የሃምዛ ሃሚድ ፈጠራ የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነቱ ሊጠበቅለት ነው

ሃምዛ ሃሚድ በውድድሩ ጊዜ አሸናፊ በሆነበት ጊዜ የተነሳው ፎቶ Image copyright Girma Worku

ገና የ3ኛ እና የ4ኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ጊዜ በፈጠራ ስራዎች ቀልቡ መሳብ እንደጀመረና ከኤሌክትሪክ የተገናኙ ነገሮችን መስራት ያስደስተው እንደነበር ያስታውሳል - የ18 ዓመት ወጣቱ ሃምዛ ሃሚድ።

ሃምዛ በፈጠራ ስራው ብቻ ሳይሆን በቀለም ትምህርቱም ጥሩ ውጤት ከሚያስመዘግቡ ተማሪዎች መካከል አንዱ ነው፤ ፊዚክስና ሒሳብም አብዝቶ የሚወዳቸው የትምህርት ዓይነቶች ናቸው።

ወሲባዊ ትንኮሳን የሚከላከል ካፖርት ተፈለሰፈ

ኮሌራን የሚቆጣጠር ኮምፕዩተር ተሰራ

የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ አስተማሪያቸው የፈጠራ ስራ የሰራ ይበረታታል ሲሉ ማስታወቂያ ያስተላልፋሉ።

ስራውን ለማሳየት ዕድሉን ለመጠቀም የፈለገው ሃምዛ የትራፊክ መቆጣጠሪያ መብራት ሰራ፤ ነገር ግን ስራው የመጀመሪያው በመሆኑ በራስ መተማመን አልሰጠውም፤ እየፈራ እየተባ ፈጠራውን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር በተገኙበት አቀረበ።

ያኔ ታዲያ ፊቱን በደስታ ብርሃን ያፈካ፤ ያልጠበቀውን ምላሽ አገኘ፤ በስራው ከመደነቃቸው የተነሳም ተማሪዎች በተሰበሰቡበት የአንድ 'ቢክ' እስክርቢቶ ሽልማት ተበረከተለት። ደስታው ወደር አልነበረውም፤ የልጅነት ልቡ ዳንኪራ ረገጠች።

የትራፊክ መብራቱ (ፈጠራው) ሰዎች የተሽከርካሪ አደጋ እንዳይገጥማቸው የሚያስተምር ቅርፅ (ሞዴል) ነበረ፤ እርሱ እንደሚለው ከዚያ በኋላ ድፍረትንም ድልንም ደጋግሞ መቀዳጀት ጀመረ።

የ4ኛ ክፍል ተማሪ እያለ በአስተማሪው ድጋፍ ራዲዮ ላይ የሚገጠም ድምጽ ማጉያ (ስፒከር) ሰርቶ በመወዳደር የሁለተኝነት ደረጃን አግኝቷል።

ሃምዛ 20 የሚሆኑ የፈጠራ ስራዎችን በተለያየ ጊዜ አቅርቧል። የሻይ ማሽን፣ ጤፍን በመስመር ለመዝራት የሚያስችል መሳሪያ እንዲሁም ሻማ ከቀለጠ በኋላ እንደገና ተመልሶ አገልግሎት የሚያስገኝ መሳሪያ ሰርቶ ለዕይታ አቅርቧል።

የሚማርበትን ትምህርት ቤት ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችልና አርፋጂ ተማሪን በዘመናዊ አሰራር የሚቆጣጠር ማሽን፣ ዘመናዊ የአስተያየት መስጫ ሳጥን እንደሰራም ይናገራል።

ኔት ወርክና ገንዘብ የማያስፈልገው ስልክ የፈጠረ ሲሆን የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር ካሉበት ሆነው ስብሰባ ማካሄድ የሚያስችል ነው። እነዚህ የፈጠራ ስራዎቹ ከብዙው በጥቂቱ ያውም በጥቅሉ የተገለጹ መሆናቸውን ግን አስምሮበታል - ሃምዛ።

Image copyright University of Gonder

ገመድ አልባው የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ (Wi-power)

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካልና ኮምፒዩተር ምህንድስና የአንደኛ ዓመት ትምህርቱን በመከታተል ላይ የሚገኘው ሃምዛ የአልበርት አንስታይንና የቶማስ ኤድሰንን የሕይወት ታሪኮችና ስራዎች ማንበብ ያዘወትራል።

በኢትዮጵያ የሚታዩ ችግሮችን በፈጠራ ስራዎቹ የመፍታት ህልም አንግቧል፤ እርሱ እንደሚለው ለዚህ የፈጠራ ስራው ተወልዶ ባደገበት ጃን አሞራ ያለው የኃይል መቆራረጥ ለፈጠራው እንዳነሳሳው ይገልፃል።

