በአዲስ አበባ ዕድሜያቸው ከ15-24 የሚሆኑ አፍላ ወጣቶች በከፍተኛ መጠን በኤች አይቪ እየተያዙ ነው

የጸረ ኤች አይ ቪ ኤድስ ሪቫን Image copyright FAROOQ NAEEM

በአዲስ አበባ የኤች አይቪ የስርጭት መጠን እየጨመረ እንደመጣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠያ ፅ/ቤት ኃላፊ ሲስተር ብርዛፍ ገብሩ ለቢቢሲ ገለፁ። ይህም የሆነው የመከላከል ስራው ላይ መዘናጋት በመታየቱ እንደሆነ አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ የስርጭት መጠኑ 3.4 በመቶ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊዋ ዛሬም በከፍተኛ ሁኔታ በቫይረሱ ከተያዙ መካከል ሴቶች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ ብለዋል።

በከተማዋ ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኙ ግለሰቦች 109 ሺህ መሆናቸውን ያስታወሱት ሲስተር ብርዛፍ ከእነዚህ መካከል ዕድሜያቸው ከ15-24 የሚሆን ወጣቶች በከፍተኛ ቁጥር በቫይረሱ መያዛቸውን ጥናቶች እንደሚያሳዩ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ 76 በመቶ የሚሆኑት ወጣት ሴቶች ስለ ኤችአይቪ እውቀት የላቸውም ተባለ

ሳይንቲስቱ መንትዮች ኤች አይ ቪ እንዳይዛቸው ዘረ መላቸውን አስተካከለ

የማትተነፍሰው ከተማ: አዲስ አበባ

በዘውዲቱ ሆስፒታል የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አስቴር ሸዋአማረም በኃላፊዋ ሀሳብ ይስማማሉ። ለኤች አይቪ ምርመራ ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል ከሚሄዱ መካከል እድሜያቸው ከ15 እስከ 24 የሆነ አፍላ ወጣቶች መካከል የኤች አይቪ ቁጥሩ ከፍ ብሎ አንደሚታይ ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠያ ፅ/ቤት ኃላፊ ሲስተር ብርዛፍ እንደሚሉት አዲስ አበባ ከጋምቤላ ቀጥሎ በከፍተኛ ሁኔታ የኤች አይቪ ስርጭት የሚታይባት ከተማ ናት።

በጋምቤላ የኤች አይቪ የስርጭት መጠን 4.8 መሆኑን አስታውሰው አንዳንድ የሀገሪቱ ከተሞች ላይም የስርጭት መጠኑ ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል።

ለዶ/ር አስቴር በከተማዋ በአፍላ ወጣቶች ያለው የኤች አይቪ የስርጭት መጠን ከፍ ማለት ምክንያት መዘናጋት ነው። ሲስተር ብርዛፍም ከዚህ የተለየ ሀሳብ የላቸውም፤ መንግስትና አጋር ድርጅቶች ኤች አይቪ ላይ የሚሰጡት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች መቀዛቀዛቸው በአዲሱ ትውልድ የስርጭት ምጣኔው ከፍ እንዲል ምክንያት መሆኑን አበክረው ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም ወደ ህዝቡ ወጥተው ስለ ኤች አይቪ የሚያስተምሩ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ግለሰቦች ዛሬ አለመኖራቸውም በአሁኑ ወቅት ለተፈጠረው መዘናጋት አስተዋፆ እንዳለው ሲስተር ብርዛፍ ያምናሉ።

ስለኤች አይ ቪ /ኤድስ የሚነገሩ 8 የተሳሳቱ አመለካከቶች

በአሁኑ ወቅትም ከእነዚህ ግለሰቦች ጋር ለመስራት እቅድ መኖሩን አስረድተው አሁን ከተፈጠረው መዘናጋት የተነሳ አድልኦና መገለል እንደ አዲስ እያገረሸ ስለሆነ የከተማው አስተዳደር መደገፍ በሚገባቸው በኩል ደግፎ እንዲያስተምሩ እንዲያደረግ እንደሚያመቻቹ ተናግረዋል።

የኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠያ ፅ/ቤት ኃላፊዋ እንደሚሉት በከተማዋ ያለውን የኤች አይቪ የስርጭት መጠን አሳሳቢ የሚያደርገው በአፍላ ወጣቶች መካከል ያለው የስርጭት መጠን ከፍተኛ መሆኑ ነው። ለዚህም ኃላፊዋ እንደምክንያትነት የጠቀሱት ከስራ አጥነት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ነው።

"ስራ አጥነት ለኤች አይቪ የሚያጋልጡ ስፍራዎች እንዲውሉ ገፊ ምክንያት ነው" የሚሉት ሲስተር ብርዛፍ በከተማዋ ያሉ የኢንዱስትሪና የሆቴሎች መስፋፋት ሌላው እንደምክንያት ያነሱት ነው።

በከተማዋ የመጤ ባህሎች መስፋፋትም እንደሚታይ የገለፁት ሲስተር ብርዛፍ የራቁት ዳንስ ቤት፣ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት፣ ጫት፣ ሺሻና ቡና ቤቶች መበራከታቸው ለኤች አይቪ መስፋፋት አስተዋፅኦ ማድረጉን ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየው የኮንስትራክሽን ስራዎች ላይ ለመሰማራት ከተለያዩ ከተሞች የሚመጡ ወጣቶች ቁጥር ከፍ ማለትም የስርጭቱ መጠን ከፍ እንዲል እንዳደረገው አብራርተዋል።

ፅህፈት ቤታቸው በከተማዋ ለኤች አይቪ ተጋላጭ ብሎ የለያቸውን የከተማዋ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሲዘረዝሩ በትምህርት ቤትም ሆነ ውጭ ያሉ ወጣቶች፣ የቀን ሰራተኞች፣ የከባድ መኪና የረዥም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ በወህኒ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች፣ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ግለሰቦች፣ እና በቅርቡ በተደረጉ ጥናቶች እንደታየው ደግሞ ባሎቻቸውን በፈቱ ሴቶች የስርጭት ምጣኔው ከፍ ያለ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶቹ በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች የትምህርት ስራውን ሊያውኩና ወጣቶቹን ለኤች አይቪ ሊያጋልጡ የሚችሉ መዝናኛዎችን ከትምህርት ቤት መራቅ አለባቸው የሚል አቋም ይዞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመስራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል።

የአለም ጤና ድርጅት እኤአ በ2030 አዲስ በቫይረሱ የሚያዝ ግለሰብ መኖር የለበትም የሚል ራዕይ አስቀምጧል።

በኢትዮጵያ የኤች አይቪ የስርጭት መጠኑ 0.9 በመቶ ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