ሳይንስ እንዲህ ይላል፦ «ስጦታ ከመቀበል፤ መስጠት ያዋጣል»

ሳይንስ እንዲህ ይላል፦ «ስጦታ ከመቀበል፤ መስጠት ያዋጣል»

የፎቶው ባለመብት, HECTOR RETAMAL

የፈረንጆቹ ገና ዛሬ ነው፤ የኛ ደግሞ ዳር ዳር እያለ ነው።

ታድያ በዓል ሲመጣ ስጦታ መሰጣጣቱ የተለመደ ነው። ስጦታ መስጠት የሆነ ደስ የሚያሰኝ ነገር አለው፤ «መቀበልን የመሰለ ነገር ደግሞ የለም» የሚሉም አይጠፉም።

አጥኚዎች ስጦታ ከመቀበል ይልቅ መስጠት የተሻለ የመንፈስ እርካታ እንደሚሰጥ መርምረን ደርሰንበታለን ይላሉ።

ለዘመድ፣ ለጓደኛ፣ ለቤተሰብ፣ ለፍቅረኛ ስጦታ ምን ልሸምት የሚለው ጭንቀት የበዓል ትሩፋት ነው። ታድያ እርስዎ በመጪው ገና ለወደዱት ሰው ምን ዓይነት ስጦታ ለመስጠት አሰቡ? «እራሴን» እንዳይሉን ብቻ!?!?!

ኤድ ኦብራያን የተሰኙ የአዕምሮ ጤና ባለሙያ «ደጋግሞ መስጠት ለመንፈስ እርካታ ነው፤ ሰላማዊ መኝታ ነው» ባይ ናቸው።

100 ተማሪዎች ተመረጡ፤ ለእያንዳንዳቸው አምስት አምስት አምስት ዶላር በየቀኑ እንዲሰጣቸው ሆነ። ታድያ ያንን አምስት ዶላር ማጥፋት ያለባቸው በተመሳሳይ ነገር ላይ ነው፤ አሊያም በስጦታ መልክ ማበርከት።

ግማሾቹ ገንዘቡን ለቀረበላቸው አገልግሎት ማመሰገኛ 'ቲፕ' አደረጉት፣ ግማሾቹ ደግሞ ለእርዳታ ድርጅት ለገሱት፣ የተቀሩቱ ደግሞ ያሻቸውን ሸመቱበት።

ተማሪዎች በየቀኑ ያንን በማድረጋቸው ምን ያክል እርካታ እንዳገኙ ያሳውቁ ዘንድ መጠይቅ ቀረበላቸው፤ ያለማንገራገርም ሞሉት።

ውጤቱም እንደተጠበቀው ሆነ፤ ሁሉም ተማሪዎች ባደረጉት ነገር እጅግ መደስታቸውን የሚለገልፅ ቅፅ ሞሉ። ነገር ግን ገንዘቡን በመጠቀም ያሻቸውን ነገር የሸመቱት ተማሪዎች ደስታቸው ከቀን ቀን እየቀነሰ እንደመጣ በሞሉት ቅፅ ላይ መስተዋል ተቻለ።

እርግጥ ነው፤ ከመቀበል መስጠት ለምን የተሻለ ደስታ ሊያጎናፅፍ እንደቻለ ግልፅ አድርጎ የሚያስቀምጥ ጥናት አልተገኘም።

ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች ይነሳሉ፤ ለምሳሌ ምን ዓይነት ስጦታ መስጠት ነው ደስታን የሚያጎንፅፈው? መጠኑ ምን ያክል መሆን አለበት? እና መሰል።

ሱዛን ሪቻርድስ የበጎ አድራጎት ሥራ ለሰጪው ምን ዓይነት የአዕምሮ ሰላም ይስጥ ይሆን? የሚለውን ጥያቄ ይዛ ጥናት አካሄደች፤ ውጤቱም በጎ ሆኖ ነው ያገኘችው።

በፈቃዳቸው የበጎ አድራጎት ሥራ የሚያከናውኑ የጭንቀት በሽታ ያለባቸው ሰዎች የተሻለ የአዕምሮ ደስታ እንደሚያገኙ የአጥኚዋ ሥራ ያሳያል።

የሱዛንም ሆነ የኦብራያን ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች ስጦታ በየቀኑ ቢሰጣቸው ፊታቸው ላይ የሚነበበው የደስታ ስሜት ከቀን ቀን እየቀነሰ እንደሚመጣ ነው።

ጥናቶቹ ላይ የተሳተፉ ሰዎችም ይህንኑ ነው በግልፅ ያሳዩት፤ በየቀኑ ስጦታ ለሌሎች ሰዎች መስጠት የቻሉቱ ተማሪዎች በየቀኑ ደስታቸው እየላቀ ነው የመጣው።

በቅርቡ ያረፈችው የኮምፒውተር ባለሙያ ኤቬሊን ቤሬዚን እንዲህ ትላለች «አንድ ግብ መምታት ጊዜያዊ ደስታ ሊሰጥ ይችል ይሆናል፤ ዋነኛው ደስታ ያለው ግን ያንን ግብ ለማሳካት በሚደረገው ትግል ውስጥ ያለው ሂደት ነው።»