ሳዑዲ የአሜሪካ 'ጣልቃ ገብነትን' አወገዘች

ሞሃመድ ቢን ሳልማን እና ትራምፕ በዋይት ሃውስ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ትራምፕ አሜሪካ ከሳዑዲ ጋር ስላላት የንግድና ወታደራዊ ግንኙነት ቀጣይነት ሲሟገቱ ቆይተዋል

አሜሪካ ሳዑዲ በየመን እያደረገች ላለችው ጦርነት የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ እንድታቆም ሴኔቱ ውሳኔ ማስተላለፉን ሳዑዲ አውግዛለች።

በጋዜጠኛ ኻሾግጂ ግድያም ሴኔቱ የሳውዲው ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን ተጠያቂ በማድረጉም ነው ሳዑዲ አሜሪካን የወቀሰችው።

የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሴኔቱን ውሳኔ እውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተና ጣልቃ ገብነት የታየበት ብለውታል።

ባለፈው ሳምንት ሴኔቱ ያስተላለፈው የውሳኔ ሃሳብ የመፅደቅና ህግ የመሆን እድሉ እጅግ አነስተኛ ነው ቢባልም ሳውዲ የሴኔቱን እርምጃ አውግዛ ብቻ አላረፈችም። ይልቁንም ለትራምፕ ቁጣዋን ማሳወቅን መርጣለች።

''የሚፈርስ የግድቡ አካል የለም'' የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ

የአለማየሁ ተፈራ ፖለቲካዊ ካርቱኖች

የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያወጣው መግለጫ ይህን የአሜሪካ እርምጃ አገሪቱ እንደምትቃወም አስታውቋል።

የሳዑዲ መግለጫን ተከትሎ እስካሁን አሜሪካ የሰጠችው ይፋዊ ምላሽ የለም።

ሴኔቱ ሃሙስ እለት ያስተላለፈው ውሳኔ በአገሪቱ የ1973 የጦርነት ህግ መሰረት፤ የአሜሪካ ኮንግረስ አካል የሆነ ክፍል አገሪቱ የወታደራዊ ድጋፏን እንድታቋርጥ ውሳኔ ሲያስተላልፍ ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

ቁርስ የቀኑ እጅግ አስፈላጊ ምግብ ነውን?

አስገዳጅ ያልሆነው የሴኔቱ ውሳኔ ሃሳብ እስላማዊ ፅንፈኞችን እየተዋጉ ከሚገኙት ውጭ አሜሪካ በየመን ግጭት ያሳተፈቻቸው ሃይሎቿን እንድታስወጣ ለትራምፕ ጥሪ የሚያስተላልፍ ነው።

ሴኔቱ በጋዜጠኛ ሃሾግጂ ግድያም የሳውዲው ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማንን ተጠያቂ ያደረገው በሙሉ ድምፅ ነው።

አሜሪካ ባለፈው ወር ለሳዑዲ የጦር አውሮፕላኖች ነጃጅ መሙላት አቁማ ነበር። አሁን ደግሞ ይህ የሴኔቱ የውሳኔ ሃሳብ ህግ መሆን ከቻለ ክልከላው የሚፀና ይሆናል ማለት ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