'ለምን ብዙ ወንዶች በመጀመሪያው የፍቅር ቀጠሮ ሒሳብ መክፈል ይኖርባቸዋል'

አኔ ሩቼቶና እና የፍቅር ጓደኛዋ ዛክ Image copyright አኔ ሩቼቶ

የ27 ዓመቷ አን ሩቼቶ ፀሐፊ ስትሆን ነዋሪነቷ ቶሮንቶ ካናዳ ነው። በፍቅር ግንኙነት ጅማሬ ላይ የሚጠየቅ ወጪን መክፈል ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ጽፋለች።

ለመጀመሪያ ጊዜ የፍቅር ቀጠሮ ላይ መገኘት ስጀምር እናቴ "በነጻ የሚገኝ ነገር የለም" ስትል አስጠንቅቃኛለች። "ወንዶች ዕዳ እንዳለብሽ እንድታስቢ ይፈልጋሉ" ብላ ስለጉዳዩ ታብራራለች።

እናቴ ይህን ያደረገችው በፍርሀት እንድርድ እንዳልሆነ ባውቅም ንግግሯ አዲስ ሰው ባገኘሁ ቁጥር ጭንቀት ይፈጥርብኝ ነበር። አምስት ዶላር የሚያወጣ ቢራውን ወንዶች እንዲገዙ ግዴታ አለባቸው የሚለውን ሃሳብ ለመተው ጊዜ ቢወስድብኝም፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ግን ወደኋላ ተመልሼ አላውቅም።

ከ14 ዓመቴ ጀምሮ የፍቅር ቀጠሮ ላይ እንደተገኘ ሰው አንድ ጥሩ አጋር ማግኘት እንዴት እንደሚቻል እንዲሁም አንድ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ሳገኝ ምን ዓይነት ባህሪዎችን መመልከት እንዳለብኝ ብዙ ጊዜ አስብና አወራ ነበር።

''የአንድ ቤተሰብ አባላት ግድያ'' በቤኒሻንጉል ክልሏ ያሶ ከተማ

". . . ጥፍር መንቀል ሕጋዊ አይደለም ስንለው ብሔሩ ውስጥ ለመደበቅ ይሞክራል" ጠ/ሚ ዐብይ

ታሪክ እየቀየሩ ያሉት ሴቶች

በአሁኑ ወቅት አጋር መፈለጊያ የተለያዩ መተግበሪያዎች እና የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በመኖራቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ የፍቅር ግንኙነትን መመስረት ቀላል ሆኗል።

ሆኖም በመጀመሪያው የፍቅር ቀጠሮ ላይ ማን ነው መክፈል ያለበት የሚለው ግን ጥልቅ ክርክር ያስነሳል።

ሴቶች ከወንዶች እኩል እንዲቆጠሩ ወጪውን ለሁለት በማካፈል የራሳችንን ድርሻ መክፈል አለብን የሚለውን አመክንዮ እቀበለው ነበር። ይህ ችግር እንዳይፈጥር እርግጠኛ ለመሆንም አቅምን ያገናዘቡ ርካሽ እና የሚያምሩ ምግብ ቤቶች፣ ባሮች እና መናፈሻዎችን ሁሌም እመክራለሁ።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ እንደማህበረሰብ ያለን ገቢ በመለያየቱ ሒሳብ ላይ እኩል መካፈል የለብንም ትላለች አን

ከአምስት ዓመት ገደማ በፊት ጓደኞቼና አስተማሪዎቼ ሃሳቡን ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባ የሚያደርገኝን ነገር አስተዋወቁኝ።

እንደግሎሪያ ጄን ዋትኪንስ (ቤል ሁክስ በሚለው የብዕር ስሟ ነው የምትታወቀው) የመሳሰሉ የፌሚኒስት ፀሐፊዎች አሁን ካለው የማህበረሰብ አወቃቀር ማን ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሆነ እንዳስብ አደረጉኝ። እሷና ሌሎችም ከትንሿ የግለሰቦች ግንኙነት ጀምሮ የበላይነት እንዴት እንደሚሠራ እንዳስብ አደረጉኝ።

'በጣም ውድ የአኗኗር ዘይቤዎች'

ሰዎች አሁን ባለው የኅብረተሰብ መዋቅር ላይ ተመስርተው በተለያየ መንገድ ጥቅም ያገኛሉ። ስለዚህ አብረን ጊዜያችንን በምናሳለፈው ሰው ማንነት ላይ በመመስረት ሁለቱም ወገኖች እኩል ክፍያ እንዲከፍሉ አይጠበቅም።

ሴቶች በአማካይ ከወንዶች ያነሰ ገቢ ያገኛሉ። ካናዳ ውስጥ አንድ ወንድ በሥራ ቦታው አንድ ዶላር ሲያገኝ ሴቶች ግን በአማካይ 0.69 ዶላር ያገኛሉ።

ይህ ማለት የኑሮ ወጪያችን ዝቅተኛ ነው ማለት አይደለም፤ እንዲያውም በብዙ ሁኔታዎች በጣም ውድ ሊሆን ይችላል።

በሴቶች ገጽታ እና ባህሪ ዙሪያ የሚጠበቁ ነገሮች ቁሳዊ እና የግል ወጪዎች አላቸው። የሴቶች አካላዊ ገጽታዎች በጣም ትልቅ ደረጃዎች ላይ የተቀመጡ ሲሆን ከመዝናኛ ኢንዱስትሪው እስከ ኋይት ሀውስ ድረስም በተደጋጋሚ የማፌዣ ማዕከል ይሆናሉ።

በቤተሰብ፣ በሥራ፣ በፍቅር ግንኙነት፣ በጓደኝነት እና በሁሉም የህይወታችን ክፍሎች ከወንዶች ይልቅ የተረጋጋን፣ ይበልጥ የምንረዳ፣ የምንገነዘብ፣ ተለዋዋጭ እና ሚዛናዊ እንድንሆን ይጠበቃል። እነዚህን ማሟላት በቁሳዊ እና በስሜታዊ መልኩ ካየነው በጣም ውድ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ የክፍያ ጉዳይ የወንዶች ወይንም የሴቶች በሚል የሚከፈል አይደለም። በጾታ፣ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ ደረጃ፣ በዘር፣ በዜግነት እና በሌሎች ላይ የተመሠረቱ የተለያዩ ተሞክሮዎች አሉን።

እኩልነት እና ድርሻ አንድ አይደሉም። እኩልነት ማለት ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ጫማዎች ያገኛል ማለት ነው። ድርሻ ደግሞ ሁሉም ለእግሮቹ የሚስማማውን ጥንድ ጫማዎች ያገኛል ማለት ነው። ጥሩ ግንኙነት በሚመሠረትበት ጊዜ ሰዎች ድርሻቸውን ለማሳካት ይጥራሉ።

Image copyright Anne Rucchetto
አጭር የምስል መግለጫ አን እና የወንድ ፍቅረኛዋ ዛክ ጋር ከአንድ ዓመት በላይ አብረው ቆይተዋል

በመጀመሪያ ፍቅር ቀጠሮዬ ላይ ስለውድ የመኪናው አይነት እና ስለጎበኛቸው ቦታዎች በጉራ የሚያወራው ሰው ሂሳቡን አካፍሎ የራሱን ብቻ ለመክፈል ሲፈልግ ማየቴ ግራ አጋብቶኝ ነበር። የሚያስደንቀው ነገር እነዚህ አለን የሚሉ ወንዶች ናቸው ብዙ ጊዜ እኔን እና ጓደኞቼን "እኔ ፌሚኒስት ስለሆንኩ ሒሳቡን እንካፈል" ሚሉት።

የሴቶች የሥራ ክፍያ ዝቅተኛ ስለመሆኑ ወንዶች አመኑም አላመኑም ዝቅተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሴቶች አነስተኛ ክፍያ እንደሚያገኙ ወንዶች ተስማሙም አልተስማሙም በቀጥታ ጥቅም ያገኙበታል።

ይህ ማለት ወንዶች ሁሌም ጠንክረው አይሠሩም ወይም ሁሌም መክፈል አለባቸው ለማለት አይደለም። በፍቅር ቀጠሮው ላይ ከተገኘው ወንድ በላይ ገቢ ካለኝ ሂሳቡን በመክፈሌ ወይንም በመጋራቴ ደስተኛ ነኝ።

በመጀመሪያ የፍቅር ቀጠሮ ላይ ወንዱ በመክፈሉ "ዕዳ" እንዳለብኝ እንዳውቀው የሚያደርግ ነገር ካደረገ ሂሳቡን በመክፈል ከእሱ ጋር ያለኝን ግንኙነት እዘጋዋለሁ። ይህን የመሰለው ኋላ ቀር አስተሳሰብ የአመለካከት፣ የክብር እና የስምምነት ችግር መኖሩን ያሳያል።

'ሚዛናዊ ያልሆኑ ፈተናዎች'

ከወንዶችም ሆነ ከሴቶችም ጋር የፍቅር ቀጠሮ ነበረኝ። በሚያስደንቅ ሁኔታ በማንኛውም ጊዜ ከሴት ወይም የጾታ ልዩነትን ከሚያከብር ሰው ጋር ለፍቅር ቀጠሮ ስወጣ ሒሳብ ለመክፈል እንሽቀዳደማለን።

ከአሁኑ ጓደኛዬ ከዛክ ጋር ከአንድ ዓመት በላይ ቆይቻለሁ። እንስሳትን እንደሚወድ ሲነግረኝና ስለ ጓደኞቼ ያለውን አድናቆት ሲገልጽ ስለእርሱ መልካም ስሜት የነበረኝ ሲሆን ስለሠራተኞች መብት ደግሞ ተመሳሳይ ሀሳብ አለን። ለመጀመሪያ ፍቅር ቀጠሯችን እሱ ሲከፍል ለሁለተኛው እኔ ነበርኩ የከፈልኩት።

አሁን አብረን ለግብዣ ስንወጣ ወይም አንዳችን የሌላችንን ቤት በምጎበኝበት ጊዜ አቅማችን በሚፈቅደው መሠረት ወጪን እንጋራለን። ይህ ለወደፊቱ ሊለወጥ ቢችልም ለሁለታችንም የሚሰራ ሚዛን ሆኖ አግኝተነዋል። ዋነኛው ግባችን ሁለታችንም እንደተከበርን እንዲሰማን እና መጠቀሚያ እንዳልሆንን ማረጋገጥ ነው።

የመጀመሪያ የፍቅር ቀጠሮዎች በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ሰዎች የተለያዩ የሃብት ድርሻ ያላቸው መሆኑን ለመገንዘብ አነስተኛ አጋጣሚ ነው። ጥሩ ጓደኛ እና ጥንዶች ለመሆን የምንፈልግ ከሆነ ሚዛናዊ ያልሆኑ የኃይል አለመመጣጠኖችን መጋፈጠጥ በሁሉም ግንኙነቶች ውስጥ ወሳኝ ነው።

በመጀመሪያው ፍቅር ቀጠሮ መክፈል የየትኛውንም የግንኙነት መጨረሻ አይገልጽም።

ግንኙነት ይበልጥ በተጠናከረ ቁጥር ግለሰቦቹ ይበልጥ የሚስማማቸውን ቀመር ይመርጣሉ። በመጀመሪያው ፍቅር ቀጠሮ መክፈል ያለባቸው (ወይም የሌለባቸው) እነማን እንደሆኑ የተለያየ ግምት ቢኖረንም አሳቢነት ግን ሁልጊዜም ጥሩ ነው።

100 ሴቶች ምንድን ነው?

የቢቢሲ 100 ሴቶች ከዓለም ዙሪያ 100 ተጽዕኖ ፈጣሪ እና አነሳሽ ሴቶችን በየዓመቱ በማሳወቅ ታሪኮቻቸውን ያጋራሉ።

የአውሮፓዊያኑ 2018 በዓለም ዙሪያ ለሴቶች መብት አንድ ታሪካዊ ዓመት ሆኗል። ስለዚህ ቢቢሲ 100 ሴቶች ፍቅር፣ ንዴት እና ቁጣ ተጠቅመው እውነተኛ ለውጥ በአካባቢያቸው የሚገኘውን ዓለም የሚፈነጥቁ ናችው።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