መፈናቀልና ግድያን የተቃወሙ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ግጭት

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ መለያ Image copyright Bule hora university

ከሰሞኑ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ጭንቅላታቸውን ይዘው መሬት ላይ በግንባራቸው ተደፍተው የሚያለቅሱና ሽማግሌዎች ከተጎነበሱበት አንዲነሱ ሲያግባቧቸው የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በስፋት ተሰራጭቷል።ይህም ሁኔታ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎታል።

በተንቃሳቃሽ ምስሉም ላይ የሚታዩት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሲሆኑ በአንሶላና በብርድ ልብስ ጊዜያዊ መጠለያ ሰርተው ሜዳ ላይ የተበተኑና ብሶታችንንና ችግራችንን የሚሰማ አጣን በማለት ምሬታቸውን እየገለፁ ነበር።

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር መርሻ አሻግሬ የታዩት ምስሎች እውነተኛ ስለመሆናቸው ማረጋጋጫ ሰጥተውናል።

ለብሶታቸውም ምክንያት የሆነው በአገሪቱ ላይ ያሉት መፈናቀልና መገደል እንደሆነ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይናገራሉ።

"ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ተስፋና ስጋት አለ" ኦባንግ ሜቶ

ብሄራዊ ባንክ ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ጋር የግሉን ዘርፍ ለማገዝ ስምምነቶችን አደረገ

መጠየቅ ካለብን የምንጠየቀው በጋራ ነው፡ አባይ ፀሐዬ

በአገሪቱ የተለየዩ ክፍሎች በተለይ በኦሮሚያ ክልል ሰዎች ይገደላሉ፤ ይፈናቀላሉ። ሰዎች እየተፈናቀሉና እየሞቱ እኛ አንማርም በማለት ከሁሉም ክልል የመጡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ባለፈው ማክሰኞ ትምህርት አቋርጠው ሰልፍ እንደወጡ ይናገራሉ።

የተሰማቸውን ስሜት አስተላልፈው የተመለሱት ተማሪዎች በቀጣዮቹ ሶስት ተከታታይ ቀናት ትምህርት እንዳልገቡ ያስረዳሉ።

በዚህ ግራ የተጋባው ዩኒቨርስቲም በሶስተኛ ቀናቸው አርብ ዕለት ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀው የሰላም ኮንፈረንስ ስብሰባ ላይ ተማሪዎቹ እንዲሳተፉ ጥሪ ቢያቀርቡላቸውም አሁንም አሻፈረኝ በማለታቸው የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች፣ የዞኑ አስተዳደር፣ የከተማው ከንቲባ ተማሪዎቹ ባልተገኙበት ውይይይቱን አካሂደዋል።

በተጨማሪም በአገራዊ ጉዳይ ላይ ውይይት እናድርግ የሚል ድጋሚ ጥሪ ቢደረግላቸውም "ሰላም በሌለበት፤ ስለ ሰላም አናወራም" በማለት ሳይገኙ እንደቀሩ ዶ/ር መርሻ ይናገራሉ።

ዩኒቨርሲቲው አስቸኳይ የምክር ቤት ስብሰባ ጠርቶ ተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲው ጋር ውይይት ማድረግ ካልፈለጉ በትምህርት ክፍላቸው ውይይት ተደርጎ ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ የሚጠይቅ ማስታወቂያ ማውጣቱን ይናገራሉ።

በዚህ መካከል ከአማራ ክልል የመጡ ተማሪዎች ጥያቄያው ከቀረበ የሚመለከተው አካል መልስ እስኪሰጥ ድረስ "ትምህርት እንጀምር' የሚል አቋም ላይ ቢደርሱም ከሌላ ወገን በኩል ደግሞ ትምህርት መቆም አለበት የሚለው አቋም በመፅናቱ በተማሪዎቹ መካከል በቡድን የተከፋፈለ ውጥረት መንገሱን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይገልፃሉ።

ይህ ውጥረትም አይሎ "አብረን ተስማምተን ያቆምነውን ትምህርት እናንተ እንዴት ትምህርት ትጀምራላችሁ" በሚል መነሻ ሰኞ ሌሊት ግጭት በመፈጠሩ በ2 ተማሪዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ነገር ግን ዩኒቨርስቲው ለምንም ቅድመ ሁኔታ ተማሪዎች ትምህርት እንዲጀምሩ ማስታወቂያ ቢያወጣም ማክሰኞ ሌሊት ግጭት አገርሽቷል።

በግጭቶቹም 12 ተማሪዎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ሁለቱ ከባድ ጉዳት አጋጥሟቸዋል። አንደኛው ግጭቱን ለመሸሽ ሲል ከአንደኛ ፎቅ በመዝለሉ ስብራት ያጋጠመው ሲሆን ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተልኮ ህክምና እተከታተለ ይገኛል። ሌላኛዋ ተማሪም እንዲሁ አይኗን በእስክርቢቶ ተወግታ በሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ህክምናዋን እየተከታተለች እንደምትገኝ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ቀሪዎቹ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው 10 ተማሪዎች በዚያው ቡሌ ሆራ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛሉ።

ይህንንም ተከትሎ ከአማራ ክልል የመጡ ተማሪዎች ግቢውን በመልቀቅ በአንሶላና በብርድ ልብስ ጊዜያዊ መጠለያ ሰርተው ሜዳ ላይ እንደተበተኑ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይገልፃሉ።

ለደህንነታችን እንሰጋለን በሚል ግቢውን ለቀው እንደወጡ የሚናገሩት ዶ/ር መርሻ "ፊት ለፊታቸው ከሚገኝ ህንፃ ፍራሽ በማስገባት እንዲገቡ ቢጠየቁም ፈቃደኛ አይደሉም" ብለዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጨምረውም " ትኩረት ለመሳብ ካልፈለጉ በስተቀር በአሁኑ ሰዓት ወደ ዩኒቨርሲቲው ቢገቡም ማንም ጥቃት የሚያደርስባቸው የለም ሲሉም ያክላሉ።

ተማሪዎቹ ሜዳ ላይ ተበታትነው በዚህ መልክ መገኘታቸውም ለደህንነታቸውም ሆነ የፀጥታ ኃይሎች እነርሱን ለመጠበቅ እንዳልቻሉ ያብራራሉ።

ተማሪዎቹ ባሉበት አካባቢ ምግብ ማቅረብ ስለማይችሉና ለመመገብም ቦታው ምቹ ባለመሆኑ ተማሪዎቹ በአንድ መድረክ ተገናኝተው እስከሚስማሙ ድረስ የተለያየ ሰዓት ተመድቦላቸው በየተራ እየሄዱ እንደሚመገቡ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ዶ/ር መርሻ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልፀው ከትናንት በስቲያ ውይይት ተካሂዶ የኦሮሚያ ተወላጆች ለእርቅ ዝግጁ መሆናቸውን ሲገልፁ በአማራ ተወላጆች በተንቀሳቃሽ ምስሉ እንደታየው አንገታቸውን መሬት ላይ በመድፋት የአባ ገዳዎችን፣ የአገር ሽማግሌዎችንና የሐይማኖት አባቶችን ልመና ሳይቀበሉ እንደቀሩ ያብራራሉ።

"ከክልል ወይም ከፌደራል የመጣ ባለስልጣን በሌለበት በዚህ መልኩ ችግራችን እንዲፈታ አንፈልግም" በማለታቸውም በዛሬው ዕለት ታህሳስ 9/2011 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት፣ የአማራ ክልል የፀጥታና ደህንነት ምክትል ኃላፊ፣ የዞን አስተዳደር እንዲሁም ከፌደራል የመጡ ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

በዩኒቨርሲቲው የፌደራልና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ተበራክተው መገኘታቸው የባሰ ውጥረት ፈጥሯል ስለመባሉ የጠየቅናቸው ምክትል ፕሬዚደንቱ "ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበት አካባቢና ዙሪያው የተለያዩ ግጭቶችና የፀጥታ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ የተማሪዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የክልሉ ልዩ ኃይልና የፌደራል ፖሊሶች ቀደም ብለው የተሰማሩ ናቸው" ብለዋል።

በተማሪዎቹ ላይ ጉዳት አድራሾቹን ለመያዝ እስካሁን ጥረት እየተደረገ እንደሆነ እንጂ መያዝ አለመያዛቸውን በተመለከተ የደረሳቸው መረጃ እንደሌላቸው ይናገራሉ።

የስነ ዜጋና ስነ ምግባር መምህር የሆኑት ነጋሳ ገላና በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው ትምህርት መሰጠት አይጀምር እንጂ በግቢው ውስጥ የሚታይ ግጭትና አለመረጋጋት እንደሌለ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ተያያዥ ርዕሶች