አውስትራሊያ፡- የማይሸጥ፤ የማይታረደው ግዙፉ በሬ

አብዛኛውን ጊዜ 'ኒከርስ' በሌሎች የቀንድ ከብቶች ተከቦ ይውላል፤ ይከተሉታልም Image copyright Geoff Pearson
አጭር የምስል መግለጫ አብዛኛውን ጊዜ 'ኒከርስ' በሌሎች የቀንድ ከብቶች ተከቦ ይውላል፤ ይከተሉታልም

በምዕራብ አውስትራሊያ የሚገኘው 'ኒከርስ' የተባለው በሬ ከከብት መንጋዎች ሁሉ የተለየ ነው።

ይህ የሰባት ዓመት ዕድሜ ያለው በሬ፤ 1400 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሲሆን 1ሜትር ከ94 ሴንቲ ሜትር ይረዝማል፤ በአገሪቱ ካሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቀንድ ከብቶችም በጣም ግዙፉ ነው።

ባለቤትነቱም የምዕራብ አውስትራሊያዊው ጆን ፒርሰን ነው።

"ፓስፖርት መስጠት አልተከለከለም" የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች ተቋም

ታንዛኒያ "ከምዕራቡ ይልቅ የቻይናን እርዳታ ትመርጣለች"

እውን እንጀራ ሱስ ያስይዛል?

ፒርሰን የቁም ከብቶችን ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ ድርጅት አለው፤ ይሁን እንጂ ይህንን ግዙፍ በሬውን ወደ ውጭ መላክም ሆነ ለምግብነት መሸጥ እንዳልቻለ ይናገራል።

ይህም የ'ኒከርስን' በሕይወት የመቆየት ዕድል ጨምሮለታል።

በከብቶቹ መካከል ሲንጎማለል ላየው በእርግጥም የሰማይ ስባሪ ያክላል፤ ማንም እርሱን ደፍሮ ወደ ቄራ የሚወስደው አልተገኘም። የቄራ ሰራተኞች በበኩላቸው በሬውን ማረድም ሆነ ለመበለት የማይቻል ነው ብለዋል።

በዚህም ምክንያት 'ዕድሜህ ይርዘም' የተባለው በሬ በደቡባዊ ግዛቷ ፐርዝ 136 ኪ.ሜ በምትርቀው ፕሪስቶን ሃይቅ አቅራቢያ እንደ ልቡ እየተንጎማለለ ይገኛል።

የክኒከርስ ባለቤት ፒርሰን ለአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መረጃ በሬውን የ12 ወር ጥጃ እያለ የገዙት ሲሆን እንዲህ ይገዝፋል ብለው አላሰቡም ነበር፤ ዓመት ዓመትን እየተካ ሲሄድ ግን ከዝርያዎቹ ሁሉ በቁመቱም በክብደቱም የተለየ ሆነ ብለዋል።

"ከሌሎቹ በጣም ንቁና ግዙፉ ነው" የሚሉት ፒርሰን የእርሱ ጓደኞች ግን ገና በለጋ ዕድሜያቸው የሰው እራት ሆነዋል ይላሉ። እርሱ ግን ድርብርብ ስጋው ያልከበደው ንቁና ቀልጣፋ በመሆኑ፤ እንዲሁም ማንንም አይጎዳም በሚል ለመሬቱ ግርማ ሞገስ ለዘመዶቹም ጋሻ መከታ ሆኖ እንዲቆይ እንደተውት ያስረዳሉ።

ፒርሰን እንደሚሉት በሬው አሁንም ዕድገቱን አላቆመም።

20 ሺህ የሚሆኑ ቀንድ ከብቶች ባለቤት የሆኑት ፒርሰን አብዛኞቹ እንስሳት 'ዳልቻ' እና ጥቁር ቡናማ ቀለም ያላቸው ሲሆን እርሱ ግን ጥቁርና ነጭ ቀለም አለው። በመካከላቸው ሲቆምም ግርማ ሞገስ እንዳላበሳቸው ይናገራሉ።

እስካሁን በቁመቱ በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ የሰፈረው የጣሊያኑ 'ቢሊኖ' ሲሆን 2.027 ቁመት አለው፤ ስሙ መዝገብ ላይ የሰፈረው ከ8 ዓመታት በፊት ነበር።

ግዙፉ በሬ ''ኒከርስ'' የሚለውን ስያሜ ከየት አገኘው?

''ልጅ ሆኖ ስንገዛው 'በራህማን' የተሰኘ ሌላ የበሬ አይነት ዘር ነበረን። ይህን በሬ በአጭሩ 'ብራ' ብለን እንጠራው ነበር [ብራ ማለት ጡት ማስያዣ ማለት ነው] ከዚያም ይህን ወይፈን 'ኒከርስ' ብለን ሰየምነው [ኒከርስ ማለት ከወገብ እስከ ጉልበት ድረስ የሚሸፍን የሴት ልጅ የውስጥ ልብስ ማለት ነው] ከዛ በቃ ብራ እና ኒከርስ ኖረን።'' ፒረሰን ያስረዳሉ።