የኦሮሚያ ተቃውሞዎች ምን ይጠቁማሉ?

በኦሮሚያ ክልል ያለው ተቃውሞ

ላለፉት ጥቂት ቀናት ቡራዩ፣ ሰበታና ሱሉልታ ባሉ የአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ከተሞች ህዝቡ ድምፁን ለማሰማት አደባባይ ወጥቷል። እንደ ወለጋና ነቀምት ያሉ የምዕራብ ኦሮሚያ ከተሞችም ተመሳሳይ ሰልፎችን ተስናግደዋል።

ምንም እንኳ እየተካሄዱ ያሉት ሰላማዊ ሰልፎች ናቸው ቢባልም የሰዎች ህይወት ጠፍቷል አካል ጉዳትም ደርሷል።

ህዝቡን ገፍቶ አደባባይ ያወጣው ባለፈው ሳምንት በቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ ክልል ድንበር አቅራቢያ ላይ የኦሮሚያ ፖሊሶች መገደል ነበር።

ስለዚህም ግድያውን ማውገዝ የመጀመሪያው የሰልፉ አላማ ሲሆን የኦሮሞ ግድያና መፈናቀል ይቁም፤ የኦሮሞ ህዝብ ባለፉት ሶስትና አራት አመታት የታገለው የኦሮሞን ችግር ለመፍታት እንጂ ኦሮሞን ስልጣን ላይ ለማውጣት አይደለም የሚል ሃሳብም በሰልፎቹ ተንፀባርቋል።

ሶሪያውያን ስደተኞች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች

''የአንድ ቤተሰብ አባላት ግድያ'' በቤኒሻንጉል ክልሏ ያሶ ከተማ

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ህዝቡን አደባባይ ያወጣው መንግስት የቤት ስራውን አለመስራት ነው ይላሉ።

መንግሥት የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ ባለመቻሉም ታጣቂዎች ሰላማዊ ሰዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው እያፈናቀሉ እንደሆነ ይናገራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት መንግሥት የታጣቂዎችን ማንነት እያወቀ ምንም ባለማድረጉ፤ የዜጎቹን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታውን ባለመወጣቱ ህዝቡ እሮሮውን ለማሰማት አደባባይ ለመውጣት ተገዷል።

መንግሥት ህዝቡን ማረጋጋት አለመቻሉ በአቅም ማነስ ነው ብለው አያምኑም። ይልቁንም ከመንግስት ቸልተኝነት ጀርባ ያለው ነገር ፖለቲካዊ ስሌት ሳይሆን እንደማይቀር ጥርጣሬ አላቸው።

"የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ያቃተው መንግስት አለ ሊባል አይችልም" ይላሉ አቶ ሙላቱ።

እሳቸው እንደሚሉት በአጠቃላይ የኦሮሚያ ህዝብም እያለ ያለው መንግስት ሊጠብቀኝ አልቻለም ነው።

"ማንም ታጣቂና ጉልበተኛ ተነስቶ ሌላውን ከቤቱ ሲያፈናቅል፣ ንብረቱን ሲያቃጥልና ሲያወድም ይህን ማን እያደረገ እንደሆነ መንግሥት ያውቃል። መከላከል ይቻል የነበረ ቢሆንም መንግሥት ይህንንም እያደረገ አይደለም" ይላሉ።

በተመሳሳይ 'አክቲቪስት' ለሚ ቤኛ የኦሮሚያ ተቃውሞ ሁለት ነገሮችን ማዕከል ያደረገ ነው ይላል።

ሰላማዊ ሰልፎቹ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል ባለፉት ጥቂት ወራት በግጭት በመቶ ሺ ለሚቆጠር ህዝብ በመፈናቀሉ፤ የ100 ሰዎች ህይወት በመቀጠፉና ከቀናት በፊትም የኦሮሚያ ፖሊሶች በመገደላቸው መንግሥት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቁ እንደሆኑ ይናገራል።

ስለዚህ የሰልፈኞቹ ዋናኛ ጥያቄው መፈናቀልና ግድያ ይቁም የሚል እንደሆነ ያስረዳል።

የኦሮሚያው ተቃውሞ ለውጡና የለውጡ መሪዎች ላይም ስጋት ይጋርጣል የሚል አስተያየት ያላቸው ቢኖሩም ለሚ ግን በዚህ አይስማም።

ነገሩ ለውጡን መቃወም፤ የለውጡ መሪዎችን አለመቀበልም እንዳልሆነ ያስረዳል።

ለውጡ ባለፉት ሶስትና አራት አመታት የኦሮሞ ወጣት ወይም ቄሮ ብዙ መስዋዕትነት የከፈለበት ከመሆኑ አንፃር ኦሮሞ ዘብ ቆሞ ከምንም በላይ የሚጠብቀው እንደሆነ ለሚ ያስረግጣል።

