ባልተወለዱ ልጆች ላይ የሚከናወን የአከርካሪ ቀዶ ጥገና የእንግሊዝ የብሔራዊ ጤና ሽፋን አካል ሊሆን ነው

ዶክተሮች ባልተወለዱ ልጆች የአከርካሪ ቀዶ ጥገና በማከናወን ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሰሞኑን ባልተወለዱ ልጆች ላይ የሚከናወን የአከርካሪ ቀዶ ጥገና የብሔራዊ ጤና ሽፋን አካል ሊሆን እንደሆነ የእንግሊዝ የጤና ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ቀዶ ጥገናው ልጆቹ በማህፀን ላይ እያሉ የአከርካሪን ህዋሳት መጠገን የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።

ይህም የመራመድ ችሎታቸውን ለማሻሻልና በህፃናት ላይ ከሚከሰቱ የአከርካሪ ችግሮች ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና እክሎችን ለማሻሻል ያስችላል ተብሏል።

ባልተወለዱ ህፃናት ላይ የሚደረገው የአከርካሪ ቀዶ ጥገና በብሔራዊ የጤና ሽፋን ካገኙት መካከል ሲሆን ከሚያዝያ ጀምሮም ተግባራዊ ይሆናል።

በእንግሊዝ በየዓመቱ 200 የሚሆኑ ህፃናት ከአከርካሪ ችግሮች ጋር ተያይዞ የሚወለዱ ሲሆን፤ ይህም በቀሪው ህይወታቸው የእግር መሸማቀቅን እንዲሁም የመማር ችግሮችን እንደሚያስከትል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ከዚህ ቀደም ህክምናው የሚሰጠው ልጆቹ ከተወለዱ በኋላ የነበረ ሲሆን፤ በማህፀን ላይ እያሉ መሰጠቱ ለረዥም ጊዜ ጤናቸውን ከማሻሻሉ በተጨማሪ መንቀሳቀስ እንደሚያስችላቸው ተገልጿል።

ባልተወለዱ ልጆች ላይ የሚደረገው የአከርካሪ ቀዶ ጥገና ለመጀመሪያ ጊዜ በእንግሊዝ ላይ የተከናወነው በዚህ ዓመት ሲሆን፤ በለንደን በሚገኝ የዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ውስጥ በማህፀን ላይ ባሉ ሁለት ልጆች ላይ ነው የተካሄደው።

በቀደመው ጊዜም በማህፀን ላይ እያሉ ህክምናውን ለማግኘት ወደ ውጭ ሀገራት ይጓዙ ነበር ተብሏል።

በህፃናት ላይ የሚከሰተው የአከርካሪ ችግር በምን እንደሚመጣ በግልፅ ባይታወቅም የፎሊክ አሲድ እጥረት ተጋላጭነቱን እንደሚጨምር ባለሙያዎች ይናገራሉ።

"ምንም እንኳን በማህፀን እያሉ የሚደረገው ቀዶ ጥገና ለሁሉም አይነት እርግዝና የማይመከርና እንዲሁም የአከርካሪ የጤና እክልን ሙሉ በሙሉ ይፈውሳል ባይባልም የብዙ ህፃናት የጤና ሁኔታ ስለሚያሻሽል ዜናውን በይሁንታ ነው የተቀበልነው" በማለት ቻሪቲ ሻይን የተባለው ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ኬት ስቲል ይናገራሉ።