ለፖለቲካ ፍላጎት የተጋጋለ ግጭት ነው፡ ሙስጠፋ ኡመር

ሞያሌ ከተማ

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የሆኑት አቶ ሙስጠፋ ኡመር የግጭቱን መንስዔ ሲያስረዱ፤ በግጦሽ መሬት ሰበብ ከኃይለስላሴ መንግሥት ጀምሮ በተደጋጋሚ ግጭቶች ይከሰቱ እንደነበረ አስታውሰው፤ ''ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ግን ሆነ ተብሎ የፖለቲካ ፍላጎት ተጨምሮበት የተጋጋለ ግጭት ነው'' ይላሉ።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ተቀስቅሶ የነበረውን የኦሮሞ ወጣቶች ተቃውሞ ለማዳከም በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች የሶማሌ ፖሊስን አንቀሳቅሰው በኦሮሚያ እና ሶማሌ ደንበር አዋሳኝ ስፍራዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድረሰዋል ይላሉ አቶ ሙስጠፋ ኡመር።

ፓርቲዎች የምርጫ ቦርድን በሚመለከት ረቂቅ አዋጅ ላይ እየመከሩ ነው

ከዚህ በፊት የነበረው ግጭት ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነበረ። በግጭቱ የተጎዱ በሁለቱም በኩል ያሉት ኃይሎች ቁጭት እና ንዴት ስላለባቸው ግጭት እንዲቀጥል እያደረጉ ነው። አሁንም ግጭቱ እንዲቀጥል የሚያደርጉት እነርሱ ናቸው ይላሉ ሙስጠፋ ኡመር።

ኢትዮጵያን ከኬንያ ጋር በሚያዋስነው አካባቢ ዋነኛዋ ከተማ በሆነችው ሞያሌ፤ የግጭት፣ የሞት እና የመፈናቀል ዜና መስማት እየተለመደ የመጣ ይመስላል። ነዋሪዎቿም በፍርሃት እና በሽብር መኖር ከጀመሩ ወራትን አስቆጥረዋል።

መንግሥት ''በስህተት የተፈጸመ ነው'' ብሎ ከ10 በላይ ንጹሃን ነዋሪዎቿ ህይወታቸውን ያጡባት፤ በከተማዋ የሚኖሩ የኦሮሞ እና ሶማሌ ወጣቶች በሞያሌ ከተማ አስተዳደር ባለቤትነት ጥያቄ በድንጋይ የሚወጋገሩባት፤ ከፍ ሲልም በይዞታ ይገባኛል ምክንያት በጦር መሳሪያ የታገዙ ኃይሎች የሚፋለሙባት ግጭት፣ ሞት እና መፈናቀል የማያጣት ከተማ ሆናለች።

እንደ አዲስ ከሁለት ሳምንታት በፊት በተቀሰቀሱ ግጭቶችም በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ቆስለዋል፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

"በምን ማስተማመኛ ነው የምንመለሰው" የሞያሌ ተፈናቃዮች

ከዓይን እማኞች፣ ከጎሳ መሪዎች እና ከአካባቢው ባለስልጣናት እንደሰማነው ከሆነ ቢያንስ እንደ አዲስ ባገረሹት ግጭቶች እስካሁን ከ20 ሰዎች በላይ ተገድለዋል።

የሰሞኑ ግጭት የተቀሰቀሰው ኦሮሚኛ ቋንቋ ተናገሪ በሆኑት ገሪ ተብለው በሚታወቁት የሶማሌ ጎሳ አባላትና በኦሮሞዎች መካከል በይዞታ ይገባኛል ምክንያት ነው።

በኦሮሞ በኩል ያሉት የሞያሌ ወረዳ ኃላፊዎች ድንበር ተሻግረው በከባድ መሳሪያ ህዝቡ ላይ ጥቃት የሚፈጽሙት የሶማሌ ታጣቂዎች ናቸው ይላሉ። በሶማሌ ወገን ያሉት በበኩላቸው ለግጭቱ፣ ለሞትና መፈናቀሉ የኦሮሞ ታጣቂዎች ላይ ጣታቸውን ይቀስራሉ።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የሆኑት አቶ ሙስጠፋ ኡመር የግጭቱን መንስዔ ሲያስረዱ፤ በግጦሽ መሬት ሰበብ ከኃይለስላሴ መንግሥት ጀምሮ በተደጋጋሚ ግጭቶች ይከሰቱ እንደነበረ አስታውሰው፤ ''ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ግን ሆነ ተብሎ የፖለቲካ ፍላጎት ተጨምሮበት የተጋጋለ ግጭት ነው'' ይላሉ።

በሞያሌ ከተማ በደረሰ ፍንዳታ የሰው ህይወት ጠፋ

ከጥቂት ዓመታት በፊት ተቀስቅሶ የነበረውን የኦሮሞ ወጣቶች ተቃውሞ ለማዳከም በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች የሶማሌ ፖሊስን አንቀሳቅሰው በኦሮሚያ እና ሶማሌ ደንበር አዋሳኝ ስፍራዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድረሰዋል ይላሉ አቶ ሙስጠፋ ኡመር።

ከዚህ በፊት የነበረው ግጭት ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነበረ። በግጭቱ የተጎዱ በሁለቱም በኩል ያሉት ኃይሎች ቁጭት እና ንዴት ስላለባቸው ግጭት እንዲቀጥል እያደረጉ ነው። አሁንም ግጭቱ እንዲቀጥል የሚያደርጉት እነርሱ ናቸው ይላሉ ሙስጠፋ ኡመር።

''ሞያሌን እንደ ሞቃዲሾ''

አቶ አሊ ጠቼ የሞያሌ ወረዳ የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ቢሮ ኃላፊ ናቸው። አቶ አሊ ሞያሌ ከተማ ከዘርፈ ብዙ ችግሮቿ ጋር ብዙ ዓመት ተሻግራለች ይላሉ። አቶ አሊ ከሳምንታት በፊት ለተቀሰቀሰው ግጭት ጽንፈኛውን ቡድንን አልሸባብን ጭምረው ተጠያቂ ያደርጋሉ።

''አልሸባብ እንዲሁም ከሶማሌ ልዩ ፖሊስ እና ከሃገር መከላከያ ያፈነገጠ ኃይል ከባድ የጦር መሳሪያ በመጠቀም ሞያሌን እንደ ሞቃዲሾ አደረጓት'' ይላሉ።

በርካታ ሰዎች ከሞያሌ በመሸሽ ወደ ኬንያ ገብተዋል

ጉዳዩን ለክልል እና ፌደራል መንግሥት ቢያሳውቁም በቂ ምላሽ አለማግኘታቸውን እና በሞያሌ ሰፍሮ የሚገኘውም የሃገር መከላከያ ሠራዊት ግጭቱን ማስቆም እንዳልቻለም ይናገራሉ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከአምስት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ ግጭቱ እንዲከሰት የሚያደርጉት የሁለቱን ክልሎች መረጋጋት የማይሹ ኃይሎች ናቸው፤ ችግሩን ከመሰረቱ ለመቅረፍ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብሏል። መግለጫው አክሎም በግጭቱ ለተጎዱ ሰዎች አስፈላጊው እርዳታ እየተሰጠ መሆኑን አመልክቷል።

''የፖለቲካ ጦርነት''

የሶማሌ ገሪ ጎሳ መሪ የሆኑት ሱልጣን ሞሐመድ ሃሰን በበኩላቸው ''ሁለቱ ህዝቦች [ገሪ እና ኦሮሞ] ከዚህ ቀደምም በይዞታ ይገባኛል ይጋጩ ነበረ። ይህ አዲስ አይደለም። ይህ ግጭት ግን የይዞታ ይገባኛል ሳይሆን የፖለቲካ ጦርነት ነው'' ይላሉ።

ሱልጣን ሞሐመድ እየደረሰ ላለው ጥፋት የኦሮሞ ታጣቂዎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ''ድንበር ተሻግረው እየወጉን ያሉት እነሱ [የቦረና ኦሮሞ] ናቸው። እኛ እራሳችንን መከላከል ነው የያዝነው። መብታችንን እየተጋፉ ነው። በትልልቅ ጦር መሳሪያዎች የሚወጉን፣ ቤታችንን የሚያቃጥሉት እነሱ ናቸው።'' ይላሉ።

የአለማየሁ ተፈራ ፖለቲካዊ ካርቱኖች

ሱልጣን ሞሐመድ እንደሚሉት ከሆነ፤ የፌደራል እና የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት ግጭቱን በውይይት ለመፍታት ሞያሌ ላይ ስብሰባ ቢጠሩንም በስብሰባው ላይ የኦሮሞ ተወካዮች በእምቢተኝነት ሳይገኙ ቀርተዋል ይላሉ።

''ምንም እንኳ እነሱ ስበሰባው ላይ ባይገኙም፤ እኛ ሰላም ነው የምንፈልገው ስንል ተናግረናል። ከዚያ በኋላም አዲስ አበባ ላይ ለስብሰባ ተጠርተን አባ ገዳው [የቦረና አባ ገዳ] ሳይገኝ ቀረ። የመጡትም ተወካዮች [የኦሮሞ ተወካዮች] ሰላም አንቀበልም ብለው ሄዱ'' ይላሉ።

የቦረና አባ ገዳ ምን ይላሉ?

''የቦረና መሬትን የሸጠው መንግሥት ነው። የግጭቱ መንስዔ መንግሥት ነው። ችግሩን መፍታት ያለበትም መንግሥት ነው'' የሚሉት የቦረና አባ ገዳ ኩራ ጃርሶ ናቸው።

''ሞያሌ ውስጥ ሁለት ባንዲራዎች [የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልል ባንዲራዎች] እስከተውለበለቡ ድረስ በከተማዋ ሰላም ሊሰፍን አይችልም።''

አባ ገዳ ኩራ፤ ሶማሌዎች ዳዋ የሚባል ወረዳ መስርተው ሞያሌን የወረዳው ከተማ ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት ማቆም አለባቸው ይላሉ። "በ1997 ዓ.ም ላይ ተካሂዶ የነበረው ህዝበ ውሳኔ ሳይሆን የመሬት ዘረፋ ነበረ" የሚሉት አባ ገዳ ኩራ መንግሥት ታሪክ ተመልክቶ ውሳኔዎችን ያስተላልፍ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በግጭቱ በመኖሪያ ቤቶች፣ በመንግሥት ቢሮዎች እና ባንኮችን ጨምሮ በንግድ ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱንም የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።