ምግብ ማብሰልና ማጽዳት የቤት ውስጥ ጥቃቶችን ለመቀነስ

ህጻን ልጁን የያዘ አባት Image copyright Elaine Jung

ሩዋንዳ ውስጥ ወንዶችን የቤት ውስጥ ስራ እንዲሰሩ በማድረግ በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመቀነስ የሚረዳ ፕሮግራም በሙከራ ላይ ነው።

ሙሆዛ ዣን ፒዬር ከዚህ በፊት ባለቤቱን ይደበድባት ነበር። የባለቤቱ ስራ ልጅ ለመውለድና እነሱን ለመንከባከብ ብቻ እንደሆነ ያስብም ነበር።

'' የአባቴን ፈለግ ነበር የተከተልኩት። አባቴ በቤት ውስጥ ምንም አይነት ስራ አይሰራም ነበር።'' ይላል።

" ልክ ወደ ቤት ስገባ የሆነ ያላለቀ ስራ ካለ ሁሌም ቢሆን እንጣላለን። ሰነፍ ነሽ እያልኩ እጮህባታለሁ። ለምን ወደ ቤተሰቦችሽ ተመልሰሽ አትሄጂም እላታለሁ።''

ነገር ግን በቤታችን ውስጥ ድንገት ትልቅ ለውጥ መጣ። ሙሆዛ ዣን ፒዬር ምግብ ማብሰልና ቤት ማጽዳት ተማረ።

በአለም ላይ በየቀኑ 137 ሴቶች በህይወት አጋሮቻቸውና በቤተሰቦቻቸው ይገደላሉ

ታሪክ እየቀየሩ ያሉት ሴቶች

የፒዬር መንደር ምዉሊሬ የምትሰኝ ሲሆን የምትገኘው በምስራቃዊ ሩዋንዳ ነው ። በዚህች መንደር በመተዋወቅ ላይ ያለው የሙከራ ፕሮጀክት ምስጋና ይግባውና ወንዶች በቤት ውስጥ ምግብ እንዲያበስሉና ሌሎች ስራዎችም መስራት እየተበረታቱ ነው።

ፕሮጀክቱ 'ባንደቤርሆ' ይባላል። እንደ ፒዬር ላሉ የአካባቢው ወንዶች ጥሩ ተሞክሮ እያስተማረ ነው።

ፒዬር ትምህርት ቤት ገብቶ ምግብ ማብሰል፣ ቤት ማጽዳትና ልጆችን መንከባከብ የሚችልበትን መንገዶች ተምሯል።

''በክፍሉ ውስጥ ወንዶች ቤት ማጽዳት ይችላሉ ወይ ተብለን እንጠየቃለን፤ የሁላችንም መልስ አዎ ይችላሉ ነው።''

'' በመቀጠል ከእናንተ መካከል ማነው ቤቱን የሚያጸዳ ሲሉን፤ ማንም እንላለን።''

ምንም እንኳን ፒዬር የቤት ውስጥ ስራዎች ባለቤቱ ብቻ መስራት እንዳለባት ቢያስብም፤ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች ምግብ የማብሰልና ቤት የማጽዳት ስልጠና ሰጥተውታል።

''ትምህርት ቤት የተማርነውን ወደ ቤት ተመልሰን ተግባራዊ ለማድረግ እንሞክራለን።'' ይላል ፒዬር።

ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ቤት ሲመለሱ ፈተና ኦለባቸው። በቤት ውስጥ የሰሩትን ምግብ ደግመው እንዲሰሩ ይጠየቃሉ።

"አሁን ጣፋጭ ምግቦች መስራት ችያለው፤ የልጆቼንም ልብሰ የማጥበው እራሴ ነኝ። ጽዳቱንም ቢሆን ቀጥ አድርጌ ይዤዋለው።'' ሲል በደስታ ይናገራል ፒዬር።

Image copyright Elaine Jung

ነገር ግን እንዲህ ተለውጦ ቤቴ ቤቴ ማለቱ በብዙ ጓደኞቹ ዘንድ ነቀፌታንና ፌዝ አስከትሎበታል። በተለይም መጀመሪያ አካባቢ ነገሮች ሁሉ ከባድ እንደነበሩ ያስታውሳል።

