ኦነግ ከመንግሥት ጋር ያደረኩት ስምምነት አልተከበረም አለ

አቶ ዳውድ ኢብሳ

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ድርጅታቸው ከመንግሥት ጋር ከስምምነት ላይ የደረሰባቸው ጉዳዮች ተግባራዊ እንዳልተደረጉ ተናገሩ።

አቶ ዳውድ ጉለሌ በሚገኘው የኦነግ ጽህፈት ቤት ውስጥ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ''እየተጣሰ ነው'' ያሉት ከመንግሥት ጋር የደረሱት ስምምነት ምን እንደነበረ ዘርዝረዋል።

በዚህ መሰረትም የተኩስ አቁም ስምምነቱ መከበር ፣ የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አስከባሪ እና ደህንነት አካል ገለልተኛ እንዲሆን ማድረግ፣ የኦነግ ሠራዊት ወደ መንግሥት ኃይል እንዲካተት ማድረግ ከኦነግ ሠራዊት አንፃር ከመንግሥት ጋር የተስማሙባቸው እንደሆኑ አመልክተዋል።

በተጨማሪም ባለፉት 27 ዓመታት የገቡበት ያልታወቁ የኦሮሞ ልጆች መጨረሻቸው ምን እንደሆነ መንግሥት ለህዝቡ እንዲያሳውቅ፣ ባለፉት 27 ዓመታት ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች ለሕግ እንዲቀርቡ ማድረግና ለውጡ ሁሉን አቀፍ እንዲሆን በሚሉ ነጥቦች ላይ ከስምምነት ላይ ደርሰው እንደነበር ተናግረዋል።

ነገር ግን የተጠቀሱት የስምምነት ነጥቦች ተግባራዊ እንዳልሆኑና እየተጣሱ መሆናቸውን ገልጸው፤ በምሳሌነትም ለተሃድሶ ስልጠና አርዳይታ ገብተው የቆዩ የድርጅቱ ወታደሮች አያያዝን አንስተዋል።

በስምምነቱ መሰረት 1300 የሚሆኑ የኦነግ ወታደሮች ስልጠና ወስደው የመንግሥት የጸጥታ አስከባሪ አካልን እንዲቀላሉ ወደ ማስልጠኛ እንዲገቡ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

"ይሁን እንጂ የኦነግ አመራሮች የሠራዊት አባላቱን እንዳይጎበኙ ተከልክለዋል፣ አንድ ፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እንዲሰለጥኑ ይደረጋሉ፣ በካምፑ ውስጥ የጦሩ አያያዝ እንደ እስረኛ እንጂ ሰልጣኝ አይደለም" በማለት ከስምምነት ያፈነገጡ ተግባራት እየተፈጸሙ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ አቶ ዳውድ የኦነግ አባላት በአዲስ አበባ ከተማ በደህንነቶች እየታፈኑ እየተወሰዱ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደምም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ አመራሮችን በመግደል ለግጭት መንስዔ የሆነው ኦነግ ነው ተብሎ የስም ማጥፋት እንደተፈፀመበት አመልክተው ክሱ ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል።