ኦባንግ ሜቶ ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ተስፋና ስጋት አለ

ኦባንግ ሜቶ

ልክ የዛሬ 17 ዓመት ጋምቤላ ውስጥ በአኙዋኮች ላይ የተፈፀመው ግድያ ወደ ሰብአዊ መብት ተከራካሪነት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት የሆነው ኦባንግ ሜቶ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ ተስፋና ስጋትን ይዟል ስለዚህ መስተካከል ያሉባቸውን ነገሮች ልናከናውን ይገባል ይላል።

ቢቢሲ፡ ከአስራ ስድስት ዓመታት የውጭ ቆይታ በኋላ ወደኢትዮተመልሰሀል። ምን ስሜት ፈጠረብህ?

ኦባግ ሜቶ፡ የተሰማኝማ ብዙ ነገር ነው። እኔ የምሰራው የሰብዓዊ መብት ሥራ ነው። ለአስራ ስድስት ዓመት ያህል ሰርቻለሁ። እና ሁሌም የምሟገተው ለኢትዮጵያዊያን መብት ነው። ሰብዓዊ መብት ስንል ለኢትዮጵያዊያን መብት ማለት ነው። የብሄር መብት አይደለም። የአንድ ጎሳ፣ የአንድ ኃይማኖት ወይንም ክልል አይደለም። የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መብት ማለት ነው።

እና ወደ አገር ቤት መመለሴ ትልቅ ደስታ ነበር የፈጠረብኝ። ሰው ሞቶ፣ የሰው አካል ጎድሎ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎ ነው ለዚህ የበቃነው። እነዚህ ሰዎች መስዋዕትነት ባይከፍሉ ኖሮ እዚህ ልሆን አልችልም ነበር። በራሴ እኔ ያደረግኩት ነገር የለም። እነርሱን ማመስገን በጣም አስፈላጊ ነው። ለውጡ የሁሉም ቢሆንም የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት የሞቱት ሰዎች ናቸው፣ የቆሰሉ ሰዎች ናቸው። እስር ቤት የነበሩ ሰዎች ናቸው። ይሄንን አስታውሳለሁ።

በእስር ቤት ውስጥ ሰቆቃና ግፍ ለተፈጸመባቸው ካሳ ሊጠየቅ ነው

ቴሬዛ ሜይ ሥልጣናቸውን እንዳያጡ ተሰግቷል

ቢቢሲ፡ ለመጨረሻ ጊዜ ወደኢትዮጵያ በመጣህ ጊዜ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አልነበርክም። ወደዚያ የወሰደህ መንገድ ምን ዓይነት ነበር?

ኦባግ ሜቶ፡ ለሰብዐዊ መብት ተከራካሪ ወደመሆን እገባለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። ከዚህ በፊት በጋምቤላ ግጭት ነበር። ያኔ የሞቱ 424 ሰዎች ነበሩ። ዛሬ ሐሙስ አስራ ሰባት ዓመት ሞላው። ከዚያ በኋላ ነው ለሰብዓዊ መብት መታገል የጀመርኩት።

ያኔ ሰዎቹን የገደለው የመከላከያ ሠራዊት ነበር። አሁንም ወደኢትዮጵያ ስንመለስ የሰብዓዊ መብት ላይ የሚከራከር ቡድን አለን። ከዚያ ቡድን አስራ ስድስት ሆነን ነው የመጣነው። ከአስራ አራት የተለያዩ ብሄሮች ነው የተገኘነው። ቡድኑን የምትመራው ኤድና አለማየሁ ናት። ስድስቱ ሴቶች ናቸው። ስንመጣ ዋነኛ ዕቅዳችን የነበረው ወደ ጋምቤላ ለመሄድ ነበር። የእኔ መገኛ ከዚያው ስለሆነ።

ሄደንም መልዕክት ስናስተላለፍ፤ በቀል አይደለም የሚያስፈልገው ነው ያልነው። እና እኛ ያሰብነው ጋምቤላ የእርቅ ምንጭ እንዲሆን ነው። የእርቅ ሒደቱ የሚጀመርበት ማዕከል እንዲሆን ነው። ግድያው ሲፈፀም የተነጣጠረው በአኙዋክ ብሄረሰብ አባላት ላይ ነበር። እነርሱ አሁን በቀለኞች ሊሆኑ ይችላሉ። ግድያው የተፈፀመው በመከላከያ ሰራዊት አባላት ስለነበረ ምሬት ሊኖር ይችላል።

እኔ ግን ያሰብኩት፤ መጥፎን ነገር በመጥፎ ነገር ማስተካከል አይቻልም። ስለሆነም ሰዎቹን ሰበሰብን፤ ከዚህ በፊት ያልተሞከረ ነገር አደረግን። ከዚህ ቀደም ስለሞቱት ሰዎች ምንም አይነሳም። ምንም ማስታወሻ የለም። ትንሽ ቪዲዮ ነበረን እርሱን አሳየን። የሞቱት ሰዎች የእያንዳንዳቸው ስም ተነበበ። መታሰቢያ እንዲኖር ነው የፈለግነው። ለበቀል ሳይሆን ከዚህ በኋላ እንዳይደገም። እንዲህ መሰል ነገር ዳግመኛ መኖር የለበትም። ይሄንን አድርገን ወደ አዲስ አበባ ተመለስን።

የ7 ዓመቷ ህፃን መፀዳጃ ቤት አልሰራልኝም ስትል አባቷን ከሰሰች

ፈረንሳይ 'አላሁ አክበር' ብሎ ተኩስ የከፈተውን ግለሰብ በማደን ላይ ናት

ኻሾግጂ የዓመቱ ምርጥ ሰው ዝርዝር ውስጥ ተካተተ

ቢቢሲ፡ ከውጭ እንደመጣህ የመጀመሪያ ጉዞህን ያደረግከው ወደጋምቤላ ነበር። በዚህ ሳምንት አጋማሽ ተመልሰህም ትሄዳለህ። ለምን ጉዳይ ነው?

ኦባግ ሜቶ፡አዎ። አሁን አርባ ሁለት ዓመቴ ነው። ሃያ ስምንት ዓመት ያህል በውጭ ነው የኖርኩት። እ.ኤ.አ በ2001 ገደማ ወደጋምቤላ ሄጄ የኗሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል የሚያግዝ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አቋቁሜ እንቀሳቀስ ነበር። ከዚያ እ.ኤ.አ. 2003 በክልሉ ሆስፒታል ለማቋቋም እየጣርን ነበር። ሆኖም ያኔ በክልሉ እና በፌዴራል መንግሥት መካከል ውጥረት ነበር። የጋምቤላ አስተዳዳሪ እና ሌሎችም ሰዎች ሲታሰሩ ውጥረቱ ይበልጡ ከረረ።

በታህሳስ ወር ወደ ሱዳን የስደተኞች ጣብያ በማቅናት ላይ የነበረ ተሽክርካሪ ጥቃት ደረሰበት። በውስጡ የነበሩ ዘጠኝ ሰዎች አለቁ። ጋምቤላ የነበረው የሃገር መከላከያ ሠራዊት ታዲያ ጥቃቱን የፈፀሙት የአኙዋክ ብሄረሰብ ታጣቂዎች ናቸው በማለት እርምጃ መውሰድ ጀመሩ። ሂውማን ራይትስ ዋች በዚህ ጉዳይ ላይ ጥሩ ሪፖርት አጠናቅሯል። ከተገደሉት ሰዎች መካከል የተወሰኑትን አውቃቸዋለሁ።

ከዚያ በኋላ ነው ፍትህን ፍለጋ የጀመርኩት። የአኙዋክ ፍትህ ጉባዔ የሚሰኝ ተቋም መሰረትኩ። ከዚያም ለሰብዓዊ መብት ወደ መታገል ገባሁ። እነርሱ ባይሞቱ ኖሮ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችም አልሆንም ነበር። መንግሥት ክስተቱን ሲያስተባብል ነው የኖረው።

አሁን ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ሰዎች ማውራት የጀመሩት። ሐሙስ አስራ ሰባተኛ ዓመት ይሆነዋል። ከዚያን ሁሉ ጊዜ በኋላም ግን ትናንትና የተከናወነ ነው የሚመስለኝ። አዕምሮዬ ውስጥ አሁንም ለጋ ነው። እናም ለመጀመሪያ ጊዜ ሞታቸው የተደበቀ አይሆንም። እርሱን በሚያስታውስ ዝግጅት ላይ ለመገኘት ነው የምሄደው።

ቢቢሲ፡ ከዚያ በኋላም ወደተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ተጉዘሃል። ምንድን ነበር ዓላማህ?

