ቁርስ የቀኑ እጅግ አስፈላጊ ምግብ ነውን?

ቁርስ የቀኑ እጅግ አስፈላጊ ምግብ ነውን? Image copyright Vince Talotta

ጤናማና የተስተካከለ ሰውነት ያላቸው ሰዎች ቁርሳቸውን አይዘሉም ይባላል። ነገር ግን ቁርስ መብላት ሙሉ በሙሉ ጤናማ ወይም ቀጭን ያደርገናል ማለት አይደለም።

ነገር ግን ምን ያህሎቻችን ቁርስ በትክክለኛው ሰአት እንመገባለን?

ቁርስ ሳይዘሉ መመገብ ትክክለኛ መሆኑን ለማሳየት የሚቀርበው ምክንያት ሌሊቱን ሙሉ ሲጾም ያደረ ሰውነታችንን በምግብ መጠገን አለብን የሚለው ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ሰውነታችን የሚያድገው እና ጉዳት የደረሰባቸው የሰውነት ክፍሎች የሚጠገኑት በምንተኛበት ወቅት መሆኑ፤ ብዙ ጉልበት እንድንጨርስ ያደርገናል።

ስለ አንጀታችን የማያውቋቸው ስድስት አስገራሚ እውነታዎች

ስለዚህ በቁርስ ሰአት ምግብ መብላት ብቻ ሳይሆን የተመጣጠነ ምግብ መመገብ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የስነ ምግብ ባለሙያዋ ሳራ ኤልደር ትናገራለች።

ነገር ግን አሁንም ድረስ ቁርስ የዕለቱ እጅግ አስፈላጊ ምግብ ነው ወይ? በሚለው ሃሳብ ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም።

ቁርስ አስፈላጊ ነው ወይስ አይደለም?

በተለያዩ ጥናቶች መሰረት ቁርስ መብላትም ሆነ ቁርስ መዝለል ተያይዘው የሚነሱት ካላስፈላጊ ውፍረት ጋር ነው። ምንም እንኳን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የተለያዩ ሃሳቦች ቢኖሩም፤ ግንኙነቱ ግን ምንድነው?

ሰባት ዓመታት በፈጀና 50 ሺ ሰዎች በተሳተፉበት አንድ ጥናት መሰረት የተመጣጠነ ቁርስ በሰአቱ የሚመገቡ ሰዎች ምሳ ወይም እራት ሰአት ላይ ከበድ ያለ ምግብ ከሚመገቡ ሰዎች አንጻር፤ የክብደት መጠናቸው ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ እንደተገኘ ያሳያል።

አትክልት ብቻ ስለሚመገቡ ሰዎች ሊያውቋቸው የሚገቡ ነገሮች

አጥኚዎቹ እንደሚሉት እነዚህ ቁርሳቸውን በትክከል የተመገቡ ሰዎች ቀኑን ሙሉ የሚሰማቸው የረሃብ ስሜት የቀነሰ እንደሚሆንና የሚመገቧቸው ምግቦች መጠን እንደሚቀንስ ያስረዳሉ።

የተመጣጠነ ቁርስ በተገቢው ሰአት መመገብ ያልቻሉት ሰዎች ደግሞ ሰውነታቸው ሌሊቱን ሙሉ ያቃጠለውን ሃይል መተካት ስላለበት፤ ቀኑን ሙሉ ምግብ ቢመገቡም የመርካት ስሜት ስለማይኖራቸው ከመጠን ያለፈ ምግብ እንዲመገቡ ይገደዳሉ።

ሆኖም አጥኚዎቹ ቁርስ ያልተመገቡ ሰዎች በቀጥታ ላላስፈላጊ ውፍረት የተጋለጡ ናቸው የሚለውን ሃሳብ ማረጋገጥ አልቻሉም።

Image copyright anamejia18

ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያጋጠማቸው 52 ሴቶችን ያካተተ የ12 ሳምንት ጥናት ተደርጓል። ሁሉም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ምግብ ሲሆን የሚሰጣቸው፤ ግማሾቹ ቁርስ እንዲበሉና ግማሾቹ ደግሞ ቁርስ እንዳይበሉ ተደርገዋል።

በተገኘው ውጤት መሰረትም ተሳታፊዎቹን ክብደት እንዲቀንሱ ያደረጋቸው ቁርስ ሳይሆን፤ በተደጋጋሚ የሚያደርጉት ነገር በመቅረቱ ነው።

በጥናቱ ለመሳተፍ ከምጣታቸው በፊት ቁርስ ይመገቡ የነበሩት ግማሾቹ ሴቶች ቁርስ ሳይመገቡ ለ12 ሳምንታት ከቆዩ በኋላ 8.9 ኪሎ የቀነሱ ሲሆን፤ ከጥናቱ በፊት ቁርስ የማይመገቡ የነበሩት ግማሾቹ ደግሞ ለ12 ሳምንታት ቁርስ እንዲመገቡ ከተደረጉ በኋላ 7.7 ኪሎ ቀንሰዋል።

ልጆችዎ ጤናማ ምግብ እንዲመገቡ ማድረጊያ መላዎች

ቁርስ መብላት ወይም አለመብላት ውፍረት ለመቀነስ ማረጋገጫ መሆን ካልቻለ፤ በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት ታዲያ ምንድነው?

በአቤርደን ዩኒቨርሲቲ የምግብ ፍላጎት ፕሮፌሰር የሆነችው አሌክሳንድራ ጆንስቶን እንደምትለው አብዛኛዎቹ ቁርስ የሚመገቡ ሰዎች የጠዋት እንቅስቃሴ የማድረግና ከሱሶች የመራቅ ባህሪ አላቸው።

ስለዚህ በቁርስና በውፍረት መካከል ያለውን ግንኙነት እስኪረጋገጥና በደንብ የዳበረ ጥናት እስኪሰራበት ድረስ ይሄ ነው ብሎ ለመደምደም ከባድ ነው ትላለች አሌክሳንድራ።

ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ለማስተካከል የሚረዱ ዘጠኝ ሚስጥሮች

በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት በተሰራ ሌላ የዳሰሳ ጥናት መሰረት የቁርስ ሰአትን ማሳለፍ በደማችን ውስጥ የሚገኘውን የስኳር መጠንና የደም ግፊትን ለመቀነስ እንደሚረዳ ያሳያል።

ምንም እንኳ ሙሉ ውጤቱ ገና ይፋ ባይደረግም፤ ከሰሬይና አቤርደን ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የጥናት ባለሙያዎች የደረሱበት መረጃ እንደሚያሳየው ከበድ ያለ ቁርስ መመገብ ክብደትን ለመቆጣጠር ይረዳል።

አሁን አሁን እየወጡ ባሉ መረጃዎች መሰረት ግን ቁርስ የሚያያዘው ከብደት ጋር ብቻ አይደለም። ቁርሳቸውን የማይበሉ ሰዎች በልብ በሽታ የመጠቃት እድላቸው 27 በመቶ የጨመረ ሲሆን፤ ታይፕ 2 በሚባለው የስኳር በሽታ የመያዝ እድላቸው ደግሞ 21 በመቶ የጨመረ ነው።

Image copyright KucherAV

ከዚህ በተጨማሪ ቁርስ መመገብ የአእምሮ መነቃቃት ለመፍጠርም ይረዳል ተብሏል። ይህ ማለት ለነገሮች ትኩረት ሰጥተን እንድንሰራና ህጻናት ደግሞ በቀላሉ ቋንቋዎችን እንዲማሩ ይረዳቸዋል።

ጫትን መቆጣጠር ወይስ ማገድ?

ቁርስ መብላት በራሱ ወሳኝ እንዳልሆነና ጉልህ ልዩነት የሚፈጥረው በቁርስ ሰአት የምንመገበው የምግብ አይነት ነው ብለው የሚከራከሩም አልጠፉም።

የተመጣጠነ ቁርስ መመገብ ለብዙ ነገር ቢጠቅምም፤ ማንኛውንም የምግብ ሰአት አክብሮ መመገብና ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ለማግኘት መሞከር ተገቢ እንደሆነ የስነ ምግብ ባለሙያዋ ሳራ ኤልደር ትመክራለች።