የኤርትራውን ሚኒስትር በጥይት ያቆሰለው መያዙ ተነገረ

ጄኔራል ስብሐት ኤፍሬም

የፎቶው ባለመብት, ERi-TV

የኤርትራ ኃይልና ማዕድን ሚኒስትር ጄነራል ስብሐት ኤፍሬም ማንነቱ ባልታወቀ ግለሰብ በጥይት ተመትተው እንደቆሰሉና ለከፍተኛ ህክምና ከአገር እንደወጡም ሰሞኑን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሲገለፅ ነበር።

የኤርትራ መንግሥት በጄኔራሉ ላይ ስለደረሰው ጥቃት ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥም በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር አቶ እስጢፋኖስ አፈወርቅ ግን የደረሰውን ጥቃት አውግዘው ሚኒስትሩ እንዲያገግሙ መልካም ምኞታቸው በትዊተር ገፃቸው አስተላልፈዋል።

"ስብሐት ከደረሰበት ጉዳት እንዲያገግም እመኛለሁ፤ ይህንን የፈሪዎች ሥራም አወግዛለሁ" ብለዋል።

በዚህ ጉዳይ ቢቢሲ ከኤርትራ መንግሥት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ግን አልተሳካም።

ደረሰ የተባለው ጥቃት በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ አድብቶ በነበረ አንድ ግለሰብ መፈፀሙንና ግለሰቡም በቁጥጥር ስር እንደዋለ ለቢቢሲ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ከአስመራ አሳውቀዋል።

ጄኔራል ስብሐት ለ19 ዓመታት የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን ፤ በመጀመሪያዎቹ የኤርትራ የነጻነት ዓመታት ደግሞ የአሥመራ ከተማ አስተዳደርና የጤና ሚኒስትር ነበሩ።

ጄኔራል ስብሐት ኤፍሬም ከሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ ከፍተኛ አመራሮች አንዱ ሲሆኑ የፖለቲካ ጽህፈት ቤት አባልም ናቸው።