የሳዑዲው ልዑል እንዲለቁ የሚቀርቡ ጥያቄዎች 'ቀይ መስመር' ናቸው

ሞሃመድ ቢን ሰልማን ከትራምፕ ጋር ሲጨባበጡ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ "አልጋ ወራሹ ስለግድያው ሊያውቁም ላያውቁም ይችላሉ" - ትራምፕ

የሳዑዲ አረቢያው አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን ስልጣን እንዲለቁ የሚቀርቡት ጥያቄዎች "ቀይ መስመር" ናቸው ሲሉ የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ለቢቢሲ ገለጹ።

ሳዑዲ አረቢያ ከጋዜጠኛ ጀማል ካሾግጂ ግድያ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ውግዘት እየደረሰባት ነው።

አዴል አል-ጁቢር እንዳሉት በኢስታንቡል ቆንስላ ውስጥ በተፈጸመው ግድያ የአልጋ ወራሹ እጅ የለበትም።

ከቀናት በፊት የአሜሪካ ኮንግረስ በግድያው ውስጥ ልዑል ሳልማን ስለመኖራቸው ምርመራ ሊካሄድ እንደሚገባ ፍላጎቱን አሳይቷል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን አሜሪካ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላትን ግንኙነት ተከላክለዋል።

ትራምፕ ውግዘት ከደረሰባት ሳዑዲ ጎን ቆመዋል

«ኻሾግጂ አደገኛ ሰው ነበር» የሳዑዲው ልዑል

ትራምፕ ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ "አልጋ ወራሹ ስለግድያው ሊያውቁም ላያውቁም ይችላሉ" ብለዋል።

"በሳዑዲ አረቢያ ግንኙነታችን ቀይ መስመር ነው። የሁለቱ ቅዱስ መስጊድ ጠባቂዎች (ንጉሥ ሳልማን) እና አልጋ ወራሽ ልዑል (መሐመድ ቢን ሳልማን) ቀይ መስመሮች ናቸው።" ብለዋል አል-ጁቤር።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ሳዑዲ አረቢያ ከጋዜጠኛ ጀማል ካሾግጂ ግድያ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ውግዘት እየደረሰባት ነው

"እነሱ እያንዳንዱን የሳዑዲ ዜጋ ይወክላሉ፤ ሁሉም ዜጋ ደግሞ እነሱን ይወክላል። ስለዚህ የንጉሱንም ሆነ የአልጋ ወራሽ ልዑሉን ስም የሚያጠፋ የትኛውንም ጉዳይ አንታገስም።"

አል-ጁቤር በድጋሚም አልጋ ወራሹ ከግድያው ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው አስረግጠዋል።

"ይህን ግልጽ አድርገናል። በዚህ ጉዳይ ላይ ምርመራ እያካሄድን ሲሆን እጃቸው ያለበትን ግለሰቦችም እንቀጣለን" ሲሉ ተደምጠዋል።

ልዑሉ የኻሾግጂን ገዳዮች ለፍርድ እንደሚያቀርቡ ዛቱ

ሲ አይ ኤ ግድያው ሊፈጸም የሚችለው በአልጋ ወራሽ ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን ትዕዛዝ እንደሆነ ያምናል ሲሉ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን በስፋት ዘግበዋል።

አል-ጁቤር ግን ከእነዚህ ሪፖርቶች በተቃራኒ በመቆም ግድያው በደህንነት ሠራተኞች የተፈጸመ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቱርክ መረጃዎችን ከማሾለክ ይልቅ ስለግድያው የምታውቀውን ሁሉ እንድታቀርብ የሳዑዲው ሚንስትር ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ከግድያው ጋር ተያይዞ አሜሪካ ማዕቀብ ለመጣል ካቀደች የረዥም ጊዜ ፍላጎትን መሠረት ያላደረገ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።