"ጥፍር ሲነቅል ሕዝብን ያላማከረ፤ ጥፍር መንቀል ሕጋዊ አይደለም ስንለው ብሔሩ ውስጥ ለመደበቅ ይሞክራል" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው እየተካሄደ ስላለው ለውጥና በሚቀጥለው ዓመት ስለሚደረገው ምርጫ ውይይት አድርገዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባለፈው ሳምንት ባደረገው ጥሪ መሰረት በተካሄደው ውይይት በቀጣይ ፓርቲዎች ሊያደርገቸው በሚገቡ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል።

የውይይቱ ዋነኛ ትኩረት ቀጠይ ምርጫና እየተካሄደ ያለው ለውጥ ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው መንግሥት እያካሄደ ያለውን ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጨምረውም መንግሥታቸው ሕግን ለማስከበር እየወሰደ ያለው እርምጃ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ነው መባሉ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።

እየተከናወነ ያለው ተግባር የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈፀሙና በተደራጀ ሌብነት ላይ የተሰማሩትን ብቻ ለሕግ ማቅረብ ነው። በዚህም ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ተጠያቂ ስለሚደረጉ ከብሔር ጋር ማያያዘ ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀው፤ ጥፋት ሲሰሩ ህዝብን ሳያማክሩ ጥፋተኛ ነህ ሲባሉ ከብሔር ጋር ማያያዝ አደገኛ መሆኑን አስረድተዋል።

"ጥፍር ሲነቅል ሕዝብን ያላማከረ፤ ጥፍር መንቀል ሕጋዊ አይደለም ስንለው ብሔሩ ውስጥ ለመደበቅ ይሞክራል" በማለት ድረጊቶቹ በግለሰቦች የተፈፀሙ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት ከፓርቲዎች ጋር የሚካሄደው ውይይት በሦስት ደረጃዎች ተከፍሎ የሚካሄድ ነው። በዚህም የመጀመሪያው ደረጃ ውይይቱን ማስጀመሪያ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በምርጫ ጉዳይ ላይ ትኩረቱን ያደርጋል። ሦስተኛው ደግሞ ከምርጫው በኋላ በሚኖሩ ተግባራት ላይ ትኩረት እንሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዳሉት ቀጣዩ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ እንደሚሰራና ለዚህም በምርጫ ህግ፣ በምርጫ ቦርድ ስያሜ እና የምርጫ ቦርድ አቅም ዙሪያ አስፈላጊው ሥራ ይከናወናል ብለዋል።

የምርጫ አዋጅ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥነ ምግባር አዋጅ በጠቅላይ አቃቤ ህግ በኩል (በባለሞያዎች ተጠንቶ) ማሻሻያዎች እንደተረቀቀ ነገር ግን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊወያዩባቸው ስለሚገባ ለዚያ ሲባል ለፓርላማ እንዳልቀረቡ ተናግረዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ህጋዊ ሆነው እንዲሰሩ አመቺ የህግ ማዕቀፍ እንደሚዘጋጅ ጠቁመው በቀጣይ ምርጫ የማህበራዊ ድረ ገፆች በቀታዩ ምርጫ ላይ ፈተና ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመው ይህንንም ለመከላከል ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ሌላኛው የገለፁት ነገር ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ኦፊሴላዊ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆች እንደሚያስፈልጓቸው ነው። ይህም በስማቸው የሚለቀቁና የሚያጋጩ መልዕክቶችን ለመቆጣጠር እንደሚያስችል አስረድተዋል።

ሕገ መንግሥትን ስለማሻሻልና በተቋማት ግንባታ ዙሪያ የሚከናወኑ ተግባራት እንደሚኖሩ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሕገ መንግስት ማሻሻያ ለማድረግ መወያየት እንደሚያስፈልግና አከራካሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከምርጫ በኋላ ህዝቡ ውሳኔ እንዲሰጥ እንደሚደረግ ገልፀዋል።

ስለየምርጫ ጊዜ መራዘም በተመለከተ በተነሳ ሃሳብ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እንደተናገሩት፤ የምርጫው ጊዜ እንዲራዘም በይፋ የቀረበ ሃሳብ እንደሌለ ጠቅሰው፤ ነገር ግን ሀሳቡን ማንሳትና በመወያየት ውሳኔ ላይ መድረስ እንደሚቻል ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም ፓርቲዎች በቁጥር በርካታ ሆነው ከመቅረብ ይልቅ ተቀራርቦ በመስራት መዋሃድ ባይቻል እንኳን ግንባር በመፍጠር ተጠናክረው እንዲቀርቡ መክረው፤ መንግሥትም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል።

ፓርቲዎች ለቀጣዩ ምርጫ አስፈላጊውን ዝግጅት ከወዲሁ ማድረግ እንዳለባቸው ሲያመለክቱም "የሚቀደድ ፓስፖርት ካለ ቶሎ ቀደው" ለምርጫ እንዲዘጋጁም መክረዋል።