የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አመፅን በፎቶ

በዐውደ ርዕዩ ከተካተቱ ፎቶዎች አንዱ
የምስሉ መግለጫ,

በዐውደ ርዕዩ ከተካተቱ ፎቶዎች አንዱ

የሮ አዱኛ ፎቶ አንሺ ነው። ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የነበረውን ሀገር አቀፍ ተቃውሞ የሚያሳይ የፎቶግራፍና የቪድዮ ዐውደ ርዕይ በጉራምዓይኔ የሥነ ጥበብ ማዕከልና በጀርመን ባህል ማዕከል (ጎተ ኢንስቲትዮት) አሳይቷል።

ዐውደ ርዕዩ ከሀገራዊው አመፅ ባሻገር ባለፉት ጥቂት ወራት የተስተዋለውን አንጻራዊ ለውጥም ያንጸባርቃል። ፎቶ አንሺው ለውጡን ያሳይልኛል ብሎ ያመነው፤ ተፎካካሪ ፖለቲከኞችና የኪነ ጥበብ ሰዎች ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ የተደረገላቸውን አቀባበል ነው።

የፎቶግራፍና ቪድዮ ስብስቡ "የሮ ኬኛ" የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል። ከአፋን ኦሮሞ ወደ አማርኛ ሲመለሰስ "የኛ ጊዜ" ማለት ነው። የሮ "የኔ ጊዜ" የሚለውን ያለንበትን ዘመን በካሜራው መዝግቦ ለታሪክ ማስቀመጥ ግዴታው እንደሆነ ይናገራል።

የምስሉ መግለጫ,

የተሰባበሩ የሰላም አውቶብሶችም በዐውደ ርዕዩ ይገኙበታል

ሀገራዊው አመፅ የደረሰበትን ጥግ ማሳያ እንዲሆን የመረጠው ሰላም አውቶብሶች በድንጋይ ተሰባብረው፤ በእሳት ጋይተው የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ነው። ፎቶዎቹ በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ያነሳቸው ናቸው።

"ያኔ ሰላም አውቶብስን መሄጃ አሳጥተውት ነበር። ፎቶዎቹ ቄሮ፣ ዘርማና ሌሎቹም የወጣቶች ቡድኖች ተቃውሟቸውን ያሰሙበት መንገድ ትውስታ ናቸው።"

ከቀረጻቸው ቪድዮዎች መካከል ማኅበረሰቡ ተቃውሞውን በጋራ ሲገልጽ፤ በደቦ አንድ ግለሰብ ላይ ወይም ንብረት ላይ እርምጃ ሲወሰድ የሚያሳዩም ይገኙበታል።

"አንድ ሰው 'ቦንብ ይዟል' ቢባል እውነት መሆኑ ሳይጣራ መኪናው ይቃጠላል፤ 'ወያኔ ዝም፤ ወያኔ ዝም' እያሉ ነበር" የሚለው የሮ፤ የቡድን ስሜቱ ከአንድ ሰው ወደሌላው ሲጋባ የሚፈጠረውን ድባብ ቦታው ላይ ተገኝቶ ማስተዋሉን ያስረዳል።

ነገሮች ተለውጠው ለዓመታት የሀገራቸውን መሬት መርገጥ ያልቻሉ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ኪነ ጥበበኞች ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ሌላው የዐውደ ርዕዩ ትኩረት ነው።

ለዓለምፀሐይ ወዳጆ፣ ለጀዋር መሐመድ እና ዳውድ ኢብሳ የተደረገውን አቀባበል አካቷል።

"የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ሲደረግ፤ እኔም በፎቶና በቪድዮ ተቀበልኳቸው። እነሱን ፎቶ ማንሳት መቻል በራሱ ለውጡን አሳይቶኛል።"

የምስሉ መግለጫ,

ለጀዋር የተደረገለት አቀባበል

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ ለተፎካካሪ ፖለቲከኞች 'ወደ ሀገራችሁ ግቡ' የሚል ጥሪ ካቀረቡ በኋላ፤ ጥሪው እውን መሆኑን ያረጋገጠው ለፖለቲከኞቹ ደማቅ አቀባበል ሲደረግላቸው መሆኑን ይናገራል።

"ሰውን ምን ያህል ብትወጂው ነው ከነቀምት፣ ከአርሲ. . . በእግር አዲስ አበባ ድረስ መጥተሽ የምትቀበይው?" ሲል ይጠይቃል። አቀባበል በተደረገ ቁጥር ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ያቀናውም በሁኔታው ስለተገረመ ነው።

"የደስታ ስሜቱን ማየት ለኔ ትልቅ ታሪክ ነው፤ ፎቶዎቹና ቪድዮዎቹም የተከተሰውን ግዙፍ ነገር ያሳያሉ፤ ይህንን ለሰው ማካፈል ግዴታዬ ነው፤ በሥራዎቼ አንዱን የኢትዮጵያ ታሪክ ክፍል አሳያለሁ።"

ዓለምፀሐይ ወዳጆ ታሰለጥናቸው የነበሩ የቀድሞው የህጻናት አምባ ልጆች፤ ዛሬ ነፍስ አውቀው መዝሙር ሲዘምሩላት ማየት፤ ሕዝብ ጀዋርን በአምቦ፣ በጊንጪ፣ በሀዋሳ፣ በሻሸመኔ ሲቀበለው ማየት የማይዘነጋው ታሪክ ነው።

እንደ ፎቶ አንሺነቱ ታሪክን ይሰንዳል። የየእለቱ ክስተት የቀደመውን ቀን ታሪክ እየሸፈነ ስለሚሄድም፤ 'ትላንት ይህንን ይመስል ነበር' ለማለት ካሜራውን ይጠቀምበታል። ሥራዎቹን አሰባስቦ መጽሐፍ ማሳተም ያቀደውም ለዚሁ ነው።

"ተወልጄ እስክሞት ያለው የኔ ጊዜ ነው። የአሁኑ ዘመን የኛም ጊዜ ነው። ስሜም የሮ [ጊዜ ማለት] ነው። ስለዚህ ጊዜን [የጊዜ ሀሳብን] ጠቅልዬ ዐውደ ርዕዩን "የኛ ጊዜ" ብዬዋለሁ።"