ሀገሪቷ የሽግግር ጊዜ ላይ በመሆኗ ለነገሮች ጊዜ ሊሰጥ ይገባል የሚሉ የመኖራቸውን ያህል እየታዩ ያሉ ችግሮች ለውጡን ችግር ውስጥ ሊከቱት ብሎም ሊቀለብሱ የሚችሉ እንደሆኑ ስጋት ያላቸውም ጥቂት አይደሉም።

መንግሥት ችግሩን እየፈጠሩ ያሉት ኢህአዴግ ውስጥ ለውጡን የማይደግፉ አካላት ናቸው የሚል ምክንያት ቢያቀርብም ሊተኮርበት የሚገባው ነገር አገር እየመራን ያለ አቅምና ስልጣን ያለው መንግሥት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ያቃተው መሆኑ እንደሆነ አቶ ሙላቱ ተናግረዋል።

የኢህአዴግ መንግሥት በህዝቡ ዘንድ በተለይም በኦሮሚያ ተቀባይነት አለመኖሩ ጋር ተያይዞ ኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የኦሮሚያን ጥያቄ የሚመልስ ነው ተብሎ መታየቱ ስህተት እንደሆነ ይናገራሉ።

"የኦሮሞ ብሔር ያላቸው ግለሰቦች ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ጨምሮ የተለያዩ የፌደራል ስርዓቱን ቦታ ቢይዙም የኦሮሞን ጥያቄ መመለስ ካልተቻለ ትርጉም የለውም። ካሁን በፊት ኦሮሞ የሌለበት ስልጣን በኢትዮጵያ የመንግሥት ታሪክ ውስጥ የለም" በማለት የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄው ስልጣን እንዳልሆነ ይናገራሉ።

የኦሮሞ ህዝብ በአሁኑ ሰዓት እየጠየቃቸው ያሉት ጥያቄዎች ግድያና መፈናቀል ይቁም፤ መረጋጋት ይምጣ የሚል እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሙላቱ ይህ ሲሆን ብቻ ነው ከዚህ በፊት በኦሮሞ ህዝብ ላይ የደረሰው ግፍና በደል መሻር የሚችለውም ይላሉ።

ከዚህ በፊት የኦሮሞ ህዝብ ያነሳቸው የፖለቲከኞች መፈታትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማንሳት ከፊል ጥያቄዎች ቢመለሱም አሁንም በአካባቢው ያለው ወታደር ወደ ጦር ሰፈራቸው እንዲመለሱና ህዝብን የገደሉ ሰዎች ወደ ፍርድ የሚቀርቡበት ስርዓት እንዲኖር ዋነኛ ጥያቄያቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

እንደ መፍትሔ የሚያቀርቡትም መንግሥት ብቻውን ሳይሆን የተቃዋሚ ፖርቲዎችን ባሳተፈ መልኩ ህዝቡ የሚቃወማቸውን አመራሮች በማንሳት መረጋጋትን መፍጠር እንደሚቻል ነው።

የኢህአዴግ መንግሥት ብቻውን ማረጋጋት እንደማይችል አጥብቀው እንደሚያምኑ የሚናገሩት አቶ ሙላቱ ለመንግሥት አስተያየታቸውን ቢለግሱም ጥያቄያቸው ጆሮ ዳባ ልበስ እንደተባለም ይናገራሉ።

ለህዝባዊ ጥያቄዎች አፈሙዝን እንደምርጫ መጠቀም ሊያቆም ይገባል የሚሉት አቶ ሙላቱ ዲሞክራሲያዊ የሆኑ ተቋማትን በመገንባት፣ አፋኝ የሚባሉ ህጎችን በማስተካከልና የኦሮሞ ማህበረሰብ የሚያምንባቸውን የገዳ አመራሮችን ማሳተፍ ይገባል ይላሉ።

ለሚ በበኩሉ ለዓመታት የተከማቸ ችግር ከመሆኑ አንፃር በአንድ ጊዜ ይፈታል ብሎ የማያስብ ቢሆን ጊዜ የማይሰጡ ችግሮችን መፈናቀልና ግድያ መንግሥት በአፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጥ እንደሚገባ ይጠቁማል።

ከዚህም በተጨማሪ በድንበር አካባቢ የፀጥታ ኃይልን ማሰማራትና ኃላፊነት ሊወስዱ የሚገባቸውን አካላት ወደ ፍትህ ማቅረብ እንደሆነ ይናገራል።

የመንግስት ህግና ስርዓትን በአፋጣኝ ማስከበር ለችግሩ መፍትሄ እንደሆነ አቶ ሙላቱና ለሚ ይገልፃሉ።

ተያያዥ ርዕሶች