የትራምፕ በጎ አድራጎት ድርጅት እንዲዘጋ ተወሰነ

ትራምፕና ሶስት ልጆቻቸው በጎአድራጎት ድርጅቱን ለግል ጥቅምና ፖለቲካ ትርፍ ተጠቅመውበታል በሚል ተወንጅለዋል Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ትራምፕና ሶስት ልጆቻቸው በጎ አድራጎት ድርጅቱን ለግል ጥቅምና ፖለቲካ ትርፍ ተጠቅመውበታል በሚል ተወንጅለዋል

ዶናልድ ትራምፕ እና ሌሎች ግለሰቦች የትራምፕ ፋውንዴሽንን ገንዘብ ለግል ጥቅምና ለፖለቲካዊ ትርፍ ተጠቅመውበታል በሚል የበጎ አድራጎት ድርጅቱ እንዲዘጋ ተወሰነ።

የትራምፕ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሊዘጋ መሆኑን ያስታወቁት የኒውዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባርባራ አንደርውድ ናቸው።

ትራምፕና ሶስት ልጆቻቸው ለግል ጥቅማቸውና ለፖለቲካ ትርፍ የድርጅቱን ገንዘብ ተጠቅመዋል በማለት ጠቅላይ አቃቤ ህጓ ትራምፕን ከነልጆቻቸው ወንጅለዋል።

በሌላ በኩል የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ጠበቃ፤ ጠቅላይ አቃቤ ህጓ ጉዳዩ ፖለቲካዊ መልክ እንዲይዝ እያደረጉ ነው በማለት ወቅሰዋቸዋል።

ይህ በአሁኑ ወቅት በትራምፕና በቤተሰባቸው ዙሪያ እያንዣበቡ ካሉ የህግ ጥሰት ጉዳዮች አንዱ ሲሆን ከምርጫ ጋር በተያያዘ የትራምፕና የሩሲያ ትብብር ዋነኛው ነው።

በይገባኛል ጥያቄ እሳት የምትለበለበው ሞያሌ

ጠቅላይ አቃቤ ህጓ ባርባራ አንደርውድ እንዳሉት ፋውንዴሽኑ ቢዘጋም በትራምፕ ልጆች ማለትም ዶናልድ ጁኒየር፣ ኢቫንካና ኤሪክ ላይ የተጀመረው ምርመራ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

እሳቸው እንደገለፁት በበጎ አድራጎት ድርጅቱ የተፈፀመው ህገወጥ አሰራር የሚያስደነግጥ አይነት ሲሆን ድርጅቱ የትራምፕን የንግድና የፖለቲካ ፍላጎት ከማስፈፀም የዘለለ ሚና የነበረው አይመስልም።

"ድርጅቱ የትራምፕ የንግድና የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈፀሚያ የቼክ ደብተር ያልተናነሰ ሚና ነበረው" ብለዋል።

በጠቅላይ አቃቤ ህጓ እንደተገለፀው በሚመለከተው ፍትህ አካል ተቆጣጣሪነት ድርጅቱ እንዲዘጋ እንደሚደረግ የድርጅቱ ሃብትና ንብረትም ስመጥር ለሆኑ ተቋማት የሚከፋፈል ይሆናል።

ከወንበርና ከሲጋራ የቱ ይገድላል?

"ይህ የህግ የበላይነትን የማስፈን ድል ነው። ህግ ሁሉንም በእኩል የሚያገለግል መሆኑን ማሳያም ነው" በማለት ትራምፕና የበጎ አድራጎቱ ዳይሬክተሮችም በግልፅ በተደጋጋሚ ለፈፀሙት ጥሰት ኃላፊነት እንዲወስዱ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የበጎ አድራጎቱ ጠበቃ አለን ፉቴርፋስ እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 ትራምፕ ምርጫ ካሸነፉ ጀምሮ ድርጁቱን አፍርሶ ሃብትና ንብረቱን ጥሩ ተሞክሮ ላላቸው ሌሎች ድርጅቶች የማከፋፈል ፍላጎት የነበረ ቢሆንም የኒውዮርክ አቃቤ ህግ ቢሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት ይህ እንዳይሆን ማድረጉን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕና ልጆቻቸው እስካሁን ከበጎ አድራጎት ድርጅቱ መዘጋት ጋር በተያያዘ ያሉት ነገር የለም።

መፈናቀልና ግድያን የተቃወሙ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ግጭት