ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ተነስቷል

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሀመድ አብዱላሂ መሀመድ Image copyright EDUARDO SOTERAS

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ተጥሎ የነበረውን ማዕቀብ አነሳ።

15 አባላት ያሉት የፀጥታው ምክር ቤት ሰኞ ዕለት ማእቀቡን ለማንሳት ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን፤ የማንሳት ረቂቁም በእንግሊዝ መንግሥት አማካኝነት እንደቀረበ ተገልጿል።

የማዕቀቡን መነሳት በተመለከተ ያነጋገርናቸው በቤልጄም የቀድሞው የኤርትራ አምባሳደር አቶ አምደብርሃን ወልደጊዮርጊስ፤ "ኤርትራ ላይ ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ ፍትሐዊ አልነበረም" ብለዋል።

የፖለቲከኛ እስረኞች ይፈቱ፣ የፕሬስ ነጻነት ይረከበር የሚሉ ጥያቄዎች ሲነሱ፤ የኤርትራ መንግሥት ማዕቀቡን እንደ ምክንያት ሲጠቀምበት እንደነበር "ጥያቄዎቹ ሲነሱ ጦርነት ላይ ነን፤ ማዕቀብ ላይ ነን ሲባል ቆይቷል" በማለት ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፤ የኤርትራን ሕዝብና መንግሥት እንኳን ደስ አላችሁ ብሏል። ማዕቀቡ መነሳቱ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሏል። በቀጠናው ሀገሮች መካከል ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና በሀገራቱ መካካል ጤናማ ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚረዳም ተግልጿል።

ለዘጠኝ ዓመታት ያህል የቆየው ይህ ማዕቀብ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ከመገደብ በተጨማሪ፣ ከፍተኛ የኤርትራ ባለስልጣናት እንቅስቃሴያቸው እንዲገደብና ሀብታቸውን እንዳያንቀሳቅሱ የሚል ነው።

ለሁለት አስርት አመታት ተፋጠው የነበሩት የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥት እርቅ መፈፀማቸውን ተከትሎ፤ የኤርትራ መንግሥት ከሌሎች ጎረቤት ሀገራትም ጋር ግንኙነቱ በመሻሻሉ ምክንያት ማዕቀቡ ሊነሳ እንደተቻለ ተገልጿል።

ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው በቁጥጥር ስር ዋሉ

በጋዛ የእስራኤልና የፍልስጥኤም ግጭት እየተባባሰ ነው

አምነስቲ የሳን ሱ ኪን ሽልማት ነጠቀ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የኤርትራ ጉብኝታቸውን ተከትሎ ኤርትራ ላይ የተጣለው ማእቀብ እንዲነሳ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉትሬዝ ይፋዊ ጥያቄ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አሜሪካን የመሳሰሉ አገራት ኤርትራ የሶማሊያ እስላማዊ አክራሪዎችና አሸባሪነትን ትደግፋለች ብለው በመክሰሳቸውና ይህንንም ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት አልሸባብን እንደሚደግፍ የተባበሩት መንግስታት አጣሪ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት፣ የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን፣ ለሁለተኛና ለሦስተኛ ጊዜ ማራዘሙ ይታወሳል፡፡

ኤርትራ በወቅቱም ጉዳዩን አልተቀበለችውም ነበር።