ቶዮታ ያለአሽከርካሪ የሚንቀሳቀሱ መኪናዎችን ሊያሰማራ ነው

የሁዋዌ ባለቤት ልጅ ካናዳ ውስጥ ታሠረች

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት አቶ ሰለሞን መስፍን፤ ሃምዛ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ ሳለ ስራዎቹን ይከታተላሉ እንደነበር ይናገራሉ። አመርቂ ውጤት በማስመዝገብም ዩኒቨርሲቲውን ሊቀላቀል ችሏል።

አቶ ሰለሞን የእርሱ ፈጠራዎች አካል የሆኑት ገመድ አልባ የኤሌየየክትሪክ ማስተላለፊያና ገመድ አልባ የኢንተርኔት አገልግሎት በዩኒቨርሲቲው እንደተሞከሩ ይገልጻሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የሳይንስ ቀን አስመልክቶ ለሶስተኛ ጊዜ በተከበረው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አገር አቀፍ ውድድር ላይ ገመድ አልባው የኢንተርኔት አገልግሎት (Signal Wi Fi) ፈጠራው ሁለተኛ ደረጃን አግኝቶ ሽልማት ተበርክቶለታል።

ይሁን እንጂ ገመድ አልባው የኤሌክትሪክ ኃይል (Wi power) ከስራዎቹ ሁሉ አዲስና ተሰምቶ የማይታወቅ በመሆኑ የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነቱ እስኪረጋገጥ ድረስ ስለ ስራው በዝርዝር መግለፅ እንደማይፈልጉ አቶ ሰለሞን ጨምረው ተናግረዋል።

"የኤሌክትሪክን ኃይል ያለ ገመድ ማስተላለፍ የማይታመን ነገር ነው" የሚሉት አቶ ሰለሞን በዩኒቨርሲቲው 60 ሜትር ርቀት ላይ እንደተሞከረና ያለምንም የገመድ ማስተላለፊያ አምፖል ማብራት እንደተቻለ በአይናቸው መታዘባቸውን ግን አልሸሸጉንም።

ከዚህ ቀደም በግሉ ባደረገው ሙከራ ኃይሉ በሚተላለፍበት አቅጣጫ ሰዎች ሲሻገሩ ንዝረት ይፈጥር እንደነበርና ያችግር ግን አሁን መስተካከሉን ከራሱ ከሃምዛ እንደሰሙ ጨምረው ገልፀዋል።

Image copyright University of Gonder FB

"የፈጠራ ስራውን በአዕምሮ ባለቤትነት ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው"

ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ከዚህ ቀደም ዣንጥላዎችን እንዲሁም በኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን በመጠገን ከሚያገኘው ገንዘብ ለፈጠራ ስራው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ያሟላ ነበር።

አንዳንዴም በኤሌክትሮኒክስ ንግድ የተሰማሩ የአካባቢው ነጋዴዎች የሚያስወግዷቸውን ቁርጥራጮችና ሌሎች ቁሳቁሶችን ይለግሱታል፤ አንዳንዴም በርካሽ ይሸጡለታል።

ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ ግን ይህ የቀረለት ይመስላል፤ በዩኒቨርሲቲው የፈጠራ ስራ ማዕከልና ቤተ ሙከራዎች እንዲጠቀም፣ መምህራንም በቅርብ እንዲያግዙትና የሚያስፈልገው ነገር እንዲሟላላት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አቶ ሰለሞን ነግረውናል።

የአንስታይን ደብዳቤ በ84 ሚሊዮን ብር

በሕይወት ከሌለች እናት የተወለደችው ሕፃን

ዩኒቨርሲቲውም ተጓዳኝ የሆኑ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት፣ እያንዳንዱን የፈጠራ ስራዎች እንደ አንድ ፕሮጀክት በመውሰድ በጥናት እንዲሰሩ እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸውልናል።

ዩኒቨርሲቲው ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እንደ ሃምዛ ያሉ በፈጠራ ስራ የተሰማሩ ወጣቶችን በማገዝ እየሰራ ይገኛል።

ተማሪው የጊዜም ሆነ የሌላ ጫና እንዳይገጥመው የፈጠራ ስራ ውጤቶቹን ቀስ በቀስ ተግባራዊ እንዲደረጉና በጥናት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ እየሰሩ ነው። በዚህም መሰረት ዩኒቨርሲቲው የፈጠራ ስራው በአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት እንዲመዘገብ ማድረግ ቅድሚያ የሰጠው ጉዳይ ሆኗል።

ፈጠራውን ለማስመዝገብም በሂደት ላይ እንደሚገኙ አቶ ሰለሞን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ተያያዥ ርዕሶች