ኮሚሽኑ ለምን አስፈለገ? ስልጣን እና ተግባሩስ?

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን ለማቋቋም የወጣውን ረቂቅ አዋጅ ከአምስት ሳምንታት በፊት ማጽደቁ ይታወሳል።

ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ የትግራይ ክልላዊ ምክር ቤት የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ ውድቅ እንዲሆን የሚጠይቅ የውሳኔ ሐሳብ አጽድቋል። ምክር ቤቱ የኮሚሽን ማቋቋምያ አዋጁን ኢ-ሕገመንግስታዊ ነው ብሎታል።

መንግሥት በበኩሉ የኮሚሽኑ መቋቋም፤ በክልሎች የአስተዳደር ወሰን፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና በማንነት ጥያቄዎች ዙሪያ የሚታዩ ተደጋጋሚ ችግሮችን በማያዳግም መንገድ ለመፍታት ያስችላል ይላል።

ታኅሣሥ 11 2011 ዓ.ም ረቂቅ አዋጁ የ313 የምክር ቤት አባላትን የይሁንታ ድምጽ አግኝቶ የነበረ ሲሆን 33 አባላት ደግሞ ተቃውመውታል። በተጨማሪም አራት ተወካዮች ድምጸ ተአቅቦ አድረገው ነበረ።

1. የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን ምንድነው?

የአባላቱ ቁጥር በመንግሥት የሚወሰነው ይህ ኮሚሽን፤ ከአስተዳደር ወሰን እና ከማንነት ጥያቄዎች ጋር በተያየዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች የመፍትሄ ሃሳቦችን ይሰነዝራል እንጂ ውሳኔ የማስተላለፍ ስልጣን የለውም። ኮሚሽኑን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ መሰረት ኮሚሽኑ ሥራውን በነጻነትና በገለልተኝነት ያከናውናል ተብሏል።

2. ኮሚሽኑ ለምን አስፈለገ?

በሃገሪቱ ከአስተዳደር ወሰን እና ከማንነት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎች በተለያዩ አካባቢዎች ለአለመረጋጋት መንስዔ መሆናቸው በስፋት ይነገራል።

መንግሥት የኮሚሽኑ መቋቋም፤ በክልሎች የአስተዳደር ወሰን፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና በማንነት ጥያቄዎች ዙሪያ የሚታዩ ተደጋጋሚ ችግሮችን በማያዳግም መንገድ ለመፍታት ያስችላል ይላል።

ኮሚሽኑም ግልጽ እና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከአሰተዳደር ወሰኖች፣ ራስን በራስ ከማስተዳደር እንዲሁም ከማንነት ጋር የተያያዙ ግጭቶችን መንስዔ በመመርመር የመፍትሄ ሃሳቦችን ለህዝብ፣ ለሁለቱ ምክር ቤቶች እንዲሁም ለሥራ አስፈጻሚው አካል እንዲያቀርብ ነው የሚቋቋመው።

3. የኮሚሽኑ ስልጣን እና ተግባር ምንድነው?

ከአስተዳደራዊ ወሰኖች አከላለል፣ ራስን በራስ ከማስተዳደር እንዲሁም ከማንነት ጥያቄ ጋር የተገናኙ ማናቸውንም አይነት ግጭቶችን በጥናት ለይቶ አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በሪፖርት መልክ ያቀርባል።

ከአስተዳደራዊ ወሰኖች እና ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተነሱ ግጭቶች ተፈተው፣ በአጎራባች ክልሎች መካከል ያለው መልካም ግንኙነት የሚታደስበትና የሚጠናከርበትን መንገድ የማመቻቸት ግዴታ ይኖርበታል ተብሏል።

4. የኮሚሽኑ አባላት እነማን ናቸው?

''በሥራ ልምዳቸው በማህበረሰቡ የተመሰገኑና መልካም ስም ያተረፉ ይሆናሉ'' ይላል አዋጁ፤ ስለ ኮሚሽኑ አባላት አሰያያም ሲዘረዝር። የኮሚሽኑ አባላት ቁጥር በመንግሥት የሚወሰን ሲሆን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ እና ሌሎች አባላት በጠቅላይ ሚንስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ወካዮች ምክር ቤት ይሰየማሉ።

5. በኮሚሽኑ መቋቋም ላይ የተነሱ ጥያቄዎች ምንድናቸው?

የአዋጁን መጽደቅ የተቃወሙ የምክር ቤቱ አባላት፤ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ክልሎች እና ባለድርሻ አካላት በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ሳይመክሩበት እና ሳይወያዩበት በጥድፊያ መጽደቁ ትክክል አይደለም በለዋል። ከዚህ በተጨማሪም ሕገ-መንግሥቱን ይጥሳል፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንን ይጋፋል ብለዋል።

በተቃራኒው የረቂቅ አዋጁን መጽደቅ የደገፉት በበሉላቸው፤ አዋጁ በሁለት ቋሚ ኮሚቴዎች ተመርምሮ ከሕገ-መንግሥቱ ጋርም ሆነ ከሌሎች አዋጆች ጋር እንደማይጋጭ ተረጋግጧል፤ ኮሚሽኑ ውሳኔ የማስተላለፍ አቅም ስለሌለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንን አይጋፋም ብለዋል።