'' ትክክለኛ ወንድ ምግብ አያበስልም'' ይሉት ነበር።

''ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ እንደውም ባለቤቴ የሆነ መድሃኒት ሳትሰጠው አይቀርም ብለው እስከማሰብ ደርሰው ነበር።''

በቤት ውስጥ ስራዎችን መስራት ከጀመረ ወዲህ፤ ከሌላ ጊዜው በተለየ ልጆቹ እሱን መቅረብ መጀመራቸውንና ባለቤቱ የሙዝ ንግድ መጀመሯን ይናገራል።

በዚህ ምክንያትም የቤተሰባቸው ገቢ መጨመሩንና ልጆቹ በአግባቡ መመገብ መጀመራቸውን በኩራት ይናገራል።

"ባለቤቴም ቢሆን እንደ ድሮው በቁጣ አትመልስልኝም። ቁጭ ብለን ተወያይተን በነገሮች ላይ እንወስናለን።''

"ማንም መብታችንን ሊሰጠን ስለማይችል፤ ሴቶች ማንንም ሳይጠብቁ በራሳቸው መታገል አለባቸው"

የተነጠቀ ልጅነት

ፍርሃትና ነጻነት

የፒዬር ባለቤት ሙሳብዪማና ዴልፊን ከዚህ በፊት ትንሽ ነጻነትና ብዙ ፍራቻ እንደነበረባት ታስታውሳለች።

''በህይወቴ ስራ ሰርቼ ገንዘብ ማግኘት እቻላለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። ምክንያቱም ስለ እንደዚህ አይነት ነገሮች ለማሰብ ጊዜውም አልነበረኝም። ሁሌም ቢሆን ቤት ውስጥ የሆነ ያላለቀ ስራ ይኖራል።''

Image copyright Elaine Jung

ዴልፊን ሁሌም ቢሆን ሌሊት 11 ሰአት በመነሳት ወደ ሙዝ ገበያው ስትሄድ፤ ፒዬር ደግሞ ቤት ውስጥ አራት ልጆቻቸውን ይንከባከባል።

''ደክሞኝ ከስራ ስገባ ቤቱ ንጹህ ሆኖ፣ ቆንጆ ምግብ ቀርቦ ይጠብቀኛል።'' ትላለች።

ሴቶችና ከሴቶች ጋር ተያይዘው የሚነሱ የተሳሳቱ ሃሳቦችን ለመቀየር አልሞ ደቡብ አሜሪካ ውስጥ የተቋቋመው ፕሮጀክቱ፤ ህጻናትን የመንከባከብና ሌሎች የቤት ውስጥ ስራዎችን ወንዶች 50 በመቶ ማከናወን ሲጀምሩ እውነትም እኩልነት ሰፍኗል ማለት ነው ብሎ ያምናል።

አስተባባሪዎቹ በሰሩት የዳሰሳ ጥናት መሰረት ባለፉት ሁለት ዓመታት ሩዋንዳ ውስጥ ምግብ ማብሰልና ህጻናትን ስለመንከባከብ ስልጠና የወሰዱ አባቶች ሚስቶቻቸውን የመደብደብና ሁሉንም ስራ እነሱ እንዲሰሩ የመጠበቅ አስተሳሰባቸው በእጅጉ ቀንሷል።

የፒዬርና የዴልፊን የተቀየረ አስተሳሰብ ለቤተሰባቸው ብቻ ሳይሆን ለመላ መንደሪቱ ትልቅ ትምህርት ሆኗል።

''በመኖሪያ መንደራችን የባልና የሚስት አለመስማማት ሲኖርም ሆነ ሌላ ግጭት ሲፈጠር ለማስታረቅ እኛ የምናቀርበው ሃሳብ ሁሌም ቢሆን ተቀባይነት ያገኛል።''

"ምክንያቱ ደግሞ እኛ በቤታችን ውስጥ ሰላማዊ ኑሮ ስለምንኖር ነው።''