የኦነግ እና የመንግሥት እሰጣገባ

አለማየሁ እጅጉ

የፎቶው ባለመብት, EBC

ባለፉት ዓመታት በከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሲናጥ የከረመው የኦሮሚያ ክልል፤ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ ለተወሰነ ጊዜ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖበት ቆይቷል።

ይሁን እንጂ በምዕራብ ኦሮሚያ የተከሰቱት ግጭቶች፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ድንበር ላይ የተፈጸሙት ግድያዎች እና መፈናቀል፣ በደቡብ ኦሮሚያ ሞያሌ ከተማ እና አጎራባች ቀበሌዎች በይዞታ ይገባኛል የተፈጠረው ግጭት፣ ይህንንም ተከትሎ ግድያ እና መፈናቀልን ይቁም በማለት በተለያዩ የክልሉ ከተሞችና ዩኒቨርሲቲዎች የተደረጉት የተቃውሞ ሰልፎች የክልሉን ሰላም እና መረጋጋት አደፍርሰውት ቆይተዋል።

በሞያሌ አካባቢ በኦሮሞ እና ገሪ መካከል ለሚከሰቱት ግጭቶች በሁለቱም ወገን ያሉት ለግጭቾቹ መንስዔ አንዱ አንዱን ተጠያቂ ያደርጋሉ። በኦሮሞ በኩል ያሉት የሞያሌ ድንበር ተሻግረው በከባድ መሳሪያ ህዝቡ ላይ ጥቃት የሚፈጽሙት የሶማሌ ታጣቂዎች ናቸው ይላሉ። በሶማሌ ወገን ያሉት በበኩላቸው ለግጭቱ፣ ለሞትና መፈናቀሉ የኦሮሞ ታጣቂዎች ላይ ጣታቸውን ይቀስራሉ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ድንበር ላይ ለሚከሰቱት ግጭቶች ደግሞ መንግሥት ''የታጠቁ ኃይሎች'' የሚላቸውን አካላት ተጠያቂ ያደርጋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በምዕራብ ኦሮሚያ ከተከሰቱት አለመረጋጋቶች እና ግጭቶች ጋር በዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ስም አብሮ በስፋት ይነሳል።

በወረሃ ጥቅምት አጋማሽ ላይ ቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ ውስጥ በመንግሥት እና በኦነግ ሠራዊት አባላት መካከል ግጭት መከሰቱን ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።

ምንም እንኳ የቄለም ወለጋ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ታመነ ኃይሉ በኦነግ እና በመንግሥት ኃይል መካከል የተደረገ ምንም አይነት ግጭት የለም ያሉ ቢሆንም የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ቄለም በምትባል አነስተኛ ከተማ በሃገር መከላከያ ሠራዊት አባላት እና በኦነግ ታጣቂዎች መካከል ግጭት ስለመኖሩ አረጋግጠዋል።

የደምቢዶሎ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ክብረት ዋቅጋሪም ግጭት ነበረ በተባለበት ምሽት ሦስት የፖሊስ አባላት በቦንብ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታላቸው እንደመጡ ተናግረው ነበር።

በወቅቱ የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግሥት እንዲሁም የኦነግ አመራሮች በክስተቱ ላይ አስተያየታቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ከጥቂት ሳምንታትም በፊት በምዕራቡ ክፍል ያጋጠመን የጸጥታ መደፍረስ በሽምግልና ለመፍታት የሃገር ሽማግሌዎች ኦነግን እና መንግሥትን ለማግባባት ወደ ስፍራው አቅንተው ነበር። ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ ካቀኑት ሽማግሌዎች መካከል አንዱ የነበሩት ሼክ ሐጂ ከአካባቢው ህዝብ እና በስፍራው ከሚገኙ የኦነግ ወታደሮች እና አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

''ወደ ሃገር ውስጥ ሳንገባ በመሪዎቻችን እና በክልሉ ፕሬዚዳንት መካከል የተደረሰው ስምምነት ለምን ተግባራዊ አልተደረገም?'' የሚል ጥያቄ በኦነግ ወታሮች መነሳቱን ሼክ ሐጂ ከሳምንታት በፊት ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

ኦነግ እና መንግሥት አሥመራ ላይ የደረሱት ስምምነት ምን ነበር?

ከጥቂት ወራት በፊት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ እና በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ የሚመራ ልዑክ ወደ ኤርትራ ተጉዙ ከኦነግ ጋር ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል።

መንግሥት እና ኦነግ የደረሱበት ዝርዝር ስምምነት ይፋ ባይሆንም ኦነግ ሰላማዊ ትግልን ለማካሄድ እና ሠራዊቱም በየደረጃው በመንግሥት ሰላም አስከባሪ ኃይል ወይም በሌሎች መስኮች ውስጥ እንዲቀላቀል ከስምምነት መድረሳቸው ተነግሯል።

በወቅቱ የኦነግ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ቶሌራ አደባ ''. . . በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦነግ መካከል የነበረው ጦርነት እንዲያበቃ እና ኦነግ በሰላማዊ መንገድ ሃገር ውስጥ ገብቶ እንዲሠራ ከስምምነት ላይ ደርሰናል'' ሲሉ ተናግረው ነበር።

በኦነግ እና በመንግሥት መካከል የተፈጠረው ልዩነት ምንድነው?