ኦባግ ሜቶ፡ ወደ ሌሎች ስድስት ክልሎች ተጉዘናል። ዋናው ዓላማችን ከሰዎች ጋር ለመገናኘት እና ሃሳባቸውን ለመስማት ነበር። ሕዝቡ ምን እያለ ነው? ብለን ለማዳመጥ። የሰብዓዊ መብት ሥራ የአዲስ አበባ ወይንም የከተማ ብቻ አይደለም። ዓላማችንም በመጀመሪያ አገሩን እስካሁን ካቆዩ ሽማግሌዎች ጋር ለጥቆም ነገ የሚረከቧት ወጣቶችን ለማግኘት ነው።

የኃይማኖት አባቶችም ጥበብን ፍቅርን የማስተማር ኃላፊነት አለባቸው። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የተከናወነው ነገር ቀላል አይደለም። ሌላው ቀርቶ ምግባር (ሞራል) የሚባል ነገር ከልጆቻችን ተወስዷል። ብዙዎች ስለኢትዮጵያዊነታቸው ቀርቶ ስለማንነታቸው የማያውቁ አሉ። ከማኅበረሰብ ውስጥ የሰዎችን ሥነ ምግባር ስትወስድ ገደልካቸው ማለት ነው።

አንደኛው በየቦታው የታዘብኩት ነገር ብሔራዊ ስሜት የሚባል ነገር ያለመኖሩን ነው። ሁሉም በየብሔሩ ነው። ይሄንን ትውልድ እንዴት ነው መቀየር የሚቻለው? ብዙ ሥራ ያስፈልጋል። ከከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ስንገናኝም ያነሳነው ይሄንን ነው። የእኛ ተቋም የሚለው ከዘር በፊት ሰብዓዊነት ይቅደም ነው። ሰው በሰውነቱ በቂ ነው ነው። ሁላችንም አብረን ነፃ ካልወጣን አንዳችንም ነፃ ልንወጣ አንችልም ነው።

በየቦታው እንደተመለከትነው ትልቅ ተስፋ አለ። ግን ደግሞ ስጋትም አለ። ይሆናል ተብሎ የማይታሰበው ሲሆን ያመጣው ተስፋ ትልቅ ነው። ያ ደግሞ እኔንም ጨምሮ ማለት ነው። ተስፋ ደግሞ ያለተግባር ዋጋ የለውም። በጊዜም ይወሰናል። እስከመቼ ድረስ? እነዚህ ወጣቶች ጥሩ ትምህርት ያገኛሉ ወይ? ጥሩ ሥራ ያገኛሉ ወይ? በየቦታውስ ያለው ግጭት?

ብዙ ሰዎች ይፈናቀላሉ። በብሄር ፖለቲካ ምክንያት ነው። ይህን ችግሩ ፖለቲካ ነው ያመጣው። በእኔ አመለካከት ዋናው ችግር ሌላ ሳይሆን በብሔር የተቃኘው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ነው። ለምን ቢባል ሥርዓቱ ሲተገበር ለአገሩ ዕድገት አይደለም፣ ለሰላም አይደለም፣ ለእኩልነት አይደለም፣ ለፍትህ አይደለም። አገር የሚመሩ ሰዎችን ለመጥቀም ነው።

ቢቢሲ፡ አንዴ ላቋርጥህና. . . አሁን ያለው ብሔር ተኮር ፌዴራላዊ ርዓት የተለያዩ ፍላጎቶችን ለማመቻመች ልዩነቶችን ለማቻቻል እና ብዝነትን ለማክበር ያለው ብቸኛ መንገድ ነው ሲሉ የሚከራከሩ ወገኖች አሉ።

