የላውሮ ግምት፡ ማንቸስተር ዩናይትድ በአዲሱ አሰልጣኝ ስር ውጤታማ ይሆናል?

Ole Gunnar Solskjaer

ማንቸስተር ዩናትዶች በጊዜያዊው አሰልጣኝ ኦሌ ጉናር ሶልሻር ሥር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ለማድረግ ወደ ካርዲፍ ያቀናሉ። ምን ዓይነት ውጤት ያስመዘግባሉ?

የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ማርክ ላውረንሰን "ከዚህ ቀደም ከነበረው ማንቸስተር በእጅጉ የተለየ ቡድን የምንመለከት ይሆናል። በጆዜ ሞውሪንሆ ስር ውጤታማ ያልነበሩት ተጫዋቾች ትኩረት ስለሚደረግባቸው ያላቸውን ብቃት ለማሳየት ይጫወታሉ" ብሏል።

"አንድ ሁለቱ ራሳቸውን በመመልከት ውጤታማ ካልሆኑበት ውድድር ዓመት በተቃራኒ መጫወት አለባቸው።"

ላውሮ ይህንን ጨምሮ የሌሎች የፕሪሚየር ሊጉን ጨዋታዎች ግምት አስቀምጧል።

የላውሮ ግምቶች

አርብ

ዎልቭስ ከሊቨርፑል

ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ያሸነፉት ዎልቭሶች ይህን የድል ጉዞዋቸውን በዚህ ሳምንት የሚቀጥሉ አይመስለኝም።

የርገን ክሎፕ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ቡድናቸውን ቢቀያይሩም ውጤታማ ከመሆን አላገዳቸውም።

የላውሮ ግምት: 1-2

ቅዳሜ

አርሴናል ከበርንሌይ

አርሴናል በሊጉ በሳውዛሃምፕተን ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ አሰልጣኝ ኡናይ ኤምሬ ማሸነፍን ብቻ አስበው ነው የሚጫወቱት።

ካርሌቶች ካለፈው ሳምንት ሽንፈት በኋላ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ገብተዋል።

የላውሮ ግምት: 2-0

በርንማውዝ ከብራይተን

በርንማውዞች መጥፎ ጨዋታ ባያሳዩም ካለፉት ስምንት ጨዋታዎች በሳባቱ ሽንፈት አስተናግደዋል።

ብራይተንን ግን እንደሚያሸንፉ እገምታለሁ። በተለይ ደግሞ ብራይተኖች ከሜዳቸው ውጭ ውጤታማ አለመሆናቸው ጨዋታውን ከባድ ያደርግባቸዋል።

የላውሮ ግምት: 2-0

ቼልሲ ከሌስተር

ሌስተሮች አጥቂያቸው ቫርዲ ሲጫወት ጠንካራ ቢሆኑም በዚህ ጨዋታ ከጉዳቱ አገግሞ ቢሰለፍም ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም።

ቼልሲዎች ከዎልቭስ ሽንፈት በኋላ በውጤታማነት መቀጠላቸውን የሚያረጋግጡበት ጨዋታ ነው።

የላውሮ ግምት: 2-0

ሃደርስፊልድ ከሳውዝሃምፕተን

ሁለቱ ቡድኖች የተቀራራበ ውጤት ቢኖራቸውም ሃደርስፊልዶች ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ተሸንፈዋል።

ጨዋታውን ያሸንፋሉ ብዬ ባልጠብቅም በአቻ ውጤት ግን ያጠናቅቃሉ።

የላውሮ ግምት: 1-1

ማንቸስትር ሲቲ ከክሪስታል ፓላስ

ክሪስታል ፓላሶች በጣም አስፈላጊ የሆነ ድል ባለፈው ሳምንት ሌስተር ላይ ቢያስመዘግቡም ይህንን ግን ኤቲሃድ ስታዲየም ላይ ይደግሙታል ብዬ አላስብም።

ፔፕ ጉዋርዲዮላ ተጫዋቾችን ቢያሳርፍ እንኳን አጨዋወታቸው አይቀየርም። ጥሩው ዜና ደግሞ ኬቪን ደ ብሩይን እና ሰርጂዮ አጉዌሮ ከጉዳት መመለሳቸው ነው።

የላውሮ ግምት: 3-0

ኒውካስል ከፉልሃም

ፉልሃሞች ባለፈው ሳምንት ከዌስት ሃም ጋር የነበራቸውን ዕድል ካለመጠቀማቸውም በላይ ተሸንፈዋል።

ኒውካስሎች አሁንም የመውረድ ስጋት ያለባቸው እና በሜዳቸው ውጤት ለማስመዝገብ የሚቸገሩ ቢሆንም ጨዋታውን እንደሚያሸንፉ እገምታለሁ።

የላውሮ ግምት: 2-0

ዌስት ሃም ከዋትፎርድ

ዌስት ሃሞች ጥሩ በመንቀሳቀስ አራት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችለዋል። ውድድሩ ሲጀምር ችግር የነበረበት የተከላካይ መስመራቸው አሁን ቅርጽ የያዘ ይመስላል።

ይህን ጨዋታ መገመት ከባድ ነው። ባለፉት ሁለት ሳምንታት በዋትፎርዶች አጨዋወት ተደምምያለሁ።

የላውሮ ግምት: 0-2

ካርዲፍ ከማንቸስተር ዩናይትድ

ካርዲፎች በሜዳቸው ካደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች አራቱን በድል ቢያጠናቅቁም ይኼኛው ግን የተለየ ነው።

አዲስ አሰልጣኝ ሲመጣ ሁሉም ጠጫዋቾች ያላቸውን አቅም ማሳት ይፈልጋሉ። የኦሌ ጉናር ሶልሻር ይህን ጨዋታ በቀላሉ የሚያሸንፍ ሲሆን ቡድኑ ቀጣይ እርምጃ በጉጉት የሚጠበቅ ነው።

የላውሮ ግምት: 0-2

እሑድ

ኤቨርተን ከቶተንሃም

የቶተንሃሙ አሰልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቸቲኖ በክረምት የማንቸስትር ዩናትድ አሰልጣኝ እንደሚሆኑ መነገር መጀመሩ ቡድኑ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል።

ባለፉት ጥቂት ጊዜያት ቶተንሃሞች ጉዲሰን ፖርክ ላይ ጥሩ ውጤት ነበራቸው። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አልተሸነፉም። ዘንድሮ ኤቨርተኖችም በሜዳቸው ውጤታማ ሲሆኑ በጨዋታው የሚሸነፉ አይመስለኝም።

የላውሮ ግምት: 1-1