ወ/ሪት ብርቱካን በወዳጆቻቸው አንደበት እንዴት ይገለፃሉ?

ወ/ሪት ብርቱካን በወዳጆቻቸው አንደበት Image copyright Anadolu Agency

ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በምርጫ 97 ጎልቶ የወጣው የቅንጅት ለአንድነት እና ዴሞከራሲ ፓርቲ ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት ነበሩ።

በሃገር ክህደት ወንጀል ተከሰው ወህኒ ማቀዋል፤ መንግሥት ይቅርታ አድርጌዎለታለሁ ብሎ ከሌሎች የፖለቲካ ሰዎች ጋር እስኪፈታቸው ድረስ።

በይቅርታ ከተለቀቁ በኋላም አንድነት ለፍትህና ዴሞክራሲ የሚባል ፓርቲ ያቋቋሙ ሲሆን የመጀመሪያ ሊቀመንበርም ነበሩ።

ይቅርታው ፖለቲከኞቹ ከእሥር ከወጡ በኋላ በሚያከናውኑት ድርጊት ላይ የተወሰነ በመባሉ ምክንያት ይቅርታው ተሽሮ እንደገና ለእሥሩ ተዳረጉ።

ከወራት በኋላ እንደገና ተፈቱ፤ ወዳጆቻቸውም እልል አሉ፤ ወ/ሪት ብርቱካን ግን እንደቀድሞው ወደፖለቲካ ማዘንበሉን ቸል በማለት ወደትምህርት ዓለም መመለስ ይሻለኛል አሉ።

ከተፈቱ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ወደአሜሪካ አቀኑ፤ በአሜሪካ ቆይታቸውም በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ስኩል ኦፍ ኬኔዲ በታዋቂው ጥቁር ምሁር ዱ ቦይ በተሰየመው የአፍሪካና የጥቁር አሜሪካውያን ጥናት ማዕከል ውስጥ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በህዝብ አስተዳደር (ፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን) አግኝተዋል። ለባለፉት ሰባት ዓመታትም ነዋሪነታቸውን ያደረጉት በአሜሪካ ውስጥ ነው።

በስደት እስከተመለሱበት ወቅት ድረስ ናሺናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ በተባለ ድርጅት ውስጥ በተመራማሪነት ይሰሩ ነበር።

አንዲት ቀንደኛ የቀድሞ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አባል ይሆናሉ ብሎ የጠበቀ ማንም አልነበረም፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀር፤ ለዕጩነት ያቀረቧቸው እሳቸው ናቸውና።

ኢትዮጵያም ይሁን አሜሪካ ሳሉ በቅርብ የሚያውቋቸው ወዳጆቻቸው ወ/ሪት ብርቱካን ለተሰጣቸው ሃላፊነት ትክክለኛዋ ሴት ናቸው ይላሉ።

የቦርዱ ማሻሻያና የብርቱካን ሹመት ምንና ምን ናቸው?

ለሕትመት ዓለም ከተወገደች ዓመታት የሆናት የአዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጅ የነበረው ታምራት ነገራ ስለወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከመመስከር ወደኋላ አልልም ይላል።

«ሃገሪቱ የተሻለች ሃገር እንድትሆን ወደፊት የሆነ ነገር እንደምታበረክት ታውቀዋለች፤ ፖለቲካው ውስጥ ሚና እንደሚኖራት ታውቀዋለች። አሜሪካ ትልቅ የወሰነችው ውሳኔ ከየትኛውም የዳያስፖራ ኮሚኒቲ ራሷን ማግለሏ ነው። በጣም ለሷ ቀላል ነበር፤ በጣም በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይፈልጓት ነበር። ስብሰባ እንኳን አትሄድም ነበር። ራስን ለትልቅ ነገር ማጨት የሚባል ነገር ካለ ብርቱካን ትክክለኛዋ ሴት ነች።»

ታምራት ብርቱካን ለዚህ ሥልጣን ብትበዛ ነው እንጂ አታንስም ባይ ነው፤ የተሳጣትን ነገር ማሳነሴ ግን አይደለም ይላል።

«ብዙ ፖለቲከኞች ፓርቲ መሥርተው ወደሥልጣን መውጣት ነው የሚያስቡት፤ ብርቱካን ግን ከሥልጣን በላይ ማሰብ ችላለች። ጠቅላይ ሚኒስትሩንም በጣም የማደንቀው 'ሪስኩን' በውሰዳቸው ነው። ውለታ ውለውልኛል፤ ምናምን የሚባል ነገር የለም፤ ካልተስማማት አልተስማማትም ነው።»

ከታምራት በተጨማሪ የዞን ዘጠኝ ጦማሪ የነበረችውና በቅርቡ በስደት ከምትኖርባት አሜሪካ የተመለሰችው ሶሊያና ሽመልስም ስለ ብርቱካን የምትለው አላት።

«ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫው ከመንግሥት ተፅዕኖ ለማውጣት ነው ይህን የማደርገው ያሉት ምንም የሚያጠራጥር አይደለም። መንግሥት የምርጫ ቦርዱን ራሱን እንደቻለ ተቋም እንዲቋቋም ፈልጓል ማለት ነው የሚለው ድምዳሜ ላይ እንድንደርስ ያደረገን ውሳኔ ነው።»

• «ሃገሬን ሳላስብ የዋልኩበት፤ ያደርኩበት ቀን የለም» ብርቱካን ሚደቅሳ

ሶሊያና ከትምህርትና ልምዷ ባለፈ የወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የግል ባህሪ ለቦታው ብቁ ሆና እንድትገኝ በጣም ያግዛል ትላለች።

«ፖለቲካዊ ትርጉም ባለው መልኩም ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጉዳዮችም ላይ፤ በማንኛውም ሁኔታ በፍርድ ቤትም ይሁን ባለፈችበት ሕይወት የግል ዕሴቶቿን በማስቀደም አይ ይህ አይደረግም በማለት ትቃወማለች፤ ለእውነት ትቆማለች።» ትላለች

ለበርካታ ዓመታት ከፖለቲካ ሕይወት ፀድታ መኖሯ ደግሞ የበለጠ ለቦታው ብቁ ያደርጋትል ስትል ሶሊያና ሃሳቧን ታጠናክራለች።

"በስደትም ሆና አብዛኛውን ጊዜ የፖለቲካ ተሳትፎ አላደረገችም። በግልፅ ራሷን ከፖለቲካ ካገለለች ዘጠኝ ወይም አስር ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ከዚህ በፊት የነበረው ታሪኳም የሚያሳየው ለቦታው የሚመጥን ዕሴት ያላት መሆኑን ነው። የትኛውም ቦታ ብትሆን፤ ፍርድ ቤት ሊሆን ይችላል፤ የፖለቲካ ፓርቲ፤ በስደትም ውስጥ እኒህ ባህሪዎቿ አይቀየሩም።"

ታምራትም ሆነ ሶሊያን ስለብርቱካን አውርተው የሚጠግቡ አይመስሉም፤ ምንም እንኳን ፤ ሹመቱን የተቃወሙ ባይጠፉም በርካታ ኢትዮጵያውያንም በማህበራዊ ትስስር ዘዴዎች ፎቶ እና ፅሁፎችን በማስፈር ደስታቸው ገልፀዋል

«ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የተሾሙት ለህግ ባላቸው ቀናኢነት ነው»

ተያያዥ ርዕሶች