ኢትዮጵያ፡ ሕንዳውያን የግንባታ ሠራተኞች ከታገቱ ቀናት ተቆጠሩ

የሕንድ ሰንደቅ ዓላማ Image copyright Getty Images

የሃገረ ሕንድ የሆነው አይኤል እና ኤፍኤስ (IL&FS) ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት ዓመታት የተለያዩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ሲያካሄድ ቆይቷል።

በቅርቡም ከነቀምት-ጊዳ እና ከአጋምሳ-ቡሬ ያሉ የመንገድ ግንባታዎችን ሲያካሂድ ነበር። ይሁን እንጂ ኩባንያው ባጋጠመው የፋይናንስ ቀውስ የመንገድ ግንባታ ስራውን ማከናወን ተስኖታል።

ይህም ብቻ አይደለም፤ ለሰራተኞች ደሞዝ፣ ለተቋራጮችና ለአቅራቢዎች የሚከፍለው ገንዘብ አጥሮታል።

ያነጋገርናቸው ተቋራጮች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው ክፍያው እንዲፈጸምላቸው ቢፈረድላቸውም ኩባንያው ግን ክፍያዎችን መፈጸም ተስኖታል።

ኢትዮጵያ በዲፕሎማቶቿ ላይ ሽግሽግና ለውጥ ልታደርግ ነው

"ፓስፖርት መስጠት አልተከለከለም" የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች ተቋም

አቶ ሃብታሙ ካላዩ ከዚህ ኩባንያ ጋር ለሰራተኞች መኖሪያ የሚሆን ተገጣጣሚ ቤቶችን ለመገንባት ከሁለት ዓመታት በፊት ውል ወስዶ ነበር። በውሉ መሰረት መፈጸም የነበረበት 220 ሺህ ብር ክፍያ ስላልተፈጸመላቸው ሥራውን ለማቋረጥ መገደዳቸውን ይናገራሉ።

አቶ ሃብታሙ ክፍያው እንዲፈጸምላቸው ፍርድ ቤት ቢወስንላቸውም ኩባንያው ግን የተጠየቀውን ክፍያ መፈጸም አልቻለም ይላሉ።

ኩባንያው ለሌሎች ተቋራጮች፣ የመኪና እና የተለያዩ ማሽነሪዎች አከራዮችም ያልተከፈለ ውዝፍ እዳ እንዳለበት አቶ ሃብታሙ ነግረውናል።

ደሞዛቸው ከሶስት እስከ አምስት ወራት የዘገየባቸው የነቀምት፣ ወሊሶ እና ቡሬ ሳይት ሰራተኞች ግን ሕንዳዊ የሆኑ የኩባንያውን ሰራተኞች በማገት ክፍያ እንዲፈጸምላቸው ጠይቀዋል።

በዚህም የተነሳ በቡሬ ሳይት 4፣ ወሊሶ 2 እንዲሁም ነቀምት ላይ 1 በድምሩ 7 ሕንዳውያን ላለፉት ስድስት ቀናት ታግተው ይገኛሉ።

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውንና የሚገኙበትን ሳይት የማንጠቅሰው አንድ ታጋች ''ኩባንያችን ባጋጠመው የፋይናንስ ችግር ምክንያት ለሰራተኞች ደሞዝ መክፈል አልቻለም፤ ላለፉት ስድስት ቀናት ከመጠለያ ጣቢያ እንዳንወጣ በአካባቢው ሰዎች ታግተናል፤ የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት እና የመጠጥ ውሃ እጥረት ችግር አጋጥሞናል። ያለንበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው'' ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ ያስረዳሉ።

ይህ ታጋች እንደሚሉት ከሆነ ለሰራተኞች ለወራት ያክል ያልተከፈለ ደሞዝ፣ ለተቋራጮች እና አቅራቢዎች መፈጸም የነበረበት ክፍያ አለ። በአጠቃላይ ኩባንያው ወደ 60 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ክፍያ መፈጸም አለበት ይላሉ።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር ተዋሃዱ

''የአንድ ቤተሰብ አባላት ግድያ'' በቤኒሻንጉል ክልሏ ያሶ ከተማ

''ሰራተኞቹ ያልተረዱት ነገር፤ ፤ እኛም ከ3-5 ወራት ድረስ ደሞዝ ያልተከፈለን እንደነርሱ ቅጥረኞች ነን፤ የሚለየን ነገር ቢኖር እኛ ሕንዳውያን እነርሱ ደግሞ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ነው።'' ይላሉ ታጋቹ።

እኝህ ግለሰብ እንደሚሉት ለሕንድ መንግሥት እና በኢትዮጵያ የሕንድ ኤምባሲ ለጉዳዩ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል።

''ኤምባሲው መፍትሄ እንደሚሰጠን ቃል ቢገባልንም እስካሁን መልስ አላገኘንም፤ ምላሻቸውን እየተጠባበቅን ነው'' ሲሉ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የህዝብ ግነኙነት ኃላፊው አቶ ሳምሶን ወንድሙ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የሚጠበቅበትን ክፍያ ሁሉ መፈጸሙን አስታውሰው፤ የኩባንያው ሰራተኞች የታገቱት ለሰራተኞቹ ክፍያ መፈጸም ባለመቻላቸው መሆኑን ይናገራሉ።

''ለሰራተኞቹ ክፍያ መፈጸም እንዳለበት እናምናለን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሕንዶቹ በእንዲህ ዓይነት አያያዝ መቆየት እንደሌለባቸው እንረዳለን፤ እኛም ችግሩን ለመፍታት ከሕንድ ኤምባሲ፣ አዲስ አበባ ከሚገኙ የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች እና ከሚመለከተው አካል ጋር በጉዳዩ ላይ እየመከርን ነው።'' ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለመጠየቅ በኢትዮጵያ የሕንድ ኤምባሲን ለማነጋገር ብንሞክርም አልተሳካልንም።

ተያያዥ ርዕሶች