አርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ፈርሶ አዲስ ፓርቲ ሊመሰረት ነው

የፎቶው ባለመብት, AG7
አርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ፈርሶ አዲስ ፓርቲ ሊመሰረት መሆኑን የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የአዲስ አበባ ጊዜያዊ አደራጅ ምክትል ሰብሳቢ አቶ እዮብ መሳፍንት ለቢቢሲ ገልፀዋል።
አዲሱ ፓርቲ በዋናነት የዜግነት ፖለቲካንና ማህበራዊ ፍትህን ማዕከል ያደረገ እንደሚሆን አስረድተዋል።
በሀገሪቱ ውስጥ የሰፈነውን የብሔር ፓለቲካ ወይም ዘውገኝነትን በመተው በግለሰብ ላይ የተመሰረተ መብትንም የሚያስቀድም ይሆናል ብለዋል።
"በዜግነት ላይ የተመሰረተና አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ብቻ በእኩልነት የሚታይበት ሀገር ለመመስረት እንታገላለን። የምንመሰርተው ፓርቲ ርዕዮተ አለምም እሱን ማእከል ያደረገ ይሆናል" ብለዋል።
በሀገሪቱ ላይ በብሔር የተከፋፈለ ፖለቲካና ህዝብ ከመሆኑ አንፃር በግለሰብ በዜግነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካን እንዴት ማምጣት ይቻላል የሚል ጥያቄ ከቢቢሲ የቀረበላቸው አቶ እዮብ ስትራቴጂዎችንም እየቀየሱ መሆኑንም አስረድተዋል።
አርበኞች ግንቦት 7 በንቅናቄነት ሲታገል የነበረ ሲሆን የራሱ መርሆች ቢኖሩትም ፓርቲ ባለመሆኑ የራሱ ፕሮግራም እንዳልነበረው አስረድተዋል።
አዲሱ ፓርቲ ከሌላው ጊዜ ለየት ባለ መልኩ ከታች ወደላይ የሚደራጅ መሆኑን የሚናገሩት አቶ እዮብ የሚኖረው አደረጃጀት ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ 547 የምርጫ ወረዳዎችንና በአዲስ አበባ ያለውን 23 ወረዳዎችን የሚያካትት የፓርቲ የነዋሪዎች መዋቅር ይመሰረታል ብለዋል።
ፓርቲው ያስፈልጋሉ የሚላቸውን ፖሊሲዎችን በማርቀቅ ላይ ሲሆኑ አመራሮችን መምረጥ እንዲሁም ስያሜውን በተመለከተ በጠቅላላ ጉባኤው ወይም በአባላት የሚወሰን መሆኑንም አቶ እዮብ ይናገራሉ።
የአዲሱ ፓርቲ አመሰራረትንም አስመልክቶ አርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ አመራሮች ህዝቡን ለማወያየት በአዲስ አበባ በመጪው ቅዳሜና እሁድ ውይይት ጠርተዋል።
ከአዲሱ ፓርቲ በተጨማሪ አርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ አመራሮች ወደ ሃገር ውስጥ ሲገቡ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋናን ለማቅረብና እንዲሁም ከህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያለመ መሆኑንም አቶ እዮብ ይናገራሉ።