጋዜጠኛ ትዊቷን ተመልክቶ እንዲህ አይነት መግለጫ እንዳልሰጠ አስታወቀ። በፃፈችውም ፅሁፍ ላይ ተመርኩዞ ትክክል እንዳልሆነ ምላሽ ሰጥቷታል።

በምላሹም ጁሊ ጊቹሩ ይቅርታ የጠየቀች ሲሆን የመጨረሻ ፅሁፏንም አጥፍታዋለች።

3. በኢትዮጵያ ሶማሌዎች ጥልቀት ወዳለው መቃብር እየተወረወሩ ነው

ዜናው ምን ነበር?

በሐምሌ ወር በአሜሪካ ተቀማጭነቱን ያደረገው ኢሳት ብሄራቸው ኦሮሞ የሆኑ ግለሰቦች ሶማሌዎችን ጥልቀት ወዳለው መቃብር እየወረወሩ እንደሆነ የሚዘግብ ቪዲዮ ይዞ ወጣ።

ቪዲዮው ባለፈው አመት በሁለቱ ህዝቦች አስከፊ ግጭት ባጋተመበት የኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል የተቀረፀ መሆኑን ተገልጾ ነበር።

Image copyright YouTube
አጭር የምስል መግለጫ ቪዲዮው ሰዎች ወደ ጥልቅ ጉድጓሱ ሲወረወሩ ያሳያል

ዜናው ምን አስከተለ?

የቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ቋንቋ ክፍል እንደዘገበው ይህ ቪዲዮ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች በከፍተኛ ሁኔታ በመሰራጨቱ በጂቡቲና በሶማሊያ የሚኖሩ ኦሮሞዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል።

በጂቡቲ ነዋሪ የሆኑ ኦሮሞዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በቪዲዮ ምክንያት ድብደባ የደረሰባቸው ሲሆን፤ የንግድ ቦታቸውም ተዘርፏል።

ሐሰተኛ መሆኑ እንዴት ታወቀ?

ይህ ቪዲዮ በሰኔ ወርም በካሜሮን ፈረንሳይኛና እንግሊዝኛ ተገንጣዮችም መካከል የተከሰተ ግጭት እንደሆነም ተደርጎ ብዙዎች አጋርተውታል።

በኢሳት የቀረበው ቪዲዮ የኦሮሞ ወጣቶችን ድምፅ ከነበረው ትክክለኛ ድምፅ በላይ በማስገባት የቀረበ ነው።

ኢሳት ቪዲዮው ትክክለኛ አለመሆኑን ሲያውቅ ወዲያውኑ ቪዲዮውን ከገጹ ላይ በማንሳት በዩቲዩብ ገጹ በኩል በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።

ነገር ግን ኢሳት ቴሌቪዥን ቪዲዮውን ስለማቀናበሩና ቪዲዮው ሃሰተኛ መሆኑን እያወቀ ስለማሰራጨቱ የሚያመለክት ነገር የለም።

ማስተካከያ ዲሴምበር 23፡ ይህ ጽሁፍ የኢሳት ቴሌቪዥን ቪዲዮውን አለማቀናበሩን ወይም ቪዲዮው ሃሰተኛ መሆኑን እያወቀ እንዳላሰራጨ ግልጽ ለማድረግ መስተካከያ ተደርጎበታል።

4. የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ መልቀቅ

ዜናው ምን ነበር?

በየካቲት ወር የደቡብ አፍሪካው ኤስኤቢሲ ጋዜጠኛ በወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጃኮብ ዙማ ስልጣን ለመልቀቅ መስማማታቸውን ዘገበ።

ባለስልጣናትን እንደምንጭ በመጠቀም ሼቦ ኢካኔንግ በቀጥታ ስርጭቱ ላይ ሰበር ዜና በሚል አስተላለፈው። በወቅቱም የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ከፍተኛ አመራር አባላት በቀድሞው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን ስብሰባ ላይ ነበሩ።

ሌላኛው የደቡብ አፍሪካ ጋዜጠኛም ይህንኑ ዜና በትዊተር ገፁ አጋራው።

ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ በተለያዩ የሙስና ቅሌቶች ከፍተኛ ግፊት እየተደረገባቸው የነበረ ሲሆን፤ ከፓርቲያቸውም በተደጋጋሚ እንዲወርዱ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

ሃገሪቷም ፕሬዚዳንቱ ሊለቁ ይችላል የሚለውን ዜና በጉጉት እየጠበቁት ነበር።

ዜናው ምን አስከተለ?

ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ለቀቁ የሚለውን ዜና ተከትሎ በአንድ ፐርሰንት ጨምሮ የነበረው የደቡብ አፍሪካ ራንድ፤ ቃል አቀባዩ የኤስኤቢሲ ሪፖርትን ውሸት ነው ብለው ማጣጣላቸውን ተከትሎ ወደነበረበት ተመልሷል።

ዜናው ሐሰት ነበር?

የፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ቃል አቀባይ "ሐሰተኛ ዜና ነው" በሚል ሪፖርቱን አጣጣለው።

ነገር ግን ከሶስት ቀናት በኋላ ጃኮብ ዙማ ከስልጣን ለቀቁ።

5. የታንዛንያው መሪ ሴተኛ አዳሪነትን ለማስቀረት ከአንድ በላይ ሚስት ማግባትን መደገፋቸው

Image copyright Zambian Observer

ዜናው ምን ነበር?

የታንዛንያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ሴተኛ አዳሪነትን ለማስቀረት ወንዶች ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት እንዳለባቸው ተናግረዋል የሚል ዜና በከፍተኛ መንገድ ተሰራጨ።

በፅሁፉ እንደተጠቀሰው 14000 ወንዶች በተገኙበት ኮንፍረንስ ፕሬዚዳንቱ ከ70 ሚሊዮን ታንዛንያውያን መካከል 40 ሚሊዮኖቹ ሴቶች እንደሆኑና 30 ሚሊዮኖች ወንዶች እንደሆኑ ገልፀዋል የተባለ ሲሆን ፤ በወንዶች እጥረት ምክንያት ሴተኛ አዳሪነትና ዝሙት እየጨመረ መምጣቱን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል ብሎ ፅሁፉ ጠቅሷል።

ዜናው ምን አስከተለ?

በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመጀመሪያ በዛምቢያ ኦብዘርቨር በየካቲት ወር የታተመው ዜና ምንም አልፈጠረም ነበር። ነገር ግን በታንዛንያ ብሄራዊ ቋንቋ ስዋሂሊ በኒፓሽኦንላይን ድረገፅ የታተመው ፅሁፍ ከፍተኛ ተነባቢነትን አገኘ።

ድረ ገፁንም ተከትሎ በታዋቂው ጃማይ ፎረምስ ድረገፅ መታተሙን ተከትሎ በኬንያ፣ ዛምቢያ፣ ደቡብ አፍሪካና ጋና ድረ ገፆች ለመታተም በቃ።

ሐሰተኛ መሆኑ እንዴት ታወቀ?

የታንዛንያ የመንግሥት ቃል አቀባይ በስዋሂሊ ቋንቋ ፕሬዚዳንቱ እንዲህ አይነት አስተያየት እንደማይሰጡና ሰዎችም ቸላ ሊሉት እንደሚገባ በማውገዝ በትዊተር ገፁ አስቀመጠ።

የቢቢሲ ስዋሂሊም እውነተኛነቱን ለማረጋገጥ ባደረገው ምርምር ትክክለኛ አለመሆኑን አረጋግጧል።

በሐሰተኛው ዜና ፕሬዚዳንቱ የታንዛንያን የሕዝብ ቁጥር 70 ሚሊዮን እንደሆነና የሴቶች ቁጥር ከወንዶች በአስር ሚሊዮን እንደሚደርስ አስቀምጧል።

ነገር ግን በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው የህዝብ ቁጥር ግምት መሰረት የታንዛንያ ህዝብ ቁጥር ከ60 ሚሊዮን በታች እንደሆነና በፆታዎቹም መካከል ይህ ነው የሚባል ልዩነትም እንደሌለ አስቀምጧል።

ይህ ሐሰተኛ ዜና የወጣበት ድረ ገፅም ለብዙ ታንዛንያውያን ከታዋቂው የታንዛንያ ጋዜጣ ኒፓሼ ጋር እንደሚመሳሰልም የቢቢሲ ስዋሂሊ ዘገባ ያሳያል።

ነገር ግን ሐሰተኛ ዜና የወጣበት ድረ ገፅና ጋዜጣው ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላቸው ታውቋል።