"ሥልጣን ለደም ግፊት አጋልጦኛል" ኃይሌ ገብረሥላሴ

ኃይሌ ገብረሥላሴ

የቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ባልደረባ ባለፈው ሳምንት ኃይሌ ገብረሥላሴን በአዲስ አበባ አግኝታው ነበር።

ከመነሻውም ግሩም ጥያቄ ነበር ያነሳችለት።

አንተ የዓለም ሪከርድ ስትሰብር፣ የኦሎምፒክ ወርቆችን ስታፍስ ነው የኖርከው። ዓለም የሚያውቅህም በጽናትህ ነው። ስናውቅህ በ"ይቻላል" መርህ ነው። ፍጹም ተስፋ የምትቆርጥ ሰው አልነበርክም። ለምን ሥልጣንህን ለቀቅክ? እንዴትስ እጅ ሰጠህ?

በታላቁ ሩጫ ላይ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች ላይ የአበረታች መድኃኒት ምርመራ ሊካሄድ ነው

እርግጥ ነው ኃይሌ ምላሽ ሰጥቷታል። ምላሹ ግን የሁልጊዜው አልነበረም። እንደሁልጊዜው አልተፍነከነከም። የሚናፈቀው ያ ሳቁ እምብዛምም ነበር።

"እንዲያውም ሥልጣን ለደም ግፊት አጋልጦኛል" ሲል እግረ መንገዱን ያልተጠበቀ ምላሽን ሰጥቷታል፤ ለቢቢሲ ስፖርት አካፍሪካ ወኪል።

'...ከሁለት ዓመት በፊት ወደዚህ ሥልጣን ስመጣ ብዙ ፈተና ነበረው። አትሌቶችን ማርካትና ጥያዎቻቸውን መመለስ ነበር ህልሜ። ያንን ለማሳካት ያለኝን ነገር ሁሉ ለዚሁ ሥራ መስጠት ነበረብኝ። ጊዜዬን ገንዘቤን ጉልበቴን ዕውቀቴን...የሚገርምሽ በቤተሰባችን ደም ግፊት ያለበት ሰው የለም። አሁን እኔ ብቻ ነኝ ግፊት የያዘኝ..."

ታሪክ እየቀየሩ ያሉት ሴቶች

በቃለ ምልልሱ መሐል እግረ መንገድ የተገለጸው ይህ የኃይሌ ገብረሥላሴ የጤና እክል በራሱ ለአድናቂዎቹ አስደንጋጭ ዜና መሆኑ እንደተጠበቀ ኾኖ ለመሆኑ ይህን ያህል ኃይሌን ሊያስመርር የቻለው ጉዳይ ምንድነው?

Image copyright JAVIER SORIANO

"አትሌቶች ቅሬታ ነበራቸው። ጥቂት ቢሆኑም የማይታወቁ ቢሆኑም በኔ ደስተኛ ያሆኑ አትሌቶች ሰልፍ አደረጉ። ዝነኛ ላይሆኑ ይችላሉ'ኮ። ብዙ ላይሆኑ ይችላሉ። ግን ተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ። በቃ በኔ ደስተኞች አልነበሩም። እንዴ! እነሱን ማስደሰት ካልቻልኩ ለምን ብዬ አመራር ላይ እቆያለሁ? ለሌሎች ድል መስጠት ነበረብኝ።..."

ኃይሌ የርሱን ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በገዛ ፈቃድ መነሳት አስታኮ በአፍሪካ ሥልጣንንን ርስት ማድረግ ማብቃት እንዳለበትም እግረ መንገዱን ምክር ቢጤ ጣል አድርጎ ነበር።

"እኛ አፍሪካዊያን ለተቀረው ምሳሌ መሆን አለብን። ልጣን ላይ ሙጭጭ ማለት አያስፈልግም። የምንመራው ሕዝብ ካልፈለገን መልቀቅ ነው። ሕዝብ ካልወደደን ለምን ጎትቶ እስኪጥለን እንቆያለን። ሥልጣን እንደ አትሌቲክስ ነው። ካላሸነፍክ ለሚያሸንፈው አትሌት መልቀቅ ይኖርብሃል። በቃ..."

የኃይሌ ወደ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መምጣት ብዙዎች "ይንሸራተት ይዟል" ለሚሉት የአትሌቲክስ ውጤታችን እንደ ሁነኛ ማስፈንጠሪያ ቆጥረውት ነበር። 'አሁን ገና ሞያና ሞያተኛ' ተገናኙ ያሉም ብዙ ነበሩ። ጉዞው በሁለት ዓመት ይገታል ያለ ግን አልነበረም።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን ወደ ፅዮን ውሰዱን ተማፅኖ

የቢቢሲ አፍሪካ የስፖርት ባልደረባ የመጨረሻ ጥያቄ ያነሳችለት የማበረታቻ መድኃኒቶች በአፍሪካ አትሌቶች ዘንድ የመዘውተሩን ጉዳይ ነበር።

"በአትሌቲክስ ሐቀኛ መሆን ቁልፍ ነገር ነው።" ሲል ምላሽ መስጠት የጀመረው ኃይሌ በማበረታቻ ታግዞ ዘላቂ ውጤት ማምጣት እንደማይቻል አጽእኖት ሰጥቶ ተናግሯል።

"...ዓለም አቀፍ አትሌት ለመሆን በቅድሚያ ሐቀኛና ታማኝ መሆን የግድ ነው። ሐቀኝነት ለድል ያበቃል።" ሲል ከተናገረ በኋላ በተፈጥሮ መታደላችን ምን ያህል ለውጤችን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ያብራራል።

"...ረ ለመሆኑ ኢትዯጵያና ኬንያ ለምንድነው አበረታች መድኃኒት የሚፈልጉት? ንገሪኝ! እኛ እኮ ፈጣሪ የሰጠን ማረታቻ አለ። እሱን አንጠቀምም? ተመልከችው እስኪ ተራራውን። ተመልከቺው አየሩን። ይህ የኛ የተፈጥሮ 'ዶፒንግ' ነው።"

ማበረታቻ የሚወስዱ አትሌቶች ለጊዜው ገንዘብ ማግኘት ቢችሉ እንኳ ያገኙት ገንዘብ በረከት እንደማይኖረውም ኃይሌ ጨምሮ ተናግሯል። "ይዟቸው ነው የሚጠፋው።" ይላል።

የስኬታማነት ተምሳሌቱ ኃይሌ ለቢቢሲ አፍሪካ ስፖርት ባልደረባ የሕይወት ፍልስፍናውን በገደምዳሜ አጫውቷት ነበር፤ እግረ መንገዱን።

"ሕይወት አጭር ናት፤"ሀብትና ንብረት ይዘን አንቀበርም። ባዶ ኪሳችንን ነው የመጣነው ባዶ ኪሳችንን ነው የምንሞትው። ስትቀበሪ ሳንቲም ሬሳ ሳጥንሽ ውስጥ የሚያጭቅልሽ አይኖርም። ባዶ ገላን ይዘን ነው የመጣነው ባዶ ገላችንን እንለመሳለን። ይኸው ነው።" ሲል አጠር ያለ አስተያየቱን ቋጭቷል