ፑቲን፡ አሜሪካ ስምምነቱን ጥላ ከወጣች ሩሲያ ሚሳዬል ትገነባለች

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን

አሜሪካ ከሶቪየት ሕብረት ጋር በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ሚሳዬል ላለመገንባት የተደረሰውን ስምምነት ጥላ የምትወጣ ከሆነ ሩሲያ ሚሳዬል መገንባት እንደምትጀምር ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስጠነቀቁ።

እአአ 1987 በአሜሪካ እና በቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት መካከል የተደረሰው ስምምነት አጭርም ይሁን መካከልኛ ርቀት የሚምዘገዘጉ ሚሳኤሎችን መገንባት የሚከለክል ነው።

ባሳለፍነው ማክሰኞ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ሩሲያ ስምምነቱን ጥሳለች ብሎ ወቀሳ ከሰነዘረ በኋላ ነው፤ ፕሬዚዳንት ፑቲን ሩሲያ ከስምምነቱ ልትወጣ እንደምትችል ያስጠነቀቁት።

ሩሲያ 60 የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን አባረረች

ፑቲን እንደሚሉት ከሆነ የኔቶ ወቀሳ አሜሪካ ከስምምነቱ እንድትወጣ ምክንያት ለመሆን ነው።

ፑቲን ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው በሰጡት መግለጫ በርካታ ሃገራት በአሜሪካ እና ሶቪየት ሕብረት መካከል የተፈረመውን ስምምነት በመጣስ የተለያዩ አይነት ሚሳኤሎችን አበልጽገዋል።

''በርካታ ሃገራት የጦር መሳሪያው ስላላቸው አሜሪካውያን አጋሮቻችንም እነሱ ሊኖራቸው እንደሚገባ ያስባሉ'' ያሉ ሲሆን ጨምረውም ''የእኛ ምላሽስ ምንድነው የሚሆነው? ቀላል ነው- እኛም ይኖረናል'' ብለዋል።

ሰሜን ኮሪያ የባለስቲክ ሚሳኤል ወደ ጃፓን አስወነጨፈች

ከዚህ ቀደም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያ ተግባራት ምክንያት አሜሪካ ስምምነቱን ጥላ ልትወጣ እንደምትችል ተናግረው ነበር።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ለሩሲያ ይህ መሳሪያ ከሌሎች አማራጮች ብዙ ወጪ የማያስወጣት ነው።

የኔቶ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ባወጡት መግለጫ ''የኔቶ አባል አገራት ሩሲያ ከአሜሪካ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ወደጎን በመተው 9ኤም729 ተብሎ የሚጠራውን የሚሳኤል ሥርዓት ገንብታ ሙከራ አካሂዳለች'' ብሏል።

Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ ሩሲያ ስምምነቱን በመጣስ የሚሳኤል ግንባታ አካሂዳለች የሚለውን ወቀሳ አትቀበልም።

ኔቶ ይህን መግለጫ ይዞ ከወጣ በኋላ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዎ ሩሲያ ለስምምነቱ ተገዢ ለመሆን የ60 ቀናት ገደብ ተቀምጦላታል፤ ያሉ ሲሆን ሩሲያ ወደ ስምምነቱ የማትመለስ ከሆነ አሜሪካም ምንም አይነት ግዴታ አይኖርባትም ብለዋል።

ሩሲያ በበኩሏ በተደጋጋሚ የቀዝቃዛው ጦርነት ስምምነትን የጣሰ ምንም አይነት ተግባር እንዳልፈጸመች ተናገራለች።

ትራምፕ ፑቲን አሜሪካን እንዲጎበኙ ጋበዟቸው

ትራምፕ ከፑቲን ጋር በተያያዘ ወቀሳ እየዘነበባቸው ነው

እአአ 1987 በአሜሪካ እና በቀድሞዋ ሶቪየት ዩኒየን መካከል የተፈረመው እና የመካከለኛ ርቀት ኒውክለር ኃይል ስምምነት እየተባለው የሚጠራው ሰነድ ሁለቱ ሃገራት ከባህር ላይ ከሚወነጨፉ መሳሪያዎች ውጪ ምንም አይነት የኒውክለር ይዘት ያላቸውንም ሆነ የሌላቸውን ሚሳኤል ባለቤትነትን ይከለክላል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ በወቅቱ የሶቪየት ሕብረት መሪ የነበሩት ሚካኤል ጎርቫቾቨ እና የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሮናልድ ሬገን ስምምነቱን እአአ 1987 ላይ ሲፈርሙ።

በስምምነቱ መሰረት እስከ አውሮፓዊያኑ 1991 ድረስ 2700 ሚሳኤሎች ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ ተደርገው ነበር። በተጨማሪም ይህ ስምምነት አንዳቸው የአንዳቸውን ጣቢይ እንዲፈትሹ ፍቃድ ይሰጣል። 2017 ላይ ቭላድሚር ፑቲን ስምምነቱ የሩሲያን ፍላጎት ያማከለ አይደለም ብለው ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