ሀና ጥላሁንና ጓደኞቿ የእናቶችን ምጥ በሚቆጣጠረው የፈጠራ ሥራቸው አሸነፉ

ሃና ከሽልማቷ ጋር

ሀና ጥላሁንና ጓደኞቿ በጂማ ዩኒቨርሲቲ የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ ትምህርታቸውን ተከታትለው በ2010 ዓ.ም ተመርቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ የእናቶችና ሕጻናት ጤንነት ጉዳይ ወጣቶቹን ያሳሰባቸው ገና ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ ነበር፡፡ "ሴት በመሆናችን ነገ እኛንም የሚገጥመን ጉዳይ ነው" ይላሉ ወጣቶቹ፡፡

ታዲያ ሃሳብ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር በመመረቂያ ጽሁፋቸው ለዚሁ ጭንቀታቸው መላ የሚሆን ሃሳብ ጸነሱ፤ የጥናታቸው ይዘት በወሊድ ወቅት የእናቶችን ምጥ የሚቆጣጠር መሳሪያ ለመስራት የሚያስችል ነበር፡፡

በቡድን በሰሩት በዚህ የመመረቂያ ጽሁፋቸውም በይበልጥ ይህንኑ ሃሳብ አጎለበቱት፤ ወደ ፈጠራ ሥራቸው ገፋቸውም፡፡ የፈጠራ ሥራቸው ሀ ሁ ም በዚህ መልኩ ተጀመረ፡፡

በጋራ ሆነው የእናቶች ምጥ መቆጣጠሪያ መሳሪያ (Agumentation and Induction Monitoring Device) እውን አደረጉት፡፡

''የሚፈርስ የግድቡ አካል የለም'' የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ

ይህንን የፈጠራ ስራ ከሰሩት ወጣቶች መካከል አንዷ የሆነችውና ቡድኑን ወክላ ያነጋገርናት የ23 ዓመቷ ሀና ጥላሁን ሁሉም ለጥናትና ምርምር የተለየ ፍቅር እንዳላቸው ትናገራለች።

በመሆኑም የእናቶችን አወላለድ የህክምና ሂደት ለማየት የጂማ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የካቲት፣ የጦር ኃይሎችና የሌሎች ሆስፒታሎች ማዋላጃ ክፍሎችን ጎብኝተዋል፤ የዘርፉ ሐኪሞችንም አማክረዋል፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን እናቶች ለመውለድ ዝግጁ መሆን አለመሆናቸውን እንደ ሐኪሞቹ እነርሱም በወላድ እናቶች የማህጸን በር ጣታቸውን በማስገባት ስሜቱን ለመረዳት ሞክረዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ነበር እነሱ የሰሩት የአንዲትን ሴት የምጥ ሁኔታ የሚቆጣጠረው መሳሪያ ያለምንም ንክኪ ለእናትየዋም ሆነ ለሐኪሞች የሚኖረውን ጠቀሜታ በይበልጥ መረዳት የቻሉት፡፡

የፈጠራ ሥራቸው በቀበቶ መልክ የተዘጋጀ ሲሆን ሆድ ላይ በማስቀመጥ አንዲት ሴት ምጥ መጀመሯን አለመጀመሯን የሚያመላክት ነው፤ ምን ያህል መጠን መድሃኒት እንደሚያስፈልጋትም የሚጠቁም መሳሪያ እንደተገጠመለትም ሀና ታስረዳለች፡፡

ሳዑዲ የአሜሪካ 'ጣልቃ ገብነትን' አወገዘች

ሀና እንደምትለው መሳሪያው ምንም ዓይነት የኤሌክትሪክ ጨረር የሌለው ሲሆን በእናትየዋም ሆነ በፅንሱ ላይ የሚያሳድረው አንዳችም ተፅዕኖ የለም።

"ልክ እንደ አልትራ ሳውንድ መሳሪያ ሲሆን ልዩነቱ አልትራ ሳውንድ በምስል መልክ ሲያሳይ የእኛ ግን በቁጥር ይገልጻል" ትላለች።

መሳሪያውን በቀላሉ በተገኙና በርካሽ ከውጭ አገር በተገዙ ቁሳቁሶች መሰራቱ ልዩ እንደሚያደርገው የምትናገረው ሀና በአጠቃላይ 2500 ብር ብቻ እንዳስወጣቸው ትናገራለች፡፡

ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስም አይከብድም፤ የሚመዝነው 1.5 ኪሎግራም ብቻ ነው፡፡

እርሷ እንደምትለው ውስብስብ ባለመሆኑም በ30 ደቂቃ ስልጠና ማንኛውም ሰው ተገንዝቦ ሊሰራበት ይችላል፡፡

በተለይ በአገራችን የሚታየው የመብራት መቆራረጥ ችግርን ከግምት በማስገባት የፈጠራ ሥራውን በባትሪ እንዲሰራ ለማድረግ እቅድ እንዳላቸው ትናገራለች፡፡

"ያደጉት አገራት እንዲህ ዓይነት መሳሪያ የሚጠቀሙ ሲሆን፤ዋጋው የማይቀመስ በመሆኑ በአገር ውስጥ የጎበኘናቸው ሆስፒታሎች መሳሪያው የላቸውም" የምትለው ሀና የሰሩት ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል እምነት አላት፡፡

በውድድሩ አሸናፊ ከመሆን ባሻገር መሳሪያው በደንብ ተፈትሾ ተግባር ላይ ሲውል ማየት የሀናና የጓደኞቿ ህልም ነው፡፡

የእናቶች ምጥ መቆጣጠሪያ

አዋላጅ ሐኪምና በአዋላጅ ሐኪሞች ማህበር የቀድሞ ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ ያለው ላይቀር አንዲት እናት ምጥ ላይ ሆና መግፋት ቢያቅታትና ብትደክም ምጡን ለማፋጠን የሚጠቀሙት መድሃኒት (Augmentation)፤ በሌላ በኩል ደግሞ የመውለጃዋ ቀን ደርሶ ምጥ ባይጀምራትና የማህፀን በሯ ዝግ ከሆነ ምጥ ለማስጀመር የሚጠቀሙት (Induction) እንደሚባል ያብራራሉ፡፡

ምንም እንኳን እነዚህን ሁኔታዎች ለማረጋገጥ እናትየዋ በምታሳየው ምልክቶች መረዳት ቢቻልም በማህፀን በር ገብቶ በእጅ ማየት ግን ግድ ነው ይላሉ።

የማህፀን በሯ ዝግ ከሆነ የአንድን ጣት ጫፍ እንኳን ማስገባት አይችልም፤ በዚህም መሰረት ልኬቱ እናትየዋ ልትወስዳቸው የሚገቡ መድሃኒቶችን ለመስጠትና ለመመጠን እንደሚያስችላቸው ይናገራሉ ባለሙያው፡፡

እርሳቸው ባላቸው ልምድ ይህንን የሚያሳይ መሳሪያ ጎራ ባሉባቸው እንግሊዝና አሜሪካ ቢያዩም ኢትዮጵያ ውስጥ ግን እስካሁን እንዳልገጠማቸው ይናገራሉ።

ቁርስ የቀኑ እጅግ አስፈላጊ ምግብ ነውን?

ይህ በውጭው ዓለም ያዩት መሳሪያ በአንድ ጊዜ አስር የሚሆኑ እናቶችን ምጥና የአወላለድ ሁኔታ መከታተል ያስችላል ይላሉ፡፡

"እንደዚህ ዓይነት መሳሪያዎች ደግሞ ሥራን በማቀላጠፍና በትንሽ የሰው ኃይል መስራት በማስቻል ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ነው" የሚሉት አቶ ያለው የወጣቶቹን ፈጠራም ሳያደንቁት አላለፉም፡፡

በተለይ አንዲት ሴት ስትወልድ ማንም ሊያያት አይገባም የሚል ልማድ ባለበት አገር፤ ወላዶች የተዋልዶ አካላቸውን ነጻ ሆነው ሌላ ሰው እንዲነካቸው እንደማይፈልጉ ያስረዳሉ፡፡

በዚህም ምክንያት "እናቶቹ ስለሚሸማቀቁና ደስተኛ ስለማይሆኑ የባሰ ሰውነታቸው እንዳይፍታታ ቆጥበው ይይዙታል" ይላሉ አቶ ያለው፡፡

እንዲህ ዓይነት የባህል ችግሮችን ለመፍታትም ሆነ ጉዳዩን ከማቅለል አንፃር የመሳሪያው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሚሆንም እምነት አላቸው፡፡

ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ቴክኖሎጂ የራሱ የሆነ ተጽዕኖም ሊኖረው ስለሚችል ሳይንሱን ማሳደግና መፈተሽ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ፡፡

ውድድሩ በማን ተዘጋጀ

አፍሪካውያን ወጣቶች የፈጠራ ስራቸውን ያቀረቡበት ይህ ውድድር በኢትዮጵያ ወጣቶች ሳይንስ አካዳሚ፣ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ ተቀማጭነቱን ፈረንሳይ አገር ባደረገው Association for Promotion Science in Africa (APSA)ና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ትብብር ነበር የተዘጋጀው፡፡

በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የሚዲያ ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያው አሰግደው ሽመልስ እንደተናገሩት ውድድሩ በፈጠራ ስራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ስራዎችን በአፍሪካ ደረጃ አወዳድሮ ማቅረብ፣ ድጋፍ ማድረግና አስፈላጊውን ስልጠና እንዲያገኙ ማስቻል ዋና ዓላማው ነበር፡፡

ለመላው አፍሪካ ወጣቶች በቀረበው የውድድር ጥሪ 129 የፈጠራ ሃሳቦች የቀረቡ ሲሆን ከ7 የአፍሪካ አገራት፤ የካሜሩን፣ ቤኒን፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ናይጀሪያ፣ ቶጎና ኡጋንዳ ወጣቶች ለመጨረሻ ዙር መሻገር ችለዋል፡፡

የእነዚህ ወጣቶች ሥራ የሆኑት የግብርና ስራን የሚያቀላጥፉ ፣ የቤት ውስጥ ስራን የሚያቃልሉ፣ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚረዳ መሳሪያ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ ምርታማ የሽመና መሳሪያ፣ አዝዕርትን የሚያጠቁ ነፍሳትን በኤሌክትሪክ ዘዴ ለአርሶ አደሮች መረጃ ማቅረብ የሚችል ቴክኖሎጂዎች ቀርበው ለአራት ቀናት ተጎብኝተዋል፡፡

የሃምዛ ሃሚድ ገመድ አልባ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ

በዚህም በኢትዮጵውያን ወጣቶች የተሰራው የምጥ መቆጣጠሪያ መሳሪያ የአንደኝነት ደረጃ በመያዝ አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡

በዕርቅ እስከመቼና በጓደኛው የተሰራው በኤሌክትሪክ የሚሰራ የሽመና መሳሪያ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ የካሳቫ ተክልን ከቆሻሻና ከሰው ንክኪ በጸዳ መልኩ የተለያዩ ምርቶችን እንዲሰጥ የሚያስችለው የካሜሩናዊው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ፈጠራ በሶስተኝነት ተመርጧል፡፡

እንዲህ ዓይነት ውድድሮች በፈጠራ ስራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችን ለማበረታታት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው የሚሉት አቶ አሰግደው ተመሳሳይ ውድድሮችን በየዓመቱ ለማካሄድ እቅድ እንደተያዘም ለቢቢሲ ገልጸዋል፡፡

ተያያዥ ርዕሶች