ኦባግ ሜቶ፡ መወያየት አለብን። ምናልባት የብሔር ፌዴራሊዝሙን አጥብቀው የሚደግፉ ሰዎች የራሳቸውን ጥቅም የሚያሰሉ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ ሥርዓት ጥሩ ቦታ እናገኛለን ብለው ያሰቡ ሊሆን ይችላሉ። ቢሆንም መወያየት አለብን። ሥርዓቱ ሲፀድቅ ሕዝቡ አልተወያየም እኮ። የየክልሉ ድንበር ሲወሰን የተወያየ የለም። ለመምራት እንዲመች ነው። ለፍትህ፥ ለእኩልነት አልነበረም።

ብሔር ብሔረሰቦች ብለን እዚህ እንጨፍራለን። በኋላ ሲገናኙ መገዳደል። ችግር እንዳለ ሁላችንም ማመን አለብን። ካመንን በኋላ እንዴት እንፈታዋለን ብሎ ማሰብ ነው። ሃቀኛ ሰዎች ከሆነን። በእኛ ተቋም ጥናት መሠረት አስራ ስድስት ቦታዎች የብሔር ግጭቶች የተስተውሎባቸዋል። ኢትዮጵያ እኮ ሰማንያ ብሄር ብሄረሰቦች አሏት። ሁሉም እኩል ውክልና አላቸው? አንዳንዶቹ ስማቸው ተጠቅሶ ክልል ሆነዋል። ሌሎቹስ? በዚያ ላይ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል፣ አፋር፣ ሱማሌ አጋር ናቸው ይባላል። መገለል ነው ይሄ።

ቢቢሲ፡ ስለዚህ በተለምዶ መል አገር (ሴንተር) በሚባሉት እና ዳር አገር (ፔሪፌሪ) በሚባሉት አካባቢዎች መካከል ውጥረት ወይንም የአያያዝ ልዩነት አለ ብለህ ታምናለህ?

ኦባግ ሜቶ፡አገሪቷን ከመሩት ሰዎች ድንቁርና የመጣ ነው። የአራቱ ክልሎች ፓርቲዎች ናቸው ገዥውን ፓርቲውን የፈጠሩት። ሌሎቹስ አጋር ብቻ? ምንድን ነው ይሄ መገለል ካልሆነ? እነዚህ ክልሎች ሲገለሉ ነው የኖሩት። እኛ ሁላችንም ከሌላው እኩል ለአገራችን ስንደማ፣ ስንሞት ነው የኖርነው። ስድብ ነው ለእኛ።

ቢቢሲ፡ በየሄድክባቸው ቦታዎች ሁሉ ሰዎች እየመጡ ሰላም ሲሉህ ሲያቅፉህ ፎቶ አብረውህ ሲነሱ በማኅበራዊ ሚዲያ አይተናል። እንዴት አየኸው?

ኦባግ ሜቶ፡ ከምንም በላይ ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው። ይች አገር የጎደላት ነገር ፍቅር ነው። እና ራስን ማክበር ነው። አንድ ኢትዮጵያዊ ብሔሩን፣ ኃይማኖቱን የት እንደተወለደ የማላውቀው ኢትዮጵያዊ መጥቶ ልክ እንደማውቀው ወንድም ሲያቅፈኝ ወደ አዕምሮዬ የሚመጣው ብቸኛው ነገር ለአንድ ብሔር ሳይሆን ለሰብዓዊነት ለመታገል መወሰኔ ልክ እንደነበር ነው የሚያረጋግጥልኝ።

ለምሳሌ ጎንደር ላይ የተደረገልኝ አቀባበል ጋምቤላ ላይ ከነበረውም አቀባበል የበለጠ ነው። እንዲያውም ለጓደኞቼ 'አሁን የማንነት ዘመን ላይ ነው ያለነው። እኔም ማንነቴን አገኘሁት፤ በአያቴ ጎንደሬ ነኝ' እያልኩ ስቀልድ ነበር።

የኢትዮጵያን ውበት ኖሬበት አይቼዋለሁ ነው የምለው። ለምሳሌ ወደ ሐረር አካብቢ የሄድን ጊዜ ከገበሬዎች ጋር ተገናኝቼ ነበር። አንዳንዶቹ 'ከዚህ በፊት ከጋምቤላ የመጣ ሰው አይተን አናውቅም ነበር፤ አንተ የመጀመሪያው ነህ' ብለውኛል። ሆኖም ግን ከእነርሱ አንዱ እንደሆንኩ አድርገው ነበር የተቀበሉኝ።