የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር መልቀቂያ አስገቡ

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ጀነራል ጂም ማቲስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

መልቀቂያቸውን ያስገቡት ጂም ማቲስ ከሁለት ወራት በኋላ ስራ ያቆማሉ

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ጂም ማቲስ ከሃላፊነታቸው ለመልቀቅ ደብዳቤ አስገቡ።

መከላከያ ሚኒስትሩ መልቀቂያ ያስገቡት ትራምፕ አሜሪካ ሙሉ በሙሉ ጦሯን ከሶሪያ እንደምታስወጣ ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።

ይህን የትራምፕ ውሳኔን ብዙዎች ያልተቀበሉት ሲሆን ጀነራል ማቲስም ምንም እንኳ በግልፅ ለሥራ መልቀቅ ምክንያታቸው ይህ መሆኑን ባይጠቅሱም በትራምፕና በእሳቸው መካከል የቋም ልዩነት መፈጠሩን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጀነራል ማቲስ ሌሎች አገራትን አጋር በማድረግና ወታደራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ በማድረግ ትልቅ ሚና መጫወታቸውንም ገልፀዋል።

ትራምፕ ጀነራል ማቲስን የሚተካ ሰው በአጭር ጊዜ እንደሚሾም ቢናገሩም ማንነቱን ከመግለፅ ግን ተቆጥበዋል።

ጀነራሉ በሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸው ላይ ከትራምፕ ጋር አጋር አገራትን በአክብሮት ስለመያዝና የአሜሪካ የጦር ኃይል አጠቃቀም ላይ ልዩናት እንደተፈጠረ በመጥቀስ ፕሬዝዳንቱ ከእርሳቸው ጋር የሚቀራረብ አመለካከት ያለውን የመከላከያ ሚንስትር መምረጥ ተገቢ እንደሆነ አስፍረዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩን መልቀቅ በተመለከተ የሪፐብሊካኑ ሴናተር ሊንዲሲ ግራሃም "ጀነራል ማቲስ ለትራምፕ አስተዳደርና ለአገራችን በሰጡት አገልግሎት ሊኮሩ ይገባል" ብለዋል።

ለአስርታት አክራሪ እስልምናን በመዋጋትና ወሳኝ ወታደራዊ ምክር በመስጠት ትልቅ ሚና መጫወታቸውንም ገልፀዋል።

በተቃራኒው የዲሞክራቲኩ ሴናተር ማርክ ዋርነር የጀነራሉ ስልጣን የመልቀቅ ዜናን "አስደንጋጭ" ብለውታል። ይህን ያሉት ውጥንቅተጡ በወጣው የትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ጀነራሉ የመረጋጋት ማዕከል የነበሩ በመሆኑ ነው።

በተያያዘ ዜና ከሶሪያ በተጨማሪ አሜሪካ ሰባት ሺህ የሚሆኑ ወታደሮቿን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከአፍጋኒስታንም ልታስወጣ መሆኗም ተሰምቷል።

ይህ መረጃ የወጣው አሜሪካ ጦሯን ሙሉ በሙሉ ከሶሪያ እንደምታስወጣ ትራምፕ ከገለፁ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

የአሜሪካን ጦር ከአፍጋኒስታን ስለማስወጣት አስፈላጊነት ትራምፕ ከመመረጣቸው በፊት በግልፅ ሲናገሩ የቆዩ ቢሆንም አገሪቱ ዳግም የታሊባን እጅ ውስጥ እንዳትወድቅ የተወሰነ ሰራዊታቸው በአፍጋኒስታን መቆየትን አስፈላጊነት ላይ አስምረው ነበር።

ምንም እንኳ በአገሪቱ የመከላከያ ባለስልጣናት ባይፀድቅም የጦር ሃይሉን ቁጥር የመቀነስ ፍላጎት እንዳለም ተገልጿል።

እአአ 2001 ከተፈፀመው የመስከረም 11 የአሜሪካ የሽብር ጥቃት በኋላ አሜሪካ ጦሯን በአፍጋኒስታን አሰማርታለች። የአሜሪካ ጦር ኃይል በአፍጋኒስታን ያደረገው ቆይታ ረዥሙ የአገሪቱ የጦርነት ታሪክ ነው።

በጊዜው አፍጋኒስታንን ተቆጣጥሮ የነበረው ታሊባን ለመስከረም 11 የአሜሪካ ጥቃት ሃላፊነት የወሰደውን የአልቃይዳ መሪ ኦሳማ ቢላደንን አሳልፌ አልሰጥም በማለቱ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ በአፍጋኒስታን ጦርነት መክፈታቸው የሚታወስ ነው።

ከዚያ በኋላ የታሊባን ሃይል ቢዳከምም አገሪቱን ወደ መረጋጋት ለመመለስ የአሜሪካ ጦር በአፍጋኒስታን እንዲቆይ ሆኗል።