ኢትዮጵያ በዲፕሎማቶቿ ላይ ሽግሽግና ለውጥ ልታደርግ ነው

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም

ኢትዮጵያ በተለያዩ የዓለም ሃገራት ያሉ ግማሽ ያህል ዲፕሎማቶቿን ቀደም ሲል ከነበሩባቸው የዲፕሎማቲክ መቀመጫዎች ወደ ሌላ ቦታ እንደሚዘዋወሩና አዲስ ከሚሾሙ አምባሳደሮች መካከልም ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች እንደሚካተቱ ተጠቆመ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም እንደተናገሩት ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በሃምሳ ዘጠኝ ኤምባሲ እና ቆንስላ ፅህፈት ቤቶች የሠራተኛ ድልድል አጠናቅቆ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል።

የአምባሳደሮች ሹመት በቅርቡ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በመስሪያ ቤቱ ካገለገሉ ዲፕሎማቶች በተጨማሪ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦችንም ያካተት እንዲሆን ይደረጋል በማለት "ምደባው ዕውቀትን እና ሙያዊ ብቃትን ብቻ መሰረት ያደረገ ነው" ብለዋል።

"ፓስፖርት መስጠት አልተከለከለም" የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች ተቋም

". . . ጥፍር መንቀል ሕጋዊ አይደለም ስንለው ብሔሩ ውስጥ ለመደበቅ ይሞክራል" ጠ/ሚ ዐብይ

የአምባሳደሮቹ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰየሙ ሲሆን እነማን እንደሆኑና ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ ቃል አቀባዩ ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።

በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ በየኤምባሲው እና የቆንስላ ፅህፈት ቤቱ ካሏት 412 ዲፕሎማቶች ግማሽ ያህሉ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ ይደረጋል ብለዋል ቃል አቀባዩ።

"ሠራተኞች አዲሱን ምደባቸውን እንዲያውቁ ተደርጓል፤ አዲስ መዋቅር ደግሞ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ሥራ ላይ ውሏል" ያሉት አቶ መለስ በዚሁ መዋቅር መሰረት አምስት ቋሚ ተጠሪዎች ሥራ ላይ መሰየማቸውን ገልፀዋል።

"የአሁኑ ድልድልና የባለፈው ሳምንት የመዋቅር ማሻሻያ መስሪያ ቤቱን ከወትሮው በተለየ ከፍ ያለ እርምጃ ነው ብለን እናስባለን" ሲሉም አክለው ተናግረዋል።

ለዘመነ ሉላዊነት ከሚጠብቅበት ኃላፊነት አንፃር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ራሱን መፈተሽ እንዳለበት መገንዘቡን ያስረዱት አቶ መለስ የሚገባውን ሠራተኛ ከተገቢው የሥራ ድርሻ ጋር የማገናኘት ዓላማን ያነገበ ሽግሽግ ማደረጉን ገልፀዋል።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር ተዋሃዱ

ስለኤች አይ ቪ /ኤድስ የሚነገሩ 8 የተሳሳቱ አመለካከቶች

"የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአዲስ የማሻሻያ እርምጃ ሩጫ ውስጥ ይገኛል" ያሉት ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሃገራት ጋር "የዜሮ ውጥረት ፖሊሲን" እንደምትከተል አትተው ይህን ታሳቢ ባደረገ አኳኋን የካበተ ልምድ ያላቸው ዲፕሎማቶች በጎረቤት አገራት እንደሚመደቡ ጠቁመዋል።

"ተደራድሮ የሚያሸንፍ፣ ተናግሮ የሚያሳምን፣ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የልማት ጥረት ገንዘብ ማምጣት የሚችል ዲፕሎማት ይፈለጋል" ብለዋል።

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ፣ ጥሩ ወዳጅ ማፍራት እና በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በኤምባሲዎች እና በቆንስላ ፅህፈት ቤቶች የትኩረት አቅጣጫን ለመወሰን ያገለገሉ መስፈርቶች ናቸውም ብለዋል።

ይህም በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን አንደሚታለብ ላም ከማየት አባዜ መውጣት እንደሚያስፈልግም አክለው ተናግረዋል።

በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር ከ2000 በላይ በተለያዩ አገራት እስር ቤት ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን የማስመጣት ተግባርን በማከናወን ላይ እንደሆኑ አቶ መለስ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያኑ ይመለሱባቸዋል የተባሉት አገራት የመን፣ ታንዛንኒያ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ሊቢያ ናቸው።

እንደቃል አቀባዩ ገለፃ ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ 205 ኢትዮጵያዊያን ከየመን እንዲመለሱ ተደርጓል።