ከአፋር እስከ ዲሲ፤ በዚህ ሳምንት የሚጠበቁ አምስት አበይት ክስተቶች

ቭላድሚር ፑቲን Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ቭላድሚር ፑቲን

ዕለተ ሰኞ ላይ እንገኛለን፤ አዲስ ሳምንት ጀምረናል። ምንም እንኳ ሳምንቱ ይዟቸው የሚመጣቸውን ነገሮች ሁሉ ማወቅ ባንችል ተጠባቂ የሆኑትን ግን መጠርጠሩ አያዳግትም። በያዝነው ሳምንት ይከሰታሉ ተብለው የሚጠቁ አበይት ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? እነሆ አምስቱን።

አፋር፤ ሰመራ

የአፋር ክልል ምክር ቤት ዛሬ ሊያካሂደው ባቀደው አስቸኳይ ጉባኤ ርዕሰ መስተዳድር እና የምክር ቤት አፈ ጉባኤ እንደሚሾም ይጠበቃል።

አፋር ብሔራዊ ዴሞከራሲ ፓርቲ በ7ኛ ድርጅታዊ ጉባኤው ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት ሌሎች የተለያዩ ሹመቶች እንደሚሰጡም ነው የሚጠበቀው።

ምክር ቤቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለመተግበር የሚያስችል የአስፈፃሚ አካላትን አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን በተዘጋጀ አዋጅ ላይም ውይይት ካደረገ በኋላ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በሳተላይቶች ዙሪያ ሰባት አስደናቂ እውነታዎች

(አዲስ ርዕሰ መስተዳድር ለአፋር ክልል

የአፋር ክልል ምክር ቤት ዛሬ ማካሄድ በጀመረው አስቸኳይ ስብሰባ አቶ አወል አርባን ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾሟል።

አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር በቅርቡ ክልሉን ከሚያስተዳድረው የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ሊቀ መንበርነት የተሰናበቱትን አቶ ስዩም አወልን በመተካት ነው መንበሩን የተረከቡት።

አዲሱ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ በቅርቡ አብዴፓ ባደረገው የአመራር ለውጥ የፕረቲው ምክትል ሊቀ መንበር እንዲሆኑ ተመርጠዋል።

የክልሉ ምክር ቤት እያካሄደ ባለው ስብሰባ ከርዕሰ መስተዳደሩ በተጨማሪ አፈ ጉባኤ መምረጥ እንዲሁም አዲስ በተመረጡት ርዕሰ የሚቀርቡ ሹመቶችን ያፀድቃል ተብሏል። )

ቭላድሚር ፑቲን

የሩስያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በየዓመቱ ከተመረጡ ሩስያውያውን ጋር የሚያደርጉት ውይይት ሐሙስ ዕለት እንደሚከናወን ይጠበቃል። በቴሌቪዥን መስኮት የሚተላለፈው ይህ ስብሰባ ሰዓታትን የሚፈጅ ሲሆን 4 ሰዓት ከ40 ደቂቃ የፈጀው ትልቁ እንደሆነ ይነገርላቸዋል።

«የተወደዱ ፑቲን፤ እንወድዎታለን፤ እናከብርዎታለን» ሲል ነበር አንድ ተሰብሳቢ ባለፈው ዓመት በነበረው ንግግሩን የጀመረው። ዘንድሮም በርካታ ማንቆለጳጰሶች ለፑቲን እንደሚወርድላቸው ይጠበቃል።

ስብሰባውን ይበልጥ ተጠባቂ ያደረገው ነገር ግን ፑቲን ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ስማቸው በተደጋጋሚ መነሳቱ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ፑቲን ምን ይሉ ይሆን?

ከጦርነት ይልቅ ለብዙዎች ሞት ምክንያት የሆኑት አይጦች

የብሪታኒያ እና አውሮፓ ሕብረት ፍቺ

ከፊታችን ረቡዕ ጀምሮ ብሪታኒያ እና የአውሮፓ ሕብረት በይፋ ፍቺ ለመፈፀም 100 ቀናት ይቀራቸዋል።

በእንግሊዝኛው 'ብሬግዚት' የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው ይህ ፍቺ ከመገናኛ ብዙሃን አፍ ጠፍቶ አያውቅም። ፍቺው 100 ቀናት ብቻ ይቅሩት እንጂ ብሪታኒያ ከአውሮፓ ሕብረት በምን ዓይነት ሁኔታ ትለይ የሚለው ጉዳይ አከራካሪነቱ ቀጥሏል።

አሁን አሁንማ ብሪታኒያ ተመልሳ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ትዳሯን ልታድስ ይሆን እየተባለ ይወራም ተጀምሯል።

የዲሞክራቲክ ኮንጎ ጭንቀት

በሕዝብ ብዛት በአፍሪካ አራተኛዋ ሃገር ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሕዝብ የፊታችን ዕሁድ ወደ ምርጫ ጣብያዎች በማምራት ድምፃቸውን ይሰጣሉ። ምርጫው መካሄድ ካለበት ሁለት ዓመታት ዘግይቶ ነው እየተከናወነ ያለው።

ሃገሪቱ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ብዙ መከራ አይታለች፤ ግጭቶች እዚያም እዚህም ተከስተዋል፤ በርካቶችም ተፈናቅለዋል።

የዛሬ ሁለት ዓመት ምርጫው ሊከናወን አካባቢ በነበረው ውጥረት ምክንያት ፕሬዝደንት ጆሴፍ ካቢላ ጊዜው በሁለት ዓመት እንዲራዘም ጠይቀው ነበር። ተቺዎች ግን የስልጣን ዕድሜያቸውን ለማራዘም አስበው እንጂ ሲሉ ወቅሰዋቸው ነበር።

ሃገሪቱ በፈረንጆቹ 1960 ከቤልጅየም ቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች ጀምሮ ሰላማዊ ምርጫ አከናውና አታውቅም፤ አሁንም በሃገሪቱ የተወሰኑ ክፍሎች ግጭቶች እየተስተዋሉ ነው።

ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ስለተዘረፉ ቅርሶች ምን እናውቃለን?

አሜሪካ ጨለማ ውስጥ

የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በጀት ጉዳይ ካልተስማሙ ዕለተ አርብ የአሜሪካ መንግሥት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ይገባል።

ይህ ማለት ማንኛውም በመንግሥት የተያዘ መሥሪያ ቤት አገልግሎት መስጠት ሊያቆም ይችላል ማለት ነው፤ ከቪዛ መጠየቂያ ቤቶች እስከ ብሔራዊ ፓርኮች ከአገልግሎት ውጭ ሊሆኑ ይችላሉ።

ትራምፕ ለድንበር ጥበቃ የሚሆን 5 ቢሊዮን ዶላር (136 ቢሊዮን ብር ገደማ) ይበጀትልኝ ማለታቸው ነው ፖለቲከኞቹን ለዚህ ዓይነቱ አተካራ የዳረጋቸው።

ትራምፕ ከዲሞክራቶች ጋር በነበራቸው ስብሰባ ለግንቡ የሚሆን ብር ካልተመደበልኝ «የመንግሥት ሥራን በኩራት እዘጋለሁ» ሲሉ ማወጃቸው አይዘነጋም።