''መንግሥት እና ኦነግ የደረሱበትን ስምምነት ለማስፈጸም በመንግሥት በኩል ቅድመ ዝግጅቱ ከተጠናቀቀ ሰነባብቷል፤ ጉዳዩን እያጓተተ የሚገኘው ኦነግ ነው'' የሚሉት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር አለማየሁ እጅጉ ናቸው።

በመንግሥት እና በኦነግ መካከል የተደረሰውን ስምምነት ለማስፈጻም በሁለቱም ወገን ተወካዮች የተዋቀረ ኮሚቴ አለ። የዚህ ኮሚቴ አባል የሆኑት ኮሚሽነር አለማየሁ፤ የኮሚቴው አባል የሆኑ የኦነግ ተወካዮች 'በተደጋጋሚ ስምምነቱን ከማስፈጸማችን በፊት ከሠራዊታችን ጋር የምንወያይባቸው ጉዳዮች አሉ' በማለት ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ ጉዳዩን ያጓተቱት እነሱ ናቸው እንጂ መንግሥት አይደለም በማለት ለስምምነቱ ተፈጻሚነት መዘግየት ኦነግን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

''የመንግሥት ተነሳሽነት እንደ ከዚህ ቀደሙ አይደለም'' በማለት ለቢቢሲ የተናገሩት ኦነግን በመወከል የዚሁ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሚካኤል ቦረና ናቸው።

እንደ ኮሚሽነር አለማየሁ ሁሉ አቶ ሚካኤልም "መንግሥት ጉዳዩን እያጓተተ ስለሆነ በተግባር ምንም ጠብ ያለ ነገር የለም" ይላሉ።

አቶ ሚካኤል ጨምረውም የኦነግ ሠራዊት አባላት ታሪካዊ እና በሥነ-ምግባሩ የተመሰከረለት ስለሆነ ሥራዊቱን የሚመጥን ስፍራ ሊያገኝ ይገባል ይላሉ።

አቶ አለማየሁ ለዚህ አስተያየት ምላሽ ሲሰጡ ኦነግ ሠራዊቱን ወደ አንድ ካምፓ ሳይሰበስብ፣ በስልጠና ወቅትም የእያንዳንዱ ሠራዊት አባል ማንነት እና አቅም ሳይፈተሽ፤ ለሠራዊቱ የሚመጥነው ስፍራ ይህ ነው ማለት አይቻልም ይላሉ።

ሌላው በመንግሥት እና በኦነግ መካከል ቅራኔን የፈጠረው መንግሥት ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ የሃገር መከላከያ ኃይልን ማሰማራቱ ነው።

በሁለቱ ወገን የተቋቋመው ኮሚቴ ሥራውን በአግባቡ እንዳያከናውን መንግሥት መከላከያ ሥራዊት አሰማራብን በማለት ኦነግ ይከሳል።

ኮሚሽነር አለማየሁ በበኩላቸው መንግሥት የጸጥታ ኃይልን የሚያሰማራው የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ ነው ለዚህም ደግሞ መንግሥት ፍቃድ መጠየቅ አይጠበቅበትም ይላሉ።

የኦዲፒ መግለጫ

የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ታህሳስ 11 በወቅታዊ ጎዳዮች ላይ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ መግለጫ አውጥቷል።

ክልሉን የሚያስተዳድረው ፓርቲ ''በህዝብ ትግል የተቀዳጀነው ድል በጠላት ሴራ ለሰከንድም ቢሆን አይደናቀፍም፤ ወደ ኋላም አይመለስም'' በሚል ርዕስ ጠንከር ያለ መግለጫ አውጥቷል።

በክልላችን ላይ በተሸረበው ሴራ በምዕራብ ኦሮሚያ ሕግ ተጥሶ፣ የነዋሪዎች እንቅስቃሴ ተገድቧል፣ ትምህርት እንዲቋረጥ ተደርጓል፣ ባለሃብቶች ሰርተው ሃብት ማፍራት አልቻሉም፣ የመንግሥት ተቋማት ለህዝቡ አገልግሎት መስጠት አልቻሉም፣ . . . ስለዚህ የሕዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ ካለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ የትኛውንም እርምጃ ለመውሰድ ወስኗል'' ሲል የኦዲፒ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ አውጥቷል።

ኦዲፒ ይህን አስቸኳይ ስብሰባውን ያካሄደው በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎችን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ኮማንድ ፓስት ተቋቁሞ ወደ ሥራ የመግባቱ ዜና ከተነገረ በኋላ ነው።

ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል የተባለው ኮማንድ ፖስት የፌደራል፣ የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስን ያቀፈ መሆኑ ተነግሯል።

መቀመጫውን በአሶሳ ከተማ የሚያደርገው ኮማንድ ፖስቱ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች የመሸገውን የታጠቀ ኃይል በመደምሰስ የአካባቢውን ሰላም ያስከብራል ተብሏል።