ሳዑዲ የኻሾግጂን ተጠርጣሪ ገዳዮች አሳልፌ አልሰጥም አለች

አደል አል ጁቤር Image copyright AFP

የሳዑዲው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አደል አል ጁቤር ሃገራቸው በጋዜጠኛ ጃማል ኻሾግጂ ግድያ ወንጀል የተጠረጠሩ ዜጎቿን ለቱርክ አሳልፋ እንደማትሰጥ አስታወቁ።

አደል አል ጁቤር ''ዜጎቻችንን ለማንም አሳልፈን አንሰጥም።'' ሲሉ ተደምጠዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት የቱርኩ ፕሬዚዳንት ኤርዶዋን ተጠርጣሪዎቹን ይሰጡን ብለው የጠየቁ ሲሆን፤ አንድ የሃገሪቱ ፍርድ ቤት ደግሞ ባለፈው ረቡዕ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር።

ትራምፕ ውግዘት ከደረሰባት ሳዑዲ ጎን ቆመዋል

«ኻሾግጂ አደገኛ ሰው ነበር» የሳዑዲው ልዑል

ባለፈው ጥቅምት በቱርክ የሳዑዲ ኤምባሲ ውስጥ ከተፈጸመው ከግድያ ጋር በተያያዘ ሳኡዲ 11 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውላለች።

የቱርኩ ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ከቆረጠላቸው ተጠርጣሪዎች መካከል ደግሞ የሳኡዲው የደህንነት ቢሮ ሃላፊው አህመድ አሲሪና የቀድሞው ንጉሳዊ አማካሪ አል ቃታኒ ይገኙበታል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቱርክ በጉዳዩ ዙሪያ ያገኘችውን መረጃ ለሳኡዲ ያጋራችበትን መንገድ ተችተዋል።

''የቱርክ ባለስልጣናት በተጠርጣሪዎች ላይ ያገኙትን ማስረጃ እንዲያጋሩን ብንጠይቅም በተገቢው ሁኔታ ልናገኘው አልቻልንም።'' ብለዋል።

ሳዑዲ አሁንም ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን በጉዳዩ እጃቸው እንደሌለበት እየተከራከረች ቢሆንም፤ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ግን ከፍተኛ የንጉሳዊ ቤተሰብ እጅ አለበት ሲሉ ተደምጠዋል።

የሳዑዲ ፖሊስ በበኩሉ ወንጀሉ የተፈጸመው አፈንግጠው በወጡ አካላት እንጂ ትእዛዝ ከማንም ተሰጥቷቸው አልነበረም ብሏል።

ጀማል ጂ ማን ነበር?

ጀማል በሳዑዲ ዝነኛ ጋዜጠኛ ነበር፤ የሶቪየት ሕብረት የአፍጋኒስታን ወረራን በዝርዝር ዘግቧል። እንደ ኦሳማ ቢን ላድን ከመሳሰሉ ግለሰቦች ጋር ቃለ መጠይቅ አድርጓል።

የጋዜጠኛው አስክሬን 'በአሲድ እንዲሟሟ ተደርጓል'

ለበርካታ አስርት ዓመታት ለሳዑዲ ንጉሳውያን ቤተሰብ የቅርብ ሰው ነበር፤ የሳዑዲ መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን አማካሪ ሆኖም ሰርቷል።

ባለፈው ዓመት ግን ከሳዑዲ መንግሥት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሃገር ጥሎ ወደ አሜሪካ ተሰደደ። አሜሪካም ሆኖ የዋሽንግተን ፖስት አምደኛ ሆነ።

በጽሑፎቹ የሳዑዲ አረቢያውን ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማንን ይተች ነበር።