በእንግሊዝ የሁለት ዓመቱ ታዳጊ በተፈጠረ የህክምና ስህተት መከነ

የሁለት ዓመቱ ህፃን

የሁለት ዓመቱ ህፃን የዘር ፍሬውን ለማስተካከል በተደረገ ህክምና ወቅት ባጋጠመ ስህተት መምከኑን ቤተሰቦቹ ተናግረዋል።

ህፃኑ ያለቦታው የተገኘ የዘር ፍሬውን ለማዛወር ወደ ብሪስቶል ሮያል የህፃናት ሆስፒታል የተላከው በዚህ ሳምንት መጀመርያ ነበር።

የህፃኑ አንዱ የዘር ፍሬ ጤናማ የነበረ ሲሆን አንደኛው ግን ያለቦታው ሆኖ ነበር የተወለደው። የህፃኑ አባት እንደሚሉት ይህንኑ ለማስተካከል በተደረገ ቀዶ ሕክምና ባጋጠመ ስህተት ጤናማውም ዘር እንዳያመነጭ ሆኗል።

የህፃኑን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ስማቸው ያልተጠቀሰው አባት የህፃኑ የዘር ፍሬ ያለ ቦታው እንደነበር ያወቁት በአጋጣሚ በተደረገ ቀላል ምርመራ ነበር።

ከዚያም ባለፈው ሰኞ ህፃኑ ለተሻለ ህክምና ወደ ብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ተልኮ ቀዶ ሕክምና ሊደረግለት ቀጠሮ እንደተያዘለት ይናገራሉ።

ወላጆቹ እንደሚሉት ቀዶ ጥገናው በጣም ቀላልና ለአደጋ የሚያጋልጠው አልነበረም፤ በ30 ደቂቃ እንደሚጠናቀቅም ያውቁ ነበር።

" ጠበቅን... ጠበቅን... ከ2 ሰዓት በላይ ከቆየን በኋላ የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጂ፣ ሐኪሙና አማካሪው ወደ እኛ መጡ፤ ያኔ አንዳች መጥፎ ዜና እንዳለ ተረዳን" ይላሉ።

"በድንጋጤ ተብረከረኩ፤ "ወደ ቢሮ ተጠርተው ሁኔታዎች እንደታሰበው እንዳልሆነና ቀዶ ህክምናው ውጤታማ እንዳልነበር ተነገራቸው።

ህፃኑ የዘር ፍሬ ማመንጨት አይችልም የሚለው መርዶም ተነገራቸው።

" በጣም የሚያስጨንቅ ነው ፤ በጣም አስቀያሚ አጋጣሚ ነበር፤ ለቀላል ቀዶ ህክምና ሁሉንም ነገር አመከኑት " ሲሉ አባቱ ሃዘናቸውን ይገልፃሉ።

የልጃቸው የወደፊት ህይወትም በማይታመንና በሚያሳዝን መልኩ መለወጡን ይናገራሉ።

የህፃኑ እናት በበኩላቸው ሐኪሞቹ የሰሩት ስህተት በጣም ዘግናኝ ነው ብለዋል። "ልቤን ሰብረውታል፤ የእርሱንም የወደፊት ሕይወት አጨልመውታል" ሲሉ ልባቸው አንደተሰበረ ተናግረዋል።

" የተሰማኝን መግለፅ አልችልም ፤ምንም ቃላት የለኝም ፤ እንባም ቢሆን.... የሆነ ተአምር እንዲፈጠር ነው ተስፋ ያደረግነው፤ በቃ ያለን ተስፋ ይሄው ነው" ብለዋል።

ሆስፒታሉ በሰጠው መግለጫ ላይ የሆስፒታሉ ቃል አቀባይ እንደገለፁት ሰራተኞቹ ምን እንደተፈጠረ ባወቁ ጊዜ ወላጆቹን አስጠርቶ ይቅርታ ጠይቋል።

ሁኔታውን ለማጣራት ምርመራ መጀመሩን ገልፀው እየተከታተሉ ለቤተሰቦቹ እንደሚያስታውቁም ገልፀዋል።

በኤን ኤች ኤስ ሪፖርት ከ100 ህፃናት አንዱ ህክምና ካላደረገ በስተቀር ያለቦታው ከተቀመጠ የዘር ፍሬ ጋር ይኖራል።