'የእሳተ ገሞራ ቱሪዝም'፡ አፍቃሬ እሳተ ገሞራዎች

Volcano

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሁኑ ወቅት ዓለም ላይ እየፈነዳ ያለ እሳተ ገሞራን ቀረብ ብለው የመመልከት፣ የፍንዳታ ድምፆቹን የመስማት ከዚህም አልፎ አካባቢው ላይ ተገኝተው ሙቀቱ እንዲሰማቸው የሚፈልጉ አፍቃሬ እሳተ ገሞራ ጎብኚዎች እየበዙ መሆኑ እየተነገረ ነው።

ቢያስደነግጥም እሳተ ገሞራ ያለባቸውን አካባቢዎች በማዘውተር የሚደሰቱት እነዚህ ቱሪስቶች ራሳቸውንም አደጋ ላይ እየጣሉ ፤ የድንገተኛ ህክምና እርዳታ አገልግሎት ላይም ችግር እያስከተሉ ነው እየተባለ ነው።

የሚፈነዳ እሳተ ገሞራ ለማየት ጎብኚዎች የሚገሰግሱባት አይስላንድ በነገሩ በጣም ከተቸገሩ አገራት የምትጠቀስ ናት።

በአገሪቱ በመፈንዳት ላይ ያሉ እሳተ ገሞራዎችን በቅርበት የመመልከት ፍላጎት በጎብኚዎች ዘንድ ከፍተኛ ነው። ጎብኚዎቹ በዚህ ምን ያህል ራሳቸውን ለአደጋ እያጋለጡ እንዳሉ እንደማይረዱም ተገልጿል።

በካምብሪጅ የመልክአ ምድር ማህበረሰብ የታተመ አንድ ጥናት የዚህ አይነቱ ቱሪዝም የአገራት የነፍስ አድን ስራ ላይ ትልቅ ጫና እንደሚፈጥር ያሳያል።

በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት ዶ/ር ዶኖቫን እንደሚሉት እንደዚያ ያለ አስጨናቂ ቦታ ላይ በመገኘት የሚደሰቱ ሰዎች በሌሎች መሰል ነገሮችም ይሳባሉ።

"ጋዙን መተንፈስና ምድር የምታወጣውን ድምፅ መስማት ያሻቸዋል፤ የመሬትን ድምፅ በደንብ ለመስማት መቅረብ ይፈልጋሉ" ይላሉ።

የዚህ ዓይነቱ ፍላጎታቸው አይሎ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ፈንድተው ያልጨረሱ እሳተ ገሞራዎችን እያደኑ የሚጎበኙ አፍቃሬ እሳተ ጎመራዎችም (ቮልካኖፋይል) እንዳሉ ዶ/ር ዶኖቫን ይናገራሉ።

እነዚህ አፍቃሬ እሳተ ገሞራዎች ስሜታቸው አሸንፏቸው ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ችግር የዘነጉ መሆናቸውን ዶክተሯ ያስረዳሉ።

በፍንቃይ አለቶች ወይም በእሳት ውርዋሪ መመታት እንዲሁም መርዛማ ጋዞችም ሊኖሩ ይችላሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ጎብኚዎቹ ይበልጥ የማይረዱት የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች በፍጥነት ተቀይረው እንደ ጎርፍ ያለ አደጋ ሊመጣም ይችላል።

በእንዲህ ያለው አጋጣሚ ጎብኚዎችን መታደግ የድንገተኛ አደጋ ተቋማት ላይ ከባድ ጫና ሲፈጥር የጎብኚዎች ደህንነትም አደጋ ውስጥ ይወድቃል።

በአይስላንድ በአንድ ወቅት የደህንነት ቁጥጥርን ለማምለጥ ቱሪስቶች በሄሊኮፕተር ምሽት ላይ እሳተ ገሞራ ሳይት ላይ አርፈዋል።

እአአ 2010 ላይም የቮልካኖ ግግር አቋርጠው ወደ ፍንዳታው የሄዱ ሁለት ጎብኚዎች ሞተዋል።

የእሳተ ገሞራ ቱሪዝም ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ትልቅ እርምጃ ቢሆንም አደገኛ ጎንም እንዳለው ተገጿል።