ወገኖቹን ለመርዳት ከከተማ የራቀው ዶክተር ቴዎድሮስ

ዶክተር ቴዎድሮስ ወርቁ

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የማስተማሪያ ሆስፒታል ለህሙማን የሚያቀርበውን ደም የሚያገኘው አምቡላንሶቹን በደርሶ መልስ ስምንት ሰዓት በሚፈጅ ጉዞ ወደ ጅማ ከተማ በመላክ ነው።

ኦክስጂን የሚያመላልሱለት መለስተኛ የጭነት መኪናዎች ደግሞ ከአምስት መቶ በላይ ኪሎ ሜትር አቆራርጠው ወደ አዲስ አበባ መጓዝ አለባቸው።

ለወትሮውም ቢሆን በሆስፒታሉ እጥረት ተከስቶ የህሙማንን ህይወት ለከፋ አደጋ ከመጋለጡ በፊት ደም፣ ኦክስጂን እና መድኃኒት በተገቢው ጊዜ ማግኘቱ የራሱ ቢሮክራሲያዊ የራስ ምታቶች አሉት።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ሌላ ጋሬጣም ተጨምሮበታል - ፖለቲካዊ ያለመረጋጋት እና የመንገዶች መዘጋጋጋት።

ሆስፒታሉ ካለበት ቦታ ወደ ጅማ የሚወስዱ ሁለት መንገዶች ሲኖሩ የቴፒ ከተማን አቋርጦ የሚያልፈውን ዘለግ ያለው መንገድ በስፍራው ባለ ፖለቲካዊ ያለመረጋጋት የማይደፈር ካደረገው ሰነባብቷል።

በቦንጋ በኩል ጅማ የሚያደርሰው ሌላኛው መንገድ አማራጭ ሆኖ ቢቆይም እርሱም ቢሆን ያለፉትን ጥቂት ሳምንታት ሰላም አልነበረውም።

የከፋ ዞን በመጀመሪያ ከቡና መገኛነት ጋር፤ ለጥቆም በክልል ደረጃ ራስን ከማስተዳደር ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተቃውሞ ሰልፎችን ሲያስተናግድ ይሄኛውም መንገድ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በድንጋይ፣ በተበላሹ መኪኖች እና በወደቁ ዛፎች ለቀናት ተዘጋግቷል።

"መንገዱ ከተከፈተ በኋላ ስሄደበት ሰባ ሰባት ቦታ ላይ ተዘግቶ እንደነበር ቆጥሬያለሁ" የሚለው የሆስፒታሉ ዋና የህክምና ሥራ አስኪያጅ የሆነው ዶክተር ቴዎድሮስ ወርቁ ነው።

በሌሎች ጊዜያት እንደዚህ ተቃውሞዎች እንቅስቃሴን በሚገቱበት ወቅት አምቡላንሶችን ማሳለፍ የተለመደ ቢሆንም፤ መንገዱ በዛፍና በመሳሰሉ ግዙፍ ቁሶች ከተዘጋ ግን የማለፍ ዕድል እንደማይኖር የሚያስረዳው ዶክተር ቴዎድሮስ፤ የከፋ ዞኑ ተቃውሞ ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በሄሌኮፕተር ለማስመጣት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር ንግግር ጀምሬ ነበር ይላል።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የማስተማሪያ ሆስፒታል በያዝነው ዓመት ሰማንያ ሚሊዮን ብር አካባቢ በጀት ከመንግሥት ተመድቦለት፣ በ430 የህክምና እና የአስተዳደር ሠራተኞች ከሁለት ሚሊዮን ለሚልቁ የአካባቢው ነዋሪዎች የጤና ክብካቤ ግልጋሎት እንዲያቀርብ የሚጠበቅ ተቋም ነው።

ዶክተር ቴዎድሮስ ሃያ ስድስተኛ ዓመቱን ሳያጋምስ ነው የሆስፒታሉን የህክምና ክፍል የማስተዳደር ኃላፊነትን የተረከበው።

በኃላፊነት በቆየባቸው ያለፉት አምስት ወራት ቶሎ ቶሎ ከፍ ዝቅ የሚለው የፖለቲካ ትኩሳት ሥራው ላይ ጫና ማሳረፉን አይክድም።

በተቃውሞ ምክንያት "የቴፒ ሆስፒታል ወደ ሁለት ሳምንት ሥራ አቋርጦ በመቆየቱ ወደእኛ የሚመጡ በሽተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ነበር" እንዲሁም ከህክምና ቁሳቁሶች በተጨማሪ "ከፍ ያለ ህክምና የሚፈልጉ በሽተኞችን ወደሌላ ሆስፒታል ለመላክም ተቸግረን ነበር" ይላል።

ፈተናን መጋፈጥ

ዶክተር ቴዎድሮስ ሚዛን ቴፒ ያደረሰው የሥራ ህይወት ጎዳና ተግዳሮትን ለመጋፈጥ ካለው ዝንባሌ እንደሚነሳ ይናገራል።

ከአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ጥቁር አንበሳ ልዩ የህክምና ሆስፒታል ከሁለት ዓመት በፊት በህክምና እንደተመረቀ ቀጣይ ትምህርቱን እንዲከታትል የሚያስችለውን ውጤት ማስመዝገብ ችሎ ነበር።

ለአንድ ዓመት ከአራት ወራት ያህል ከትምህርቱ ጋር በተያያዘ እንዲያሟላ የሚጠበቅበትን የጠቅላላ ህክምና ሥራ እያከናወነ እዚያው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ባለበት ጊዜ ነበር ከመዲናይቱ ወጣ ብሎ ኅበረተሰብን የማገልገል ውሳኔ ላይ የደረሰው።

ቴዎድሮስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሞላ ጎደል በሁሉም ቦታዎች ያለው የሐኪሞች ቁጥር ከታማሚው ፍላጎት ጋር የማይመጣጠን ቢሆንም ከከተሞች እየተራቀ በተሄደ ቁጥር የችግሩ አሳሳቢነት እንደሚበረታ ጠፍቶት አያውቅም።

"በአብዛኛው የሚጎዱት ገጠር አካባቢ ያሉ [ታማሚዎች] ናቸው። በጠቅላላ ሐኪም ደረጃ ሊታከሙ የሚችሉ ብዙ ችግሮች፤ በርካታ ሰዎችን ለአደጋ እያጋለጡ፤ ለህልፈትም እያደረሱ ስለሆነ" ይህንን ለመጋፈጥ መፈለግ ተቀዳሚ ገፋፊ ምክንያቱ እንደሆነ ያወሳል።

ቀድሞ አማን ሆስፒታል ተብሎ ይታወቅ ወደነበረው የአሁኑ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የማስተማሪያ ሆስፒታል እንደደረሰ በፅንስ ክትትል እና ማዋለድ ክፍል የጠቅላላ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ነው ሥራ የጀመረው።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ምቾቱን በመተው ወደ ገጠር ያቀናው ዶክተር ቴዎድሮስ

ከጥቁር አንበሳ የህክምና ትምህርት ቤት ቆይታው በተለየ ያለማንም ክትትል ሥራ መጀመሩ ፍርሃት እንዲሰማው ሳያደርገው አልቀረም።

"ህይወትን ማዳን አልችል ይሆን የሚል ስጋት ገብቶኝ ነበር። ጥቁር አንበሳ እያለሁ በምሠራበት ወቅት ሁሌም የበላይ የሆነ ተቆጣጣሪ ክትትል ያደርግልኝ ነበር። እዚህ ግን ሁሉንም ነገር ብቻየን ነው የማደርገው" ይላል ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ።

ይሁንና ተወልዶ ካደገባት ከመዲናይቱ አዲስ አበባ አንፃራዊ ምቾት ርቆ ሊሠራ ሲወስን፤ አንደኛው ምክንያቱ በፈተና ለመገራት መሻቱ ነበር።

ሀና እና ጓደኞቿ የሰሩት የእናቶች ምጥ መቆጣጠሪያ አሁን ለሚያክመው ለእያንዳንዱ ታማሚ ኃላፊነቱ ከሞላ ጎደል እርሱ ላይ የሚወድቅ ነው።ይህም የሙያ ሥነ ምግባሩን ከወትሮም በላቀ የበረታ እንዲያደርግ፤ የኃላፊነት ስሜቱን የበለጠ እንዲጠነክር እንዳስገደደው እና በሒደቱም የተሻለ ሐኪም እያደረገው እንደሆነ ያምናል።በእርግጥም ለመላመድ ጊዜ አልፈጀበትም።

እንዲያውም ከሁለት ወራት ቆይታ በኋላ 38 ሐኪሞችን ጨምሮ ሁለት መቶ ሰላሳ የህክምና ባለሞያዎችን የሚይዘውን የሆስፒታሉን የህክምና ክፍል በበላይነት እንዲመራ ታጨ።

"ወደ ሃላፊነት ከመጣሁ በኋላ የተማርኩት ትልቁ ነገር" ይላል ዶክተር ቴዎድሮስ "በህክምናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮች ምን ያህል ውስብስብ እና ከሥርዓት ዝርጋታ ጋር የሚያያዙ መሆናቸው ነው።"

የችግሮቹ መወሳሰብ በርካታ ወጣት ሐኪሞችን ከሐገር በብዛት እንዲፈልሱ እንዳደረጋቸው እገነዘባለሁ ይላል ዶክተር ቴዎድሮስ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ድረ-ገፅ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ዝቅተኛ የህክምና ባለሞያዎች ካሉባቸው አገራት ተርታ የምትገኝ ናት ሲል ያስረዳል።

የፍልሰቱ መንስዔዎች አንድም ምጣኔ ሃብታዊ በሌላም በኩል የተጨማሪ ዕውቀትን በመፈለግ የተሻለ ባለሞያ የመሆን ፍላጎቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምቱን አስቀምጦ አብረውት ከተመረቁ ወጣት ሐኪሞች መካከል ወደ ውጭ ያቀኑ ወይንም ወደ ውጭ ለመጓዝ ሒደት ላይ የሆኑ በርካቶችን እንደሚያውቅ ይናገራል።

ዶክትር ቴዎድሮስ እነዚህን የህክምና ባለሙያዎች ወደዚያ የገፏቸውን ምክንያቶች እንደሚረዳ፤ ውሳኔያቸውንም እንደሚያከብር አፅንዖት ሰጥቶ ይገልፃል።

"ውጭ አይሂዱ፣ አይማሩ፣ አይሻሻሉ አይባልም፤ ሆኖም "ከሐኪሞች ቁጥር ማነስ፣ ከሙያውም አስፈላጊነት ጋር በተገናኘ ለአገሪቷ በጣም ያስፈልጋሉና ተመልሰው መምጣት የሚችሉበት ዕድል ካለ መልካም ነው" ይላል።

የተስፋ ፍንጣቂ

እራሱን ከፍ ላሉ ኃላፊነቶች ለማጨት ባይታወር እንዳልሆነ የሚገልፀው ዶክተር ቴዎድሮስ፤ በተማሪነት ጊዜውም የህክምና ተማሪዎችን ማኅበር በአመራርነት በማገልገል እንዲሁም ከመጀመሪያ ዲግሪ የህክምና ተማሪ የማይጠበቅ ቢሆንም ምርምሮችን በመሥራት እና ለህትመት በማብቃት ራሱን መፈተኑን በአስረጅነት ያነሳል።ብዙዎች የማይደፍሩትን የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን ጋብ አድርጎ፤ ከአዲስ አበባ ርቆ በሐኪምነት ለመስራት ሲወስንም የሚያውቁት ያልተደነቁት ለዚህ ነው።በጠቅላላ ሐኪምነት በሠራባቸው ሁለት ወራት አስቀድሞም የጠበቀውን ያህል የህክምና ችግር ማስተዋሉ የውሳኔውን ትክክለኛነት እንዳሳመነውም ያስረዳል።ነገር ግን የሆስፒታሉን የህክምና ክፍል የመምራት ኃላፊነትን ከተቀበለ ወዲህ የዘርፉ ችግሮች "እስካሁ ከማውቀውና ከገመትኩትም በላይ የተወሳሰቡ መሆናቸውን ልብ ብያለሁ" ይላል።

የህክምናው ዘርፍ ባለሞያዎችን ከሚያበቃበት መንገድ አንስቶ፣ መድኃኒቶችን እና ቁሳቁሶችን እንስሚያሰራጭበት ስልት ድረስ የሥርዓት ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው እያመነ መምጣቱን የሚናገረው ዶከትር ቴዎድሮስ "ጉዳዩ የሰዎች መቀያየር አይደለም" ይላል።

ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ወራት በአገሪቱ ውስጥ የታየው የፖለቲካ ለውጥ ወገግታውን ማሳረፉን ልብ ማለቱንም ይናገራል።

"እንደዜጋ በአገሪቱ ያለው ለውጥ ተስፋ እንድትይዝ ያደርግሃል። በሐኪሞች ዘንድም ሌላ ቦታ ያለው ዓይነት መነቃቃት ያለ ይመስለኛል።"