ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ለህግ ባላቸው ቀናኢነት መሆኑ ተገለፀ

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የቀድሞዋ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ ሾሟቸዋል።

ሹመታቸውም በአራት ተቃውሞ፣ ሶስት ተዓቅቦና በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

ወ/ሪት ብርቱካንን ለምርጫ ቦርዱ ሰብሳቢነት ያጩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ሲገልጿቸው "ለመንግሥትም ቢሆን ለማንም በተሳሳተ መንገድ እጅ የማይሰጡ ለህግ ስርዓት ፅኑ እምነት ያላቸው ፤ እምነት ብቻ ሳይሆን ለዚያም ዋጋ መክፈል ዝግጁ መሆናቸውን በተግባር ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስመሰከሩ ናቸው" ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙን ለመገንባት ዕውቀት ያላቸውና በተግባር የተፈተኑ መሆናቸውን ገልፀው የተለያዩ ፖለቲከኞችና ከፍተኛ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ባማከሩበት ወቅትም ለተቋሙ ትክክለኛ ሰው መሆናቸውን እንደመሰከሩላቸው ተናግረዋል።

በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ሹመት ላይ የፓርላማ አባላት በዋነኝነት ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ የነበረው ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከፓለቲካ ፓርቲ ጋር ያላቸው ቁርኝት ምን ያህል የፀዳ ነው የሚል ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በምላሻቸው ተሿሚዋ ገለልተኛና ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ነፃ መሆናቸውን ለእንደራሴዎቹ ያሳወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህግ አውቀው ህግን የሚያስከብሩ መሆናቸውና ፤ ለህግ ባላቸው ቀናኢነት መሆኑን ገልፀዋል።

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለአስር ወራት ያህል በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት ይመሩ የነበሩትን አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያን ተክተው ይሰራሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከተመሰረተ ጀምሮ አቶ ከማል በድሪ፣ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና፣ አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ በቦርድ ሰብሳቢነት ሰርተዋል።

በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደውም ምርጫ 2012 ነፃና ፍትሃዊ ይሆን ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ መንግሥት ቦርዱን እንደአዲስ ማዋቀር አስፈላጊነቱን ተናግረዋል።

"ሃገሬን ሳላስብ የዋልኩበት፤ ያደርኩበት ቀን የለም" ብርቱካን ሚደቅሳ

"ቀጣዩን ምርጫ ከዳር ሆኜ ባልታዘብም ተወዳዳሪ ግን አልሆንም" ብርቱካን ሚደቅሳ

ከጥቂት ቀናት በፊት በስደት ከሚኖሩበት አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ አሜሪካ በነበራቸው ቆይታ ናሺናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ በተባለ ድርጅት ውስጥ በተመራማሪነት ይሰሩ ነበር።

በአሜሪካ ቆይታቸውም በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ስኩል ኦፍ ኬኔዲ በታዋቂው ጥቁር ምሁር ዱ ቦይ በተሰየመው የአፍሪካና የጥቁር አሜሪካውያን ጥናት ማዕከል ውስጥ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በህዝብ አስተዳደር (ፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን) አግኝተዋል። ለባለፉት ሰባት ዓመታትም ነዋሪነታቸውን ያደረጉት በአሜሪካ ውስጥ ነው።

በ1967 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተወለዱት ብርቱካን ሚደቅሳ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በየካቲት 12 የተማሩ ሲሆን፤ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተከታተትለው በህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፌደራል ፍርድ ቤት 3ተኛ ምድብ ችሎት ውስጥ በዳኝነት ሰርተዋል።

የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኛ በነበሩበት ወቅት ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩትን የቀድሞ የኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ስየ አብርሃን የዋስ መብታቸውን በማክበር ውሳኔ በማስተላለፋቸው ከመንግሥት ጋር አለመግባባት ተፈጥሯል።

የፖለቲካ ህይወታቸውንም የጀመሩት ቀስተ ደመና ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲና አንድነት የሚባል ፓርቲን በመመስረት ሲሆን በአመራርነት አገልግለዋል።

ከዚያም በ1997 ዓ.ም በሀገሪቱ ፓለቲካ ውስጥ ተፎካካሪ የነበረው የቅንጅት ለአንድነትና ዴሞክራሲ ፓርቲ ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት ነበሩ።

ህገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ በሚል ክስም ለእስር ከተዳረጉት አመራሮች አንዱ ሲሆኑ፤ የእድሜ ልክ እስራት ቢፈረድባቸውም ከአንድ አመት ተኩል በኋላ በይቅርታ ተፈትተዋል።

በይቅርታ ከተለቀቁ በኋላም አንድነት ለፍትህና ዴሞክራሲ የሚባል ፓርቲ ያቋቋሙ ሲሆን የመጀመሪያ ሊቀመንበርም ነበሩ።

እንደገናም በ2000ዓ.ም የተደረገላቸውን ይቅርታ ጥሰዋል በሚል ለእስር የተዳረጉ ሲሆን ለሁለት ዓመታት ያህልም በእስር ላይ ነበሩ።

በይቅርታ የተፈቱት ወ/ሪት ብርቱካን ሃገራቸውን ጥለው በሃገረ አሜሪካ ለሰባት ዓመታት ያህል ቆይተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች