አሜሪካ ሁለት ቻይናዊያን 'ኢንተርኔት በርባሪዎችን' ከሰሰች

FBI wanted poster

የፎቶው ባለመብት, FBI

የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር የምዕራቡ አገራት ኮምፒተር ኔትወርኮችን በርብረዋል (ሃክ) አድርገዋል ያላቸውን ሁለት ቻይናዊያን ከሰሰ።

ግለሰቦቹ 'ሃክ' አድርገዋል የተባለው የግል ኩባንያዎችን እንዲሁም የመንግስት ኤጀንሲዎች ኮምፒውተሮችን ነው።

አሜሪካና ካናዳ ከንግድ ጋር በተያያዘ ከነሱ ጋር ያደረገችውን ስምምነት በመጣስ ስለላ እያደረገች ነው ሲሉም ቻይናን ወንጅለዋል።

የቀረበባቸው ክስ እንደሚያመለክተው ዙ ሁአ እና ዣንግ ሲሎንግ የተባሉት ግለሰቦች ህዋዌ ሄታይ ለተባለ ኩባንያ ሰርተዋል። ይህ ኩባንያ የሚንቀሰቀሰው ደግሞ ከቻይና የደህንነት ተቋም ጋር እንደነበርም በክሱ ተመልክቷል።

የአሜሪካው የምርመራ ቢሮ ኤፍ ቢ አይ እንዳስታወቀው ግለሰቦቹ እአአ ከ2006 እስከ 2018 የኮምፒውተር ኔትዎርኮችን በመጥለፍ የአእምሮ መብት ጥበቃ ያላቸውን የፈጠራ ስራዎች፣ ምስጢራዊ የንግድና የቴክኖሎጂ መረጃዎችን ሰርቀዋል።

ግለሰቦቹ የአሜሪካ ባህር ሃይል ኮምፒውተር ኔትወርክን በመጥለፍ በማድረግም ከመቶ ሺህ የሚበልጡ የባህር ሃይሉ አባላትን የግል መረጃም ሰርቀዋል ብሏል ኤፍ ቢ አይ።

የኤፍ ቢ አይ ዳይሬክተር ክርስቶፈር ዋሪ ሁለቱ ግለሰቦች ከአሜሪካ ውጭ በመሆናቸው ለአሜሪካ ፍትህ ስርዓት ተደራሽ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።