ታሪክ እየቀየሩ ያሉት ሴቶች

መዓዛ አሸናፊ Image copyright ullstein bild
አጭር የምስል መግለጫ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ

በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ስር ኢትዮጵያ እየተቀየረች ይመስላል። ሴቶች ከተለመደውና ባህላዊ ከሆነው በቤተሰብ ላይ የተንጠለጠለን ሃላፊነት በማለፍ ከፍተኛ በሚባሉ መንግሥታዊ ቦታዎች እየታዩ ነው።

አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያዊያን በቀድሞው ዘመን ስለነበረችው ታላቋ ንግሥት ሳባ በኩራት ሲያወሩ ቢደመጡም፤ ማህበረሰቡ ግን አሁንም የወንዶች የበላይነት የሚንጸባረቅበትና ተቀባይነት ያለው አስተሳሰብ ነው።

''የማህበረሰቡ የአፍ መፍቻ የወንዶች የበላይነት ነው። ከልጅነታችን ጀምሮ ሴቶችን ዝቅ አድርገን እየተመለከትን ነው ያደግነው" ትላለች የሥርዓተ-ጾታና የህግ ባለሙያዋ ህሊና ብርሃኑ።

የሴቶች መብት ታጋይዋ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ማን ናቸው?

"የመከላከያ ሚኒስቴርን በተሻለ መልኩ መምራት ይቻላል" ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

ሴት የሰራችው ቤት መሰረት የለውም የሚለው አባባልና ሌሎች ተመሳሳይ አነጋገሮች ደግሞ በማህበረሰቡ ውስጥ ላለው ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የመመለክት ማሳያ ናቸው ትላለች ህሊና።

102.5 ሚሊዮን ከሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ ግማሾቹ ሴቶች ሲሆኑ፤ አብዛኛዎቹ በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩት ሴቶች ሃላፊነት ደግሞ ህጻናትን ከመንከባከብና እንደ ውሃ መቅዳት፣ ምግብ ማብሰል ያሉ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ከመስራት አይዘልም።

Image copyright AFP

ከኢትዮጵያ መንግሥትና ተባባሪ አካላት የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው፤

  • 25% የሚሆኑት ሴቶች ትልልቅ ውሳኔዎችን ለባሎቻቸው አሳልፈው ይሰጣሉ
  • 50% የሚሆኑት በትዳር አጋራቸው ጥቃት ይደርስባቸዋል
  • ከ20% በታች የሚሆኑት ሴቶች ብቻ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ይከታተላሉ
  • ከ40% በላይ የሚሆኑት ደግሞ 18 ዓመት ሳይሞላቸው ወደ ትዳር ይገባሉ

እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ወደ ኋላ በሚጎትቷት ሃገር ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ሴቶችን ወደ ከፍተኛ መንግሥታዊ ሃላፊነቶች የማምጣት ውሳኔ በብዙዎች ዘንድ ይሁንታን አግኝቷል።

ከኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ እስከ ሣህለወርቅ ዘውዴ

"ማንም መብታችንን ሊሰጠን ስለማይችል፤ ሴቶች ማንንም ሳይጠብቁ በራሳቸው መታገል አለባቸው"

ብዙ የመብት ተሟጋቾችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ፤ ለሴቶች የሚሰጠውን ግምት የሚቀይሩ ብዙ ለውጦች ወደፊትም ልናይ እንችላለን እያሉ ነው።

የ42 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሾሟቸው 20 ሚኒስትሮች መካከል ግማሾቹ ሴቶች ሲሆኑ፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ግን ሃላፊነቱን የሰጡት ለአራት ሴቶች ብቻ ነበር።

በአሁኑ ሰዓትም በአፍሪካ ውስጥ በከፍተኛ የመንግሥት ሃላፊነት ቦታዎች ላይ የሴቶች እኩል ተሳትፎ ያለው በኢትዮጵያና ሩዋንዳ ብቻ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ያለእድሜ ጋብቻን ለማስቀረት ያደረገችው ከፍተኛ ትግል ላይ ተመስርታ ታዋቂዋ የሆሊዉድ ተዋናይት 'አንጀሊና ጆሊ' በአውሮፓውያኑ በ2014 ፊልም እሰከመስራት ያደረሰችው የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ጠበቃ መዓዛ አሸናፊን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አድርገው ሾመዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ በተለያዩ ሃላፊነት ቦታዎች ላይ የሰሩት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙ ሲሆን፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዋ ቢልለኔ ስዩም ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ተብለው ሥራቸውን ጀምዋል።

Image copyright Getty Images

የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአሁኑ ሰአት በአፍሪካ ብቸኛዋ ሴት ፕሬዝዳንት ናቸው።

ለሴቶች መብት የሚከራከረው የየሎ እንቅናቄ አባል የሆነችው ረድኤት ክፍሌ ለቢቢሲ ስትናገር ''እንደዚህ አይነት ነገር አይተን አናውቅም። ለአይናችን አዲስ ነው። ሃላፊነቱ ምንም ይሁን ምን የአመራር ክህሎታቸውን ለማሳደግ ይረዳቸዋል'' ብላለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሴቶች ያላቸውን ክብርና እምነት ገና የበዓለ ሲመታቸው ንግግር ላይ ስለ ለእናታቸው ምስጋና በማቅረበ ነው ያሳዩት።

''እናቴ ልክ እንደማንኛዋም ኢትዮጵያዊ እናት ሩህሩህና ጠንካራ ሰራተኛ ነበረች፤ ምንም እንኳን አሁን በህይወት ባትኖርም ላመሰግናት እፈልጋለው'' ብለው ነበር።

''በተጨማሪም የእናቴን ቦታ በመተካት ላገዘችኝ ባለቤቴም ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለው'' የሚለው ንግግራቸው በከፍተኛ ጭበጨባ ነበር ፓርላማው የተቀበለው።

'ሴቶች ከወንዶች አንጻር ከሙስና የጸዱ ናቸው'

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ወር ውሳኔያቸውን ሲያስረዱ ''ሴቶች ከወንዶች አንጻር ከሙስና የራቁ ናቸው። የምንፈለገውን ሰላም ለማምጣትም ይረዱናል'' ብለው ነበር።

ከ60 በላይ የመንግሥት ሃላፊዎች፣ የመንግሥታዊው ተቋም ሜቴክ ዋና ሃላፊና የቀድሞ የደህንነት ቢሮው ምክትል ከሙስናና ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ብዙ ሰዎች ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመክንዮም እውነት ነበር እንዲሉ አድርጓቸዋል።

አበባ ገብረስላሴ በ1997 ምርጫ ወቅት በግሏ የፓርላማ አባል ለመሆን ተወዳድራ አልተሳካላትም ነበር፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እርምጃዎች ደግሞ ወደፊት ብዙ ለውጥ ይዞ እንደሚመጣ ታስባለች።

ወ/ሪት ብርቱካን በወዳጆቻቸው አንደበት

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ መኮንን ፍሰሃ እንደሚሉት ከሆነ ግን እነዚህ ወደ ከፍተኛ ስልጣን የመጡት ሴቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሳሳቱ እንኳን አይሆንም ብሎ የመከራከር አቅም ላይኖራቸው ይችላል።

የህግ ባለሙያዋ ህሊና ግን በዚህ ሃሳብ አትስማማም።

''እነዚህ ሴቶች ወደ ስልጣን የመጡት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሁንታን ስላገኙ ብቻ ወይም በሥርዓቱ ችሮታ ሳይሆን፤ ለቦታው የሚመጥን ከፍተኛ ብቃት ስላላቸውና ጠንካራ ሰራተኞች ስለሆኑ ነው'' ትላለች።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ድፍረት ሆሊዉድ ውስጥ ታይቷል

ጥቂት ስለ ድፍረት ፊልም?

የአሁኗ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ የኢትዮጵያ ህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበርን በመመስረትና ሴቶች ላይ የሚስተዋሉ አግላይ ህጎችን በመቃወም ትታወቃለች።

ለመዓዛ አሸናፊ እንደ ትልቅ ስኬት የሚቆጠርላት አንዲት የ14 ዓመት ታዳጊን ወክላ ፍርድ ቤት የተከራከረችበት አጋጣሚ ነው። ልጅቷ ፍርድ ቤት የቀረበችው ጠልፎ ወደ ቤቱ በመውሰድ አስገድዶ የደፈራትን ባሏን በመግደል ወንጀል ተከሳ ነበር።

በፍርድ ቤት ክርክር መዓዛ አሸነፈች። ከዚህ አጋጣሚ በኋላም ኢትዮጵያ የጠለፋ ጋብቻን ከለከለች። ይህ ክስተት ብዙ ዓለማቀፍ እውቅና ያላቸው ሰዎች አይን መሳብ ቻለ።

ታዋቂዋ የሆሊዉድ ተዋናይት አንጀሊና ጆሊ በዚህ ታሪክ ላይ ተመስርቶ ተሰራውን ''ድፍረት'' የተባለውን ፊልም ፕሮዲዩስ አደረገችው።

ወ/ሮ መዓዛ ''ሁልጊዜም የማስበው ስለ አገልግሎት እንጂ ስለ ሹመት አይደለም''ሲሉ ሹመቱን እንዳልጠበቁት ቢገልጹም፤ ሹመቱ ''ትልቅ ክብር ነው" ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች