«ሰው ሲበሳጭ ማስታወሻ እይዝ ነበር» አዲስ ዓለማየሁ

ዐዲስ ዓለማየሁ

አቶ አዲስ ዓለማየሁ ለሥራ ጉዳይ ወደ ናይሮቢ ብቅ ባለበት አጋጣሚ አግኝተን፤ እስኪ ስለ ሥራ ፈጠራ አጫውተን ብለነው ነበር። መልካም ፍቃዱ ኾኖ ይህን አጭር የትጋት ታሪኩን አካፍሎናል።

አዲስ አበባ ተወለድኩ፤ በስምንት ዓመቴ ወደ ኬንያ መጣሁ። ናይሮቢ ካደግኩ በኋላ ወደ ካናዳና አሜሪካ ለትምህርትና ለኑሮ አቀናሁ።

የሆነ ቀን "ከየት ነህ?" የማልባልበት አገር ናፈቀኝ። በ2000 በፈረንጆች ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ።

ለአምስት ዓመት በ"USAID" ተቀጥሬ ሠራሁ። የኢትዮጵያን ምርት ለአሜሪካ ማስተዋወቅ ነበር ዋና ሥራዬ። በዚያ ቆይታዬ "ኢትዮጵያ 101" ኮርስ እንደወስድኩ ነው የምቆጥረው። ለምን በለኝ፤ የግል ሴክተሩ እንዴት እንደሚሠራ፣ የመንግሥት ፖሊሲዎች ምን እንደሚመስሉ የተማርኩት ከዚያ ነው። ደግሞም ሰው አውቄበታለሁ።

ከዚያ ወጥቼም "አፍሮ ኤፍኤምን" መሠረትኩ፤ በሽርክና። ከሦስት ዓመት በፊት ደግሞ ቃና ቲቪን ከአጋሮቼ ጋር በመሆን ከፈትኩ። "251 ኮሚኒኬሽንስ" የሚባለውን የብራንዲንግ፣ የማርኬቲንግና የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን የሚሠራ ኩባንያም መሥርቻለሁ።

ደበቡ አፍሪካ ውስጥም አንድ ኩባንያ አለ፤ አፍሪካ ኮሚኒኬሽን ግሩፕ የሚባል። ከአገሬው ሸሪኮች ጋር በመሆን ነው የጀመርነው።

አራዳ ሞባይል የሚባል ከቮዳኮም ጋር ደቡብ አፍሪካ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የሲም ካርድ አገልግሎት የሚሰጥ ነው። ከዚያ ውጭም የጀማመርኳቸው አዳዲስ ቢዝነሶች አሉ።

ምን አሳካህ?

በ"251 ኮሚኒኬሽንስ" በርካታ ስኬታማ ሥራዎችን ከዓለም ባንክ፣ ከኮካኮላ፣ ከጌትስ ፋውንዴሽን፣ ከ"ገርል ኢፌክት" ጋር በመሆን ሠርተናል።

ለምሳሌ "የኛ" የሚለው መለያ ስም (Brand) ከኛ ቤት ነው የወጣው፤ "ሹም ሹፌር" የዲያጆ መለያ ስም ከኛ ቤት ነው የወጣው። 'ፍክትክት' የማልታ ጊነስ ስም ከነ መለያ ምልክቱና ከነዲዛይኑ እኛ ነን የሠራነው። "ኢትዮጵያ" የሚለው አዲሱ የቱሪዝም አርማ የኛ ሥራ ነው። "ቃና" ከስሙ ጀምሮ መለያው ሁሉ ከኛ ቤት ነው የወጣው።

"ቃና ቲቪ እንዴት ተጀመረ?"

የመጀመርያው ሐሳብ የነበረው "MTV"ን የሚመስል ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመር ነበር፤ የሙዚቃ ቻናል። ይህን ለማሳካት ደቡብ አፍሪካ ሄጄ ከ"MTV" ሰዎች ጋር አውርቻለሁ።

የፎቶው ባለመብት, Addis Alemayehou/Twitter

ስኬታማ እንደሚሆን ለምን እርግጠኛ ሆንኩ?

ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አለን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አማካይ ዕድሜ 17 ነው፤ የሙዚቃ ቻናል ተወዳጅ ሊሆን እንደሚችል አሰብኩ። ኾኖም የMTV ሰዎችን ሳናግራቸው የፕሮዳክሽን ወጪያቸው ከፍተኛ በመሆኑ በአገር ውስጥ ማስታወቂያ ይሸፈናል ብለው እንደማያምኑ ነገሩኝ።

ነገሩን በራሴ መግፋት እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡

ከኢልያስ ሹትዝ ጋር አወራንበት። አሁን የቃና ሸሪክ ነው። ጥናት እናስጠና አለኝ። 'የምን ጥናት ነው ሁለት ቲቪ ቻናል ለመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ባለበት አገር' አልኩ። ብቻ ለ2 ወራት ጥናት አደረግን።

ቤቱ ቲቪ ያለው አብዛኛው ሰው ሳተላይት አለው፤ ግን አረብኛ ነው የሚያየው፡፡ ስለዚህ በአማርኛ ተርጉመን ብናቀርብስ የሚል ነገር ተነሳ። ጣሊያን ብትሄድ የሆሊውድ ፊልም በጣሊያንኛ ነው የምታየው፤ ጀርመን ብትሄድ፣ ፈረንሳይ ብትሄድ እንደዚሁ...እኛ በምንድነው የምንለየው?

በዚህ ሂደት ውስጥ እያለን 'ሞቢ ግሩፕ'ን አገኘን።

ሞቢ ሁለት የአፍጋኒስታን ወንድማማቾች የመሠረቱት ኩባንያ ነው፤ አውስትራሊያ ያደጉና ወደ አፍጋን ተመለስው የመጀመርያን ኤፍ ኤም የጀመሩ፤ ከዚያ የማስታወቂያ ድርጅት፣ ከዚያም በአካባቢው አገራት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች. . . የጀመሩ ወንድማማቾች ናቸው። ራሴን በእነርሱ ውስጥ አየሁት።

በምትሠራው ሥራ ሁሉ ራዕይህን የሚጋራ፣ አብሮህ የሚያልም፣ አብሮህ 'ሪስክ' የሚወሰድ ከሌለ ማደግ አስቸጋሪ ነው። እኔ በዚህ ረገድ ዕድለኛ ሳልሆን አልቀርም።

ቃና ቲቪ ተመልካቹ ቀንሷል?

እውነት ነው፤ በርካታ ቻናሎች መጥተዋል። የሕዝቡ አስተያየት ተቀይሯል። ሕዝቡ በፖለቲካና በወቅታዊ ጉዳይ ተይዟል። ድሮ በነበረው ሁኔታ ሰው ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አያይም ነበር፡፡ አሁን ግን ይከታተላል። ዜናው ራሱ ድራማ ሆኗል [ሳቅ]።

ወጣቱ በሚገባው ቋንቋ ለማቅረብ እንሞክራለን። 'ሽቀላ' የምትባል ነገር ጀምረናል። የሥራ ፈጠራን ለማበረታት። ሐሳብ ይዞ በፍርሃት የተቀመጠን ወጣት ለማነቃቃት ነው።

አዲስ ስቱዲዮ ከፍተናል፤ ወደፊት ያሰብናቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ. . .

ቃና ለምን ተቃውሞ በዛበት?

የትም ዓለም ያለ ነው። አዲስ ነገር ይዘህ ስትመጣ ነባሩ አሠራር ይጋፈጥሃል። አሁን ራይድ መምጣቱ ታክሲዎችን አበሳጭቷል። እዚህ ናይሮቢ ኡበር ሲጀምር እንደዛ ነበር። የተለመደውን ነገር የሚቀይር አሰራር ይዘህ ስትመጣ ያለ ነው።

በዓለም ትልቁ ሆቴል አንድ የሆቴል ክፍል የለውም፤ ኤይአርቢኤንቢ!

በዓለም አንደኛ የታክሲ ካምፓኒ አንድ ታክሲ የለውም፤ ኡበር!

በዓለም ትልቁ ሚዲያ ካምፓኒ አንድ ጣቢያ የለውም፤ ፌስቡክ

ይቺ ናት አዲሷ ዓለማችን።

የፎቶው ባለመብት, Addis Alemayehou/Twitter

ሁሉም ሰው ነጋዴ መሆን ይችላል?

አይችልም። ትልቁ ስህተት እሱ ነው። እነማን ናቸው ቢዝነስ መጀመር የሚችሉት ካልከኝ፤ ደፋሮች እልሀለው። ደፋር መሆን አለብህ።

ብዙ ሰው የራስ ቢዝነስ ሲባል በጎ በጎውን ብቻ ነው የሚያየው። የራስህ አለቃ መሆንን፣ በፈለከው ሰዓት ቢሮ መግባት መውጣት መቻልህን...። እውነት ለመናገር ብዙ ጭንቀት አለው።

ጧት ስትነሳ ስለራስህ ቤተሰቦች ብቻ ሳይሆን ስለሁሉም ሠራተኞችህ ነው የምታስበው። ከነሱም አልፈህ ስለ ሠራተኞችህ ቤተሰቦች ታስባለህ። የሰራተኛህ ቤተሰብ በሙሉ ያንተ ቤተሰብ ነው። አንድ ሰራተኛ የ 3 እና 4 ቤተሰቡን አባል ይመግባል። ስለዚህ መቶ ሰራተኛ ካለህ ሦስት መቶ አራት መቶ ሰው ባንተ ላይ ነው። ያ ኃላፊነት ቀላል አይደለም፤ ያስጨንቃል።

ከዚያ ሌላ ካንተ ቁጥጥር ውጭ ያሉ ጉዳዮች አሉ፤ የታክስ ጉዳይ አለ፣ የውጭ ምንዛሬ ጭንቀት አለ፣ ቢሮክራሲ አለ፣ መዓት ነው ጭንቀቱ። ደመወዝ መክፈል ጭንቅ የሚሆንበትም ጊዜ አለ። ይህን ሁሉ ጭንቀት የሚችል ሰው በጣም ጥቂት ነው። ሁሉም ሰው ነጋዴ የማይሆነውም ለዚሁ ነው።

ወድቄ እነሳለሁ ማለት የሚችል ሰው መሆን አለበት። በየቀኑ ከባድ ውሳኔዎችን መወሰን የሚችል ሰው መሆን አለበት። ሁሉም ሰው ነጋዴ መሆን አይችልም። አንዳንድ ሰው ተቀጥሮ መኖር ያለበት ነው።

አፍሮ ኤፍ ኤም እንዴት ተጀመረ?

አፍሮ ኤምኤምን ለምን ጀመርክ ብትለኝ እንግሊዝኛ ጣቢያ አልነበረም። ዞር ብለህ ስታየው አፍሪካ ኅብረት አለ፤ ያ ሁሉ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አለ። ብዙ ከውጭ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያን አሉ። ወጣቱ ደግሞ እንግሊዝኛ ሙዚቃ መስማት ይፈልጋል። ያኔ ምንም አልነበረም። አሁን ናይሮቢ ስንት ናቸው? ከ80 በላይ ሬዲዮ ጣቢያ አለ።

አንዳዴ ጥናት ማስጠናትም የማያስፈልገበት ሁኔታ አለ፤ ምክንያቱም ፍላጎቱ ካለው ሕዝብ ጋር በጭራሽ አይመጣጠንም።

ቃና ሲጀምር ሦስተኛ የቲቪ ጣቢያ ነበር። ለመቶ ምናምን ሚሊዮን ሕዝብ።

ወደፊት ምን አሰብክ. . .

ብሩህ አእምሮ ያላቸው ወጣቶች አሉ። አዳዲስ የቢዝነስ ሐሳብ ያላቸው። ከዚህ በኋላ ከነዚህ ወጣቶች ጋር መሥራት እፈልጋለሁ። አብሬያቸው ለማደግ ነው የምፈልገው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ቢዝነስ መጀመር ያዋጣል?

ከሕዝቡ 73 በመቶ ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች ነው። አማካይ ዕድሜ 17 ነው። ይህ ማለት ሥራ ሲይዝ ቤት የሚገዛ፣ ምግብ የሚገዛ፣ ልብስ የሚገዛ፣ ሲያገባ ደግሞ ዳይፐር የሚገዛ ነው። የሸማችነት ጊዜ ገና ያልተጀመረበት ሕዝብ ነው። መጪው ጊዜ ለቢዝነስ ብሩህ ነው።

ወጣቶች ለምን ቢዝነስ መጀመር ይፈራሉ?

ወጣቶችን ቢሮክራሲው ይፈትናቸዋል።

አንደኛ 'ኢንተርፕረነርሺፕ' የተለየ ጭንቅላትና ሞራል ያስፈልገዋል፤ ፊት ለፊትህ ያለው ብዙ ፈተና ስለሆነ።

የትምህርት ሥርዓቱ ሥራ ፈልገን እንድነገባ እንጂ ሥራ እንድንፈጥር የተዘረጋ ሲስተም የለውም። ስለ ፈጠራ፣ ስለ ሥራ አመራር፣ ስለቢዝነስ ብዙ አያስተምሩንም።

ከቤተሰብ ይጀምራል፤ አንድ ልጅ የራሴን ሥራ ነው መሥራት የምፈልገው ሲል ምን ያህል ወላጅ ነው 'በርታ! ጎበዝ! የኔ ልጅ!' የሚለው? ዕቁብም ጥሎ እንካ ሞክር የሚል አለ? ልጄ ወደፊት ነጋዴ ነው የሚሆነው ብሎ የሚያወራው የትኛው ቤተሰብ ነው?

በቢዝነስ ሐቀኛ የሚባል መንገድ አለ?

በሕጉ መመራት ነው። ሕጉን ተከትለህ ብዙ ዕድል አለ። ከካናዳ ወደዚህ ስመጣ አባቴ የመከረኝ ነገር ነበር። "ስሜን የሚያሰድብ ነገር እንዳትሠራ። የአቶ ዓለማየሁ ልጅ እንደዚህ አደረገ እንዳታስብል ብሎኝ" ነበር።

አጭሯ መንገድ ሁሌም አለች። አጭር መንገድ ብወስድ ትግሉ አጭር ይሆንልኝ ነበር። ሆኖም ያንን አልመረጥኩም።

አጭሩን መንገድ ሰው የሚመርጠው እኩል የጀመሩ ሌሎች ሰዎች በአጭሩ ሲበለጽጉ ስለሚያይ ነው። ግን እሱ የሚተኛውና አንተ የምትተኛው እንቅልፍ አንድ አይደለም።

ቢዝነስ እንዴት ጀመርክ?

ቢዝነስ ማለት የሰውን ችግር መፍታት ማለት ነው፤ በአጭሩ። የሰው ልጅ መሬት ላይ መቀመጥ ስለሰለቸው ነው ወንበር የሠራው፤ ስለበረደው ነው የሚለበስ የሰፋው።

እያንዳንዱ ችግር የቢዝነስ ሐሳብ ነው። ችግር ስመለከት ቢዝነስ ነው የማየው። ሰው ሲበሳጭ ማስታወሻ እይዝ ነበር።

እኔ ለመጀመርያ ጊዜ ለሰው ዕቃ አቅርቤ ገንዘብ ያገኘሁት ከእናቴ ነው።

ጓሮ አትክልት እያሳደኩ ለእናቴ እሸጥላት ነበር። ከታናሽ ወንድሜ ጋር አትክልት እያሳደግን እንሸጥላት ነበር። ለሁሉም ሰው እግዜር ስጦታ ይሰጠዋል አይደል? ለኔ የሰጠኝ የምለው ሁልጊዜ አዲስ ሐሳብ ከአእምሮዬ እንዳይጠፋ ማድረጉ ነው።

ከስረህ ታውቃለህ?

ሦስት አራቴ ከስሪያለሁ፤ ገበያው የማይፈልገው አገልግሎትና ምርት አምጥቼ ከስሪያለሁ፤ አሁን ወጣቶች ላይ ቶሎ ቢዝነስ ሰርቶ 'ቪትዝ' የመግዛት ባህሪ አያለሁ። ቢዝነስ አልጋ በአልጋ አይደለም። መልፋት ይፈልጋል።

እኔ እንጀራ ጋግሬ እሸጣለሁ ካልኩኝ 30 ምጣድ አያስፈልገኝም። እቤት ባለው ምጣድ ነው መጀመር ያለብኝ። ማንም ሲጀመር ገንዘብ ኖሮት አያውቅም። "251 ኮሚኒኬሽንስን" ስንጀምር በ40ሺህ ብር ገደማ ነው።

ወጣቱ ያስፈራሃል?

ይህ ሁሉ ወጣት ገበያ ነው። በዚያ መጠን አስፈሪ ነው። ወጣት ሆነህ፣ ትምህርትህን ጨርሰህ፣ ዲግሪ ይዘህ ሥራ ማጣት ተስፋ አስቆራጭ ነው። ይሄን በሚሊዮን ስታባዘው ደግሞ ለአገሩ የሚያስፈራ ሁኔታ ነው።

ከሁሉም በላይ ሥራ የሚፈጥሩ ኢንዱስትሪዎች ላይ ማተኮር አለብን። እዚህ ኬንያ የመጣሁትም በአይሲቲ በኩል እንዴት ለወጣቱ ሥራ መፍጠር ይቻላል በሚለው ላይ ለመነጋገር ነው። ዓለም ወደዚያ እየሄደች ነው።

ቴሌኮም ሲስፋፋ ብዙ ዕድል ይፈጥራል። አይቲ ኩባንያዎች ያንን ነው እየጠበቁ ያሉት። ብዙ ወጣቶች ላፕቶፕ ይዘው ፈጣን ኢንተርኔት የሚያቀርብላቸውን ብቻ እየጠበቁ ነው። ያን ካገኙ ከዓለም ጋር ተገናኝተው ሥራ መሥራት ይችላሉ። ሌላ ምንም አይፈልጉም። ላፕቶፓቸው ቢሯቸው ይሆናል።

ፋይናንስ መቅረብ አለበት። ኢትዮጵያ አንዱ ትልቁ ችግር ዕውቀትና ገንዘብ አለመገናኘታቸው ነው። ዕውቀት ያለው ገንዘብ የለውም፤ ገንዘብ ያለው ሐሳብ የለውም።

በየቢሮው የቢዝነስ ፕላን በጓሮ የሚሠረቀው እኮ ለዚህ ነው። ብር ያለው ሐሳብ የሌለው ብዙ ነው። ብዙ ሰው ፎቅ የሚሠራው ገንዘቡ ባንክ ከሚቀመጥ አንድ ነገር ልሥራበት በሚል ነው። ወጣቶች ላይ መዋል አለበት። በመንግሥት በኩልም ማበረታቻ መኖር አለበት።

በሌላ ሰው ዕውቀትና በሌላ ሰው ጉልበት ገንዘብ መሥራት ማለት ቀላል ነገር አይደለም። ሁሉም ትልልቅ ቢዝነሶች የተፈጠሩት በዚህ መንገድ ነው። ፌስቡክ የተፈጠረው በዚህ መንገድ ነው። ሐሳብ ካለው ወጣት ጋር በገንዘቤ ገንዘብ መሥራት የማምንበት ነገር ነው።

ሌላው ቢዝነስ ለመሥራት ውጣ ውረዱ መቀነስ አለበት። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ቢዝነስ ለመክፈት አይደለም ለመዝጋት እንኳ ቀላል አይደለም።

ከናይሮቢና ከአዲስ አበባ ማን ይበልጣል?

ጥለውን ሄደዋል። እኛን የገደለን የደርግ 17 ዓመት ነው። ቢዝነስ ቆመ። የነበረው ተወረሰበት። የተማረው ተገደለ፤ ጥሎ ሄደ። ከዚያ 'ሀ' ብለን ነው የጀመርነው። ባለፈው 27 ዓመትም ቢሆን ነጋዴ እንደ ሌባ የሚታይበት ሁኔታ ነው የነበረው። ነጋዴ ከሆንክ ልትበላ ልትዘርፍ የወሰንክ ተደርጎ ነበር የሚታየው።

'ነጋዴ ሀብት ይፈጥራል፤ ሥራ ይፈጥራል፤ ነጋዴ አጋር ነው' ብሎ የሚያስብ መንግሥት አልነበረም፤ አሁን ግን ተስፋ አለ።

እኛ በአገራችን እስከዚህም ነን። እስከ 40 ዓመታችን ቤተሰባችን ጋር ስለምንኖር ይመስለኛል። በአገራችን ስንኖር ሥራ ላይ ብዙም አይደለንም። ከአገር ስንወጣ ነብር ነን። ማንም አይችለንም። እንደኛ አራዳ ነጋዴ በዓለም የለም።

ነገሮች መልክ ከያዙ መንግሥት የግሉን ዘርፍ ከደገፈ አካባቢውን እንደምንቆጣጠር ምንም ጥርጥር የለኝም